Saturday, 16 August 2014

የመቶ አለቆቹ (ክፍል ሦስት)




3. የሮም መቶ አለቆች
3.1. በማረፊያው ሥፍራ (ሐዋ.22፥24)
     ቅዱስ ጳውሎስ ወደኢየሩሳሌም ጉዞ ከመጀመሩ በፊት የተነገረበት ትንቢት አስጨናቂ ነው፡፡(ሐዋ.21፥10-14) እንደሚገረፍና ለአህዛብ ተላልፎ እንደሚሠጥ ቢያውቅም፤ ጨክኖ ወደኢየሩሳሌም እየወጣ፦ ለሮሜ ቤተ ክርስቲያን “ለኢየሩሳሌምም ያለኝ አገልግሎቴ ቅዱሳንን ደስ የሚያሰኝ ይሆን ዘንድ ጸልዩ።”(ሮሜ.15፥33) በማለት እንዲጸልዩለት ያሳስባል፡፡ ጸሎቱና ጸሎታቸው ተሰምቶ “ወደ ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜ ወንድሞች በደስታ ተቀበሉን።” ብሎ ጸሐፊው ያስረግጠዋል፡፡(ሐዋ.21፥17)
   ሐዋርያው በኢየሩሳሌም የሚታወቀው “የጌታን ደቀ መዛሙርት እንዲገድላቸው ገና በመዛቱ፤ በቅዱሳንም ላይ ብዙ ክፉ በማድረጉ”ና (ሐዋ.9፥1፤13) ለኦሪት ህግ እጅግ በመቅናቱ ነው፡፡ አሁን ግን ታሪክ ተለውጦ ያሳድድ በነበረው በዚያ ነገር መሰደድ ጀምሯል፡፡ ብዙዎች ወደኢየሩሳሌም እንዳይሄድ አብዝተው የለመኑት ስለዚህ ነገር ነው፡፡ ጌታ መንፈስ ቅዱስ ግን ለእስራት ብቻ ሳይሆን በኢየሩሳሌምም እንኳ እንዲሞት ልቡን አስጨከነ፡፡ አገልግሎት ሰዎች ባዩልን አልጋ በአልጋ በሚመስለው ይቀናችኋል ቢሉንም ጌታ ባየልን በእሾሁና በጐርባጣው መንገድ በደስታ የሚቀበሉ እጆችን ያሰናዳል፡፡ ምስክርነትና ንስሐ በተካደበትና በተበደለበት መንገድ ሲሆን ብዙ ሥራ ይሠራል፡፡ በግልጥ ያሳደደውን ጌታን ባሳደደባትና ብዙዎችን በበደለባት ከተማ ቅዱስ ጳውሎስ በዚያች ከተማ ተገኝቶ ታላቅ ምስክርነትን መሰከረ፡፡ በአደባባይ ያሳደደው በአደባባይ ተሰደደ፡፡ ዛሬ ግን በዘፈን፣ በከህደት ትምህታቸው፣ በፖለቲካ … መርዝ ብዙውን ህዝብ በአደባባይ የበደሉ ንስሐቸውን በጓሮ መጨረሳቸውን ከየት እንደተማሩት ግራ ይገባል፡፡ እውነተኛ ንስሐና ምስክርነት በተሠራበት በዚያው መንገድ ቢሆን ብዙ ምህረት ከጌታ በሆነችልን ነበር፡፡

    ወደኢየሩሳሌም እንደመጣ በማግስቱ ወደቤተ መቅደስ በመግባት የኦሪትን ህግ “በጥንቃቄ በመፈጸም” ማገልገል ጀመረ፡፡ ከሰባት ቀን በኋላ ግን የነገሮች መልክ ተቀየረ፡፡ ቀድሞ በእስያ እርሱን የተቃወሙት አይሁድ፤ መቅደስ የሚያረክሰውና በየሥፍራቸው ህግን እየተቃወመ ያስተምር ነበር፥ ብለው ህዝቡን አውከው ጳውሎስን ከመቅደስ አውጥተው ጎተቱት፤ ሊገድሉትም ይደበድቡት ጀመር፡፡
   ቅዱስ ጳውሎስን ለመደብደብና ህዝቡን ለማወክ ምክንያት የሆናቸው “ጥሮፊሞስን ወደመቅደስ ያገባው መስሎአቸው ነበር”(ሐዋ.21፥29)፡፡ ሁልጊዜ ይህ ነገር ይሆናል፡፡ ለወንጌልና ወንጌላውያን ጥላቻ ያላቸው ሰዎች ወንጌላውያኑ የሚናገሩትንና የሚያደርጉትን በትክክልና በእርጋት ለማድመጥ ምንም ትዕግስት የላቸውም፡፡ በትክክል ባልተረዱት ነገር ሰውን ለመግደልና ለመደብደብ ቁጣቸው ይበረታል፡፡ እንደመቃኞ በሬ ተነድቶ “ስቀለው ስቀለው” የሚለው የአድማ ድምፅ ኢየሱስ ጌታችንን ካገኘው፤ ጳውሎስን ኋላም እኛን ትሁታን አገልጋዮቹን ማግኘቱ ትክክል ነው፡፡ አገልጋይ፥ ጌታውን አይበልጥምና፡፡ ዓለምም ለእውነትና ለእውነተኞች ያላት ጠባይ የመረረ ጥላቻና አድማ መሆኑ ያልተለወጠ የዛሬም መልኳ ነው፡፡
    ሊገድሉት ቁርጥ አላማ እንደነበራቸው ያወቀው ሻለቃ፥ ወሬውን እንደሰማ “ያን ጊዜ ወታደሮችን ከመቶ አለቆች ጋር ይዞ እየሮጠ ወረደባቸው፤ እነርሱም የሻለቃውንና ወታደሮችን ባዩ ጊዜ ጳውሎስን መምታት ተዉ።”(ሐዋ.21፥32) … ወታደሮቹም ተሸክመው ከህዝቡ መካከል ለይተው አወጡት፡፡ ወደመንደርም በቀረቡ ጊዜ ሻለቃውን ጳውሎስ ሊናገር አንዳች እንዳለው ፈልጎ ፈቃዱን ጠየቀው፡፡ መጀመርያ ላይ የቀናተኞቹ አሸባሪዎች አለቃ ቢመስለውም እውነቱን ከእርሱ ከሰማ በኋላ ፈቀደለት፡፡
  ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቲያን ከሆነ በኋላ በኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያንና  በአይሁድ ወገኖቹ መካከል መቀበል የሚያዳግተው ማንነት ነበረው፡፡ ለኦሪት ይቀና በነበረበት ቅንአቱ አሁን ለወንጌል ሲቀና አጊኝተውታልና ለቃላት በሚከብድ ጥላቻ ጠሉት፡፡ ድምጹን እንኳ ሊሰሙ በተጠየፉበት ሰዓት፤ ፈቃድ አጊኝቶ ምስክርነቱን ጀመረ፡፡(ሐዋ.22፥1-21) ምስክርነቱን ግን አላስጨረሱትም፡፡ አቧራ እያስነሱ፤ ልብሳቸውን እየጣሉ ስለጮኹ፤ ቅዱስ ጳውሎስን የጮሁበትን ምክንያት እንዲናገር በጠፍር ጅራፍ ሊገርፉት ገተሩት፡፡
     ሮማውያን አንድ ባርያ የሌላውን ሰው የተደበቀን ምስጢር እንዲያወጣ የሚያደርጉበት አንዱ ብልሃታቸው በጠፍር አለንጋ ላይ ገትረው፥ በጫፉ ላይ የአጥንት ስብርባሪዎች ወይም የብረት ቁርጥራጮች በተሸረበበት ጅራፍ ክፉኛ ገርፈው በማሰቃየት ነበር፡፡  አንድን ሮማዊ ግን በዚያ ዘመን በእንዲህ ያለ ቅጣት መቅጣት ፈጽሞ የማይቻል ነበር፡፡ ሊገረፍ የተዘጋጀበትንና ሮማዊ ዜግነት እንዳለው የተረዳው አንድ የመቶ አለቃ ፈጥኖ ነገሩን ከማስጠንቀቂያ ጋር ለሻለቃው አስታወቀው፡፡
     ይህ የመቶ አለቃ፦
1.     ቅዱስ ጳውሎስ በታሪኩ ከኦሪት የህግ ቀናኢነት ወደወንጌል ፊቱን ዘወር አድርጎ ምስክር እስከሆነበት ድረስ የተናገረውን ቃሉን በሚገባ አድምጦታል፡፡ ወንጌል ያስገርፍ(ሐዋ.5፥42)፣ በድንጋይ ያስወግር(ሐዋ.7፥58)፣ በሰይፍ ያሰይፍ(ሐዋ.12፥2)፣ በወህኒ እግር በግንድ አጣብቆ ያጣርቅ(ሐዋ.16፥24) … እንደነበር በሚገባ ያውቀዋል፡፡ ክርስትና በአይሁድም በሮማውያንም ተቀባይነት እንደሌለው (ዕውቅና እንዳልተሰጠው) በሚገባ ይረዳል፡፡
     ነገር ግን ጳውሎስን ሊገርፉት በሚገባ ወጥረው (ምናልባት በብረት አልጋ ላይ) ካሰናዱ በኋላ ትዕዛዝ ወዳስተላለፈው ሻለቃ ገብቶ ቆፍጠን ባለ ንግግር ሲናገር እናየዋለን፡፡ የመቶ አለቃው የጳውሎስን መገረፍ አልደገፈውም፡፡ “ትምህቱንም ሰምቶ” ሊጨክንበት አልወደደም፡፡ ምናልባት ሮማዊ ስለሆነ እንል ይሆናል፡፡ ነገር ግን አሁን ጳውሎስ የተያዘበት ነገር ከወንጌል ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ስለዚህ እንኳን ለመገረፍ፤ ለመገደል እንኳ ክርስትና በዚያን ዘመን የሚያበቃ በቂ ምክንያት ነው፡፡ ይህ የመቶ አለቃ ግን እንዲገረፍ እንኳ አልወደደም፡፡ ያለህግ ሰው ሊገድል አይገባም የሚል አንቀጽ ካላቸው ካመኑቱ የእስያ አይሁድ ይልቅ ይህ አህዛባዊ የመቶ አለቃ የሚገዛ የልብ ቅንነት አለው፡፡
2.    ወታደሮቹ ቅዱስ ጳውሎስን እየገረፉ እንዲመረምሩት ትዕዛዝ የሰጣቸው ሻለቃው ነው፡፡(ሐዋ.22፥25) በዚያ ላይ እንዲገደል ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ አለ፡፡(ሐዋ.22፥22) የመቶ አለቃው ግን እኒህን ሁለቱንም ብርቱ ነገሮች ጥሶ አለቃውን ባለማፍራት “ይህ ሰው ሮማዊ ነውና ታደርገው ዘንድ ካለህ ተጠበቅ” አለው፡፡ የሮማውያን ባዕለ ሥልጣናት በጠባያቸው ያሉትን ከማድረግ የማይመለሱ ግትሮችና ህጉን ሳይሆን ሌሎች ሰዎችን ለማስደሰት (በልታይ ባይነት) የሚሠሩ ናቸው፡፡(ማቴ.14፥9፤ሐዋ.12፥3፤25፥9)
  የመቶ አለቃው ይህን ሁሉ አልፎ ነው አለቃውን ገብቶ ያስጠነቀቀው፡፡  በሥልጣን አለም የኃላፊ ትዕዛዝ ህገ ወጥ እንደሆነ እየታወቀ እንኳ ከመታዘዝ በቀር መቃወም በብዙዎቻችን ዘንድ የማይታሰብ ነው፡፡ ከህጉና ከመመሪያው ይልቅ አለቃቸውንና የፖለቲካ ፓርቲያቸውን ለማስደሰት የሚሠሩ ጥቂት አይደሉምና፡፡ የአፍሪካ ፖለቲካ “እጅ እጅ ያለውና ገና ከሩቅ መጥፎ ሽታው አፍንጫ የሚሰነፍጠው” መሪና ተመሪ የተባሉቱ ለእውነትና ለህጉ ሳይሆን እውር ፖለቲካውን በእውር መሪዎች እየመሩ፤ “ይህ የምታደርጉት መልካም አይደለም” ሲባሉ የእውር ድንብራቸውን ወደመግደልና ማሰር እንጂ ሰከን ብሎ መስማት ስላልሆነላቸው ነው፡፡ የመቶ አለቃው ግን ለእውነትና ለህጉ የጨከነ ሰው ነው፡፡ ለእኛም ለእውነት መታዘዝ ይሁንልን፡፡አሜን፡፡
ጌታ በበጐነቱ ይማረን፡፡አሜን፡፡

ይቀጥላል …

No comments:

Post a Comment