Thursday 3 April 2014

ሁለተኛው መስቀል

Please read in PDF ;- huletegnaw Meskel

ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ የቱ ወንበዴ በግራ እንደተሰቀለ ሳይነግረን፤ ጌታ ግን በሁለቱ ወንበዴዎች መካከል መሰቀሉን ይነግረናል፡፡እንዳለመታደል ግራና በግራ መሆንን ፈጽሞ እንጠላለን፡፡ጸሎታችንም በቀኝ አውለኝ እንጂ በግራ አውለኝን አያካትትም፡፡መቼም ጌታ ፍየሎች(ኃጥአን) በግራ ይቆማሉ ሲል በሰማያዊ ዓለም ግራና ቀኝ አለ ሊለን አይደለም፡፡
     ግራና ጨለማ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍጥረቶች ናቸው፡፡እኛ ግን ለጠላት “ግዛትህ ነው” ብለን ስለለቀቅንለት ቅዱሱ ፍጥረት የጠላት መገለጫ ሆኖ ተገኘ፡፡ጌታ እግዚአብሔር ጨለማ በፊቱ የተገለጠ ብርሃን ነው፡፡ጨለማን ለሰይጣን ሰጥተን ጠልተነው በሰባኪዎቻችንና በመነኮሳቱ ቀሚስ መውደዳችን ግን እጅግ የሚገርም ነው፡፡
      ሰው በቦታ አይከብርም ወይም አያርፍም፡፡እግዚአብሔር ካልቆመበት ቀኝ እግዚአብሔር የቆመበት ግራ ይሻላል፡፡አዳም በውቧ ኤደን ገነት ቢቀመጥም ከእግዚአብሔር ስለተለየ በገነት መካከል ተቀምጦ ስደተኛ ፣ያላረፈ፣ ተቅበዝባዥ … ነበር፡፡ እግዚአብሔር ከሌለባት ገነት እንኳ የስደተኞች ቅዱሳን ማረፊያ አትሆንም፡፡እግዚአብሔር እንጂ ቦታ አያሳርፍም፡፡ዛሬ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በአለም ካለው ኃጢአትና ነውር የማይተናነስ ክፋት ይሰራባቸዋል፡፡ለ“ቅድስና ተለይተው” ከአለሙ ያልተሻሉ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ቦታ ቢያሳርፍ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ለብዙ ኃጢአተኞች ማረፊያ ሆነው በተገኙ ነበር፡፡በአንድ ወቅት በአንድ ቤተ ክርስቲያን ለህንጻ ማሰርያ ገቢ ማሰባሰቢያ ተብሎ በቢራና በሥጋ “የምግብ ባዛር” ተዘጋጅቶ ሳለ ፕሮግራሙን የሚመራው የመድረክ ሰው እንዲህ አለ፦ “ቅዱስ ጊዮርጊስን እየጠጣችሁ በእርሱ ትባረካላችሁ”፡፡(ጠጪዎችና ሰካራሞችን “የሚያጽናና ስብከት”)
     ጥቂት ያይደሉ ገዳማት፣አድባራትና አብያተ ክርስቲያናት በምንም መልኩ ከአለሙ ሥፍራ የማይሻሉ ናቸው፡፡የአምልኮ መልክ ይዘው የዕረፍት ቃልና መዝሙር የማያሰሙ አውደ ምህረቶችና አደባባዮችም ብዙ ናቸው፡፡ለዚህ ይመስላል በቀኝ ቆመናል እያልን በግራ ከምናስባቸው በሚበልጥ ክፋትና ነውር የተያዝነው፡፡ቦታ ቢያጸድቅ አዳም ከገነት የተሻለ የትም ሥፍራ አያገኝም፡፡
    የክርስቶስ እጆች ለሁለቱም ወንበዴዎች የተዘረጉ ናቸው፡፡እርሱ የመጣው መድኃኒት ለሚያስፈልጋቸውና ሸክም ለከበዳቸው ደካሞች ነው፡፡(ማቴ.11÷28) ይህ ወንበዴ በቀደመ ዘመኑ  ከሰራው ኃጢአትና በደል ይልቅ ዛሬም መስቀሉ ላይ ሆኖ እየተሳደበና እየተሳለቀ ነበር፡፡(ሉቃ.23÷32)ነገር ግን የመካከለኛው መስቀል ዝምታ የነበረበትንና ያለበትን በሚገባ ትኩር ብሎ እንዲመለከት አድርጎታል፡፡የፍቅር ዓይኖቹ ወቅሰውታል፡፡ያለንግግር ኃጢአተኝነቱን እንዲያይና የመስቀሉን ጽድቅ እንዲመለከትም በርህራሄ ተመልክቶታል፡፡
    ይህ ወንድም የሌላውን ኃጢአት ከመመልከት ተከልክሎ ራስን ማየት እንደሚገባ ያለህግ የሚናገረውን ባልንጀራውን ገስፆታል፡፡ቤተ ክርስቲያን ሌሎችን ለመውቀስ ከቃል የዘለለ የተገለጠ ህይወት ሊኖራት ይገባታል፡፡ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በህይወት ስላልተገለጠች መጽሃፍ ጠቅሰው የሚወቅሷት አለማውያንና ፖለቲከኞች ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በዝተዋል፡፡ይህ ወንበዴ ውንብድናውን ያወቀ፣የሌላውን ኃጢአት ደግሞ ከመናገር ዝም ያለ ነው፡፡መሰቀሉ እንደሚገባው፣ትክክልም እንደሆነ አምኖ ነው የተቀበለው፡፡ንስሐ ራስን በልክ አይቶ መውቀስና መክሰስ እንጂ የሌላውን ኃጢአት እያዩ እንደሚሻሉ ማሰብ አይደለም፡፡ዛሬ በክስና በመወነጃጀል የተያያዝንበት ዋናው መንገድ በ“እሻላለሁ” አጋንንታዊ ንስሐ ነው፡፡  ግመል እየዋጥን ትንኝ የምናጠራው ፈሪሳዊነት ዛሬም ስለሚገዛን ነው፡፡
    በእግዚአብሔር ፊት ራሳችንን የምንወቅስበት ጊዜ ስለሌለን ትርፍ የተባለውን ጊዜ ሁሉ ሰውን በመክሰስ ነው የምናሳልፈው፡፡የገዛ ነውሩን  በየቀኑ በእግዚአብሔር ፊት የሚገልጥ ሰው የባልንጀራውን ነውር በሰው ፊት ለመግለጥ ቅንጣት ታህል ብቃትና ድፍረት አይኖረውም፡፡ቢገባን እንኳን የሰውን ኃጢአት ልናወራ የተደረገልን ይቅርታና ውለታ በአድናቆት ውጦን ከምስጋና መድረክ መውረድ ባልተቻለን ነበር!!!
   አዎ! ይህ ወንበዴ የሌላው ድካም ሳይሆን የራሱ ነውር ተገለጠለት፡፡ ትልቁ የቅድስና ማዕረግ የራስን ኃጢአተኝነት ማወቅና ሁሌም በተመለስን ጊዜ የምትቀበል የእግዚአብሔር እጅ እንዳለች ማመን ነው፡፡ ወንበዴው ኃጢአቱን ተናዘዘ፡፡“ስለ አደረግነውም የሚገባንን እንቀበላለንና በእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው፤ ይህ ግን ምንም ክፋት አላደረገም ብሎ … ”(ሉቃ.23÷41)፡፡ቀጥሎም በእምነት ተናገረ …  ጌታ ሆይ፥ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ አለው።” ይህ ሰው ክርስቶስ መንግስቱ ከዚህ እንዳልሆነች ክርስቶስ ሲያስተምር አልሰማም፡፡ግና ራሱን ለእግዚአብሔር የሚሰጥ ሙሉውን ነገር ከእግዚአብሔር ይቀበላል፡፡መንግስቱ ልዩ እንደሆነች ከራሱ ከእግዚአብሔር ወልድ ተማረ፡፡“ልጆችሽ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ” እንዲል፡፡
   ጌታ ጸሎቱን አርሞ ሰማለት፡፡የቀና ልቡን እንጂ የሳተ አንደበቱን አላየም፡፡ስለዚህም ዛሬ ከእኔ ጋር በእግዚአብሔር ገነት ትኖራለህ አለው፡፡የሰውን ኃጢአት የሚያወሩና የማይመለሱ ፍጻሜያቸው ሞትና መቃብር ነው፡፡ራሳቸውን በንስሐ መንፈስና በትሁት ልብ የሚያዩ ግን መንገዳቸው ቅዱስ ማረፊያቸውም ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ገነት ነው፡፡የቁስልን ጥዝጣዜ የበደልን ዋጋ የሚያውቅ ለባልንጀራው ያዝናል እንጂ ባልንጀራውን ለሞትና ለሐሜት አሳልፎ አይሰጥም፡፡በኃጢአቱ ያገኘውን መስቀል ይገባኛል ብሎ ተቀብሎ በሌላ ከመፍረድ ራሱን ከለከለ፡፡ ስለዚህ መስቀሉን የሰውን ነውር በማውራት አላቃለለውም፡፡ደግሞም አላጉረመረመም፡፡
 ጌታ ሆይ መስቀላችንን እንዲህ ቀድሰው፡፡አሜን፡፡
        

1 comment:

  1. ተባረክልኝ ወንድሜ ሆይ፡፡ አምላክ ፀጋውን ያብዛልህ

    ReplyDelete