Friday 18 April 2014

መካከለኛው መስቀል

ለሁለት ሺህ ዘመናት ግለቱ ያልቀዘቀዘ፣ ኃጥአንን የማረከ፣ መናንያንን ከፍጡር ፍቅር ለይቶ ያመነነ፣ ደናግላንን “የዘመኔ ጌታ አንተ ነህ” እንዲሉ ያስመካ፣ ሊቃውንትና መተርጉማን ቀለምና ብራናቸውን አስቀምጠው እንዲመሠጡና እንዲደመሙ ያደረገ፣ ዘማርያን ክብራቸውን ያስጣለና በደስታ ያዘለለ፣ህጻናት ማር አንደበታቸው እየጣፈጠ የተናገሩለት፣ ሰማዕታት “ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ?” እያሉ የፎከሩት፣ ሰማይና ምድር የተራረቁት፣ የመለኮትን ክብር እንዳናይ የጋረደን መጋረጃ ከሁለት የተቀደደው ፣ከበረቱና ከመንጋው የተለዩት አህዛብ ወደአንዱ እረኛና ወደመንጋው የተጨመሩት ፣የሚያስጨንቀን ተጠርቆ በሞቱ ከመንገድ የተወገደው፣ አበው “እንዲህ ያለ ሰውን መውደድ አንዴት ያለ ፍቅር ነው?!” ብለው በመገረም የጠየቁት፣በወንበዴነት የዘላለም ባልንጀሮች የነበሩት በህይወቱ ጌታ ምርጫቸው የተለያየበት፣ከምድር እስከሰማይ የሚያድርሰው መካከለኛው መስቀል ጻድቃን የጸደቁበት፣ሰማዕታት የጨከኑበት ፣እናቶች ያነቡለት፣የሚወዱት ያለቀሱለት ድንቅ ምስጢር ነው፡፡
      የመካከለኛው መስቀል ለሁሉም ፍጥረተ አለም የሚማልድና ለሁሉም አዳማዊ ፍጥረትም እኩል እጁንም የዘረጋ ነው፡፡የመስቀሉ ደም ምርጫቸውን በንስሐ ለሚያስተካክሉ ኃጥአን ህይወትና የዘላለም ገነት ነው፡፡የመስቀሉ ደም ከአቤል ደም ይልቅ ምህረትንና የሚሻለውን የሚናገር “የማስተሥረያ ሥርዓት” ሆኖ በአብ ፊት ለኃጢአን ሁሉ የሚቆምና ስለመዳን፣ስለይቅርታ ሳይታክት የሚጮህ ነው፡፡(ዕብ.12፥23)

     በእርግጥ ለዘመነኛው ዓለም ይህ ጉዳይ የጭካኔና ኢሰብዐዊነት የጎደለው ሰቆቃን ጌታ ለምን ይደግፋል? የሚል ጥያቄ ቢያስነሳም እኛ ግን ለመለኮት ሀሳብ ተሸንፈን ይህ ምስጢር እንደምን ያለ ምስጢር ነው? እንዲህ ያለ ሰውን ማፍቀር እንደምን ያለ ሰውን ማፍቀር ነው? እያልን ከቅዱሳን አበው ጋር በመንፈስ መደነቅን እንተባበራለን፡፡
     ኃጢአተኛ በሥጋ፣በነፍስና በመንፈስ የሚቀጣውን ቅጣት እርሱ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለኃጢአተኞች ሙሉውን ቅጣት በመስቀል ተቀጣ፡፡ስለዚህም በፍርድ ተወግዶ ከከተማ ውጪ ወጥቶ በተሰቀለ ጊዜ ሁላችን እንደተቀሰፈና በእግዚአብሔር እንደተተወ ቆጠርነው፡፡በእርግጥ ቤተ ክርስቲያንም የዚህ እውነት እውነተኛ ግልባጭ ናት፡፡ሙሽራዋ እንዲህ በስቅላት ሲዋረድ እርሷ መከራን ጠልታ መኖር የምትሻ ሙሽሪት አመጸኛ ናት፡፡ቤተ ክርስቲያን እውነትን እየተናገረች  ከከተማ ውጪ በመናቅ ልትጠላና ልትሰቀልም ሙሽራዋንም በመምሰል ልትኖር ይገባታል፡፡
     የተሰበሰብነው ከምድር ከፍ ከሰማይ ዝቅ ብሎ በመስቀል በተሰቀለው ጌታ ክርስቶስ የመስቀሉ ጥላ ሥር ነው፡፡ሞቱ ነው እንደፉጨት ጥሪ ከሩቅ የጠራን፡፡ከሙታንም ዓለም ያነቃንና ወደህይወት አደባባይ በድፍረት እንድንወጣ ያበረታን፤ ህማምና ሞቱ ነው፡፡ከዘር ፣ከቋንቋ፣ከነገድ ፣ከብሔር ፣ከወንዝ ፣ከድንበር፣ከአጥንት ቆጠራ ነጻ ወጥተን ሁሉን የአዳም ዘር እንደቤተሰብ በመቁጠርና እኛም የተደመርነው በመካከለኛው መስቀል ደም ኃይልና ጉልበት ነው፡፡ዛሬ ዘርና አጥንት የምትቆጥር ቤተ ክርስቲያን እርሷ ክርስቶስን የማታውቅ አመንዝራ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡
      የመካከለኛው መስቀል ቤተ ክርስቲያንን የመሰረተው በደሙ ዋጅቶ ብዙ ነፍሳትን በመማረክና የራሱ ገንዘቦች በማድረግ ነው፡፡ከወንበዴ እስከጻድቅ ፣ከደካማ እስከብርቱ፣ከባለመድኃኒት እስከመድኃኒት ፈላጊው … በደም ዋጋ ገዝቶ የራሱ ምርጦች አድርጓል፡፡ቤተ ክርስቲያን ድንበር ሰርታ ፣ልጆቿን ለሁለት ከፍላ ከማየት በደሙ ኃይልና የፍቅር ጉልበት በብዙ ልትሸከም በብዙም ልትቀበል ይገባታል፡፡ነፍሳትን የማትጨምር፣ የማትማርክና የማታበዛ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን መስቀል መሸከሟ ያጠራጥራል፡፡እርሱ በሞቱ ለብዙዎች ህይወትና የህይወት መገኛ ከሆነ እርሷም በክርስቶስ ሞት ተሰውራለችና ለብዙ ኃጢአተኞች የህይወት ሽታ ልትሆን ይገባታል፡፡
     እልፍ ነፍሳት ያለንግግር የተሰበኩት የቀራንዮው በግ በዝምታ እንደሚታረድ በግ ተሸልቶ ባፈሰሰው ደም ነው፡፡ቤተ ክርስቲያን ያጌጠችበትን የሙሽርነቷን የደምና የጽድቅ ልብሷን በገዛ ነውርና ኃጢአቷ አውልቃ የክርስቶስን ወንጌልና የመስቀሉን ሥራ አወራለሁ ብትል ሰድበው የሚላገዱባትን እንጂ አንዳች ሰሚና አማኝ አታገኝም፡፡የዛሬዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ትልቁም ችግር ይህ ነው፡፡በዘረኝነት፣በሙሰኝነት ፣በዘፋኝነት፣በዝሙት … የተጠመዱና  የከረፋ አገልጋይና አማኝ በዝምታ ተሸክማ ወንጌል የምትጨብጥ ቤተ ክርስቲያን የፍርድ መሥፈሪያዋን ትሰፍር እንደሆን እንጂ የሚሰማ ጆሮ ፈጽማ አታገኝም፡፡
    ቤተ ክርስቲያን መዳን የሚሆንላት በመካከለኛው መስቀል ስታምንና ስትገዛለትም ብቻ ነው፡፡አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት የሚጓዙት ከመካከለኛው መስቀል ውጪ በአንደኛው ወንበዴ መስቀል ይመስላል፡፡ምክንያቱም የእውነተኛው መስቀል ፍሬ የመንፈስ ፍሬ ሊሆን ሲገባው ነገር ግን አማኞቻቸው ከሳሽና ትንኝ አጥሪ ብቻ የሆኑባቸው አብያተ ክርስቲያናት እጅግ የበዙና ለቁጥር ይታክታሉና፡፡የመካከለኛው መስቀል ግን ዛሬም እጅግ ድንቅና ከህሊናና ከመረዳት ከማስተዋልም የሰፋና የጠለቀ ነው፡፡በእውኑ ይህን ምስጢር ከትውልዱ ማን ይሆን ያስተዋለ? የእግዚአብሔር ክንድን ለማን ይሆን የተገለጠ?(ኢሳ.53፥1-3) ትውልድ ሆይ ይህን አስተውል፡፡
    ጌታ ሆይ በመስቀልህ ሞት መስቀላችንን እንድንሸከም ባርያዎችህን እርዳን፡፡አሜን፡፡
  


No comments:

Post a Comment