Sunday 27 April 2014

ደቀ መዛሙርት የጌታን ትንሳኤ ለምን ተጠራጠሩ?(ክፍል - 1)

    “ትንሳኤ ሙታንስ ከሌለ ክርስቶስ አልተነሳማ፤ክርስቶስም ካልተነሳ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ከንቱ ናት፤ደግሞም ክርስቶስን አስነስቶታል ብለን በእግዚአብሔር ላይ ስለመሰከርን ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል … ፡፡”(1ቆሮ.15፥13-16)
   “የክርስቲያን የሃይማኖት ትምህርት መነሻና መድረሻ፣በሞትና በትንሳኤ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው ቢባል ከእውነት የራቀ አይሆንም፡፡” (አበራ በቀለ(ሊቀ ጉባኤ አባ)፡፡(1996)፡፡ትምህርተ ሃይማኖት እና ክርስቲያናዊ ህይወት፡፡አዲስ አበባ፡፡ንግድ ማተሚያ ድርጅት(ማህበረ ቅዱሳን)፡፡ገጽ.209)

   “የክርስቶስ ትንሳኤ ለክርስቶስ አምላክና ለክርስቲያናዊ ትምህርታችን እውነተኛነት ከፍተኛ ምስክር ነው፤ምክንያቱም ክርስቶስ ሲገረፍ፤ሲዋረድ፤ሲሰቀል እንደዕሩቅ ብእሲ ተቆጥሮ ነበር፤ደካማም መስሎ ተገምቶ ነበርና፤ በመለኮታዊ ሥልጣኑ ሞትን አሸንፎ ሲነሳ ግን አምላክነቱን ኃያልነቱን ገልጧልና፡፡ እንዲሁም ክርስቶስ የተናገረው ያስተማረው ሁሉ ማጠቃለያው ትንሳኤው ስለሆነ ነው፡፡” (መልከጼዴቅ(አባ)፡፡1984፡፡ትምህርተ ክርስትና ፪ኛ፡፡አዲስ አበባ፡፡ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ድርጅት፡፡ገጽ.59

     ከመሠረታውያን የክርስትና ትምህርት አንዱና ዋናው የጌታን ትንሳኤ ማመንና መቀበል ነው፡፡የጌታን ትንሳኤ አለማመን ወይም መጠራጠር በጠቅላላ ክርስትናን እንደመካድ ይቆጠራል፤ከመናፍቃን እንደአንዱም ያስደምራል፡፡“ክርስቶስ ካልተነሳ እምነታችን ከንቱ ናት እስከአሁን ድረስ በኃጢአት አለን” ማለትን ያስደፍራል፡፡(1ቆሮ.15፥17) የክርስትና እምነት መገለጥ ነው፤እግዚአብሔር ራሱን በልጁ ገለጠልን፤ራሱ እግዚአብሔርም ከእኛ እንደአንዱ ሆኖ በእኛ መካከል ለእኛ ተገለጠ፡፡የዚህ ትምህርትና እምነት መደምደሚያ የተስፋውን ነገር ስናምን ነው፡፡ትልቁ የተስፋ ትምህርት ደግሞ የክርስቶስን ትንሳኤ በማመን የሙታንን ትንሳኤ ተስፋ ማድረግ ነው፡፡“የሙታንንም መነሳት ተስፋ እናደርጋለንና”፡፡(አንቀጸ ሃይማኖት)

    “ክርስቶስ ደግሞ ወደእግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለአመጸኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ህያው ነው፡፡”(1ጴጥ.3፥18)እንደተባለ ሁላችንን ክርስቶስ ወደአባቱ ያቀረበን ስለኃጢአታችን በሞተልን ሞቱ ነው፡፡ይህ መቅረብ ህያውና የዘላለም የሆነልን ደግሞ እርሱ ከሙታን መካከል በመነሳቱ ነው፡፡ይህን የጌታን ትንሳኤ ግን ደቀ መዛሙርቱ ለማመን ተቸግረው ፤በጣምም ተጠራጥረው ነበር፡፡
    ጌታ ኢየሱስ በዘመነ ሥጋዌው አጽንቶና ደጋግሞ ሲናገር የነበረው ዋና ነገሩ ሞቱና ትንሳኤውን ነው፡፡ያለሞቱ ህይወት ፤ያለደሙም ሥርየት ፤ያለትንሳኤውም የዘላለም ህይወትና የተረገጠ እውነት የለምና፡፡ጌታ ኢየሱስ ወደዚህ ዓለም የመጣበት ዋና ዓላማው ሞቶ አለምን ማዳን ነው፡፡ጌታና ንጉሥ ሲሆን ሊሞትና ሊዋረድ በአላማ የመጣ አንድ እርሱ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ኑዛዜ ሟች ካልተናዘዘና ካልሞተ እንዳይጸና በክርስቶስ ሞት ግን አብ የልጁን ህይወትና ትንሳኤ በእርሱ ለምናምን ልጆቹ በሞቱ ኑዛዜ አድሎ፤በትንሳኤው ኃይል አጽንቶልናል፡፡
     ጌታ ኢየሱስ ሞቱ እንደአባቱ ፈቃድ በጊዜው እንደሚሆንና የማይቀርም እንደሆነ ባለመታከት የተናገረውን ደቀ መዛሙርቱ አለማስተዋላቸው ብቻ ሳይሆን የ“እነሳለሁ” ንግግሩንም ስለሌላ እንጂ ስለራሱ መሆኑን እውነት አልመሰላቸውም፡፡(ዮሐ.2፥21)ምንም እንኳ ግርማ መለኮቱን ከገለጠላቸው በኋላ ሞቱንና ትንሳኤውን ደጋግሞ ቢነግራቸውም (ማቴ.16፥21) እርሱ በሦስተኛው ቀን ከሙታን መካከል ሲነሳ “ቅዠት መስሎ ታይቷቸው” ፣ “ነቢያት የተናገሩትን ሁሉ ልባቸው ከማመን ዘግይቶ”(ሉቃ.24፥11፤25)፣“የተወሰደና የተሰረቀ መስሏቸው”(ማቴ.28፥15፤ዮሐ.20፥15)፣ “የተቸነከረ ችንካሩን በጣት የተወጋ ጎኑን በእጅ ዳስሼ ካላየሁ” (ዮሐ.20፥25) በማለት በፍጹም አላመኑም ነበር፡፡ ለመሆኑ ደቀ መዛሙርቱ የጌታን ቃል ፍጹም እንዲዘነጉና ትንሳኤውን እንዲጠራጠሩ ያደረጋቸው ነገር ምንድር ነው? ስንል ከመጽሐፍ ቅዱስ አራት ምክንያቶችን ማውጣት እንችላለን፡፡
   1. ወሬ ፦ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን የጌታ ትምህርት ብቻ አላስጨነቃቸውም፤ሞቱም አላስደነገጣቸውም፤ ከሙታን መካከል እነሳለሁ ማለቱ ግን ብዙ አሸብሯቸዋል፡፡ስለዚህ ገድለውት እንኳ በማግስቱ መጥተው ከጲላጦስ ጋር መከሩ፡፡(ማቴ.27፥62) የጌታ ድምጹ ብቻ ሳይሆን ዝምታውም ብዙዎችን ይወቅሳል፡፡ያቺን አመንዝራ ሴት ከሳሾች አካልበው ይዘው መጥተው ፤በብዙ ሲከሷት “ኢየሱስ ግን ጎንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ይጽፍ ነበር”(ዮሐ.8፥6) ዝምታው የሁሉንም ህሊና ወቀሳቸውና ሁሉም ጥለዋት ሄዱ፡፡እርሷንም ደግመሽ ኃጢአትን አትሥሪ አላት፡፡
      ሙሽራው ኢየሱስ በቅድስናው ያለንግግር ይወቅሳል፡፡ሙሽራይቱ ቤተ ክርስቲያንም ያለንግግር ኃጥአንን ልትወቅስ ይገባታል፡፡ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንን እውነተኛው መሲህ “ሞቶም” ይወቅሳቸዋል፡፡የሚወቅሳቸው እያሳጣ ሊከሳቸው አይደለም፡፡በእርሱ ስለማያምኑ በማመን እንዲመለሱ እንጂ፡፡(ዮሐ.16፥10) እነርሱ ግን ይህን የፍቅር ወቀሳ ቸል ብለው ለሚብስ ክፋት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጡ፡፡ለአሳዳጅና ለከሳሽ መልስ መስጠትና መከራከር ያደክማል፤ወሬውንም መስማት ያቆስላል፤ “ዝም ብሎ የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ማድረግ ግን መልካም ነው፡፡”(ሰቆ.ኤር.3፥26)አዎ! ዝም ብሎ ከጸሎት ጋር!!!
     ስለዚህም “እኛ ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት” የሚለውን ቀድመው የተዘጋጁበትን የሐሰት ወሬ (ማቴ.27፥64) የሐሰት ወሬኞችን በገንዘብ ገዝተው በህዝቡ መካከል አስወሩት፡፡(ማቴ.28፥12) ይህም ወሬ ፈጥኖ ከሁሉም ጆሮ ደረሰ፤ አብዛኛው ህዝብም(ደቀ መዛሙርቱን ጨምሮ) አምኖ ተቀበለው፡፡
   ከእውነተኛውና ከተረገጠው ወሬ ይልቅ ሐሰተኛና የተፈበረከ ወሬ ከብዙ ሰው ዘንድ የሚደርስበት እግሩ እጅጉን ፈጣን ነው፡፡ቶሎ ተቀባይነት የማግኘት ዕድሉም ሰፊ ነው፡፡(ዕድሜው የጤዛ ዕድሜ መሆኑ በጀ እንጂ)፡፡የእስራኤል ልጆች ከነዐንን ሊወርሱ በቀረቡ ጊዜ  ምድሪቱን ይሰልሉ ዘንድ አሥራ ሁለት ሰዎችን ሙሴ እንዲልክ እግዚአብሔር አዘዘው፡፡ሙሴ እንደትዕዛዙ አደረገ፡፡አሥራ ሁለቱ ሰዎች ሄደው ምድሪቱን አርባ ቀን ሰልለው ሲመለሱ ግን ሁለት አይነት ወሬ ይዘው መጡ፡፡ክፉና ደግ፡፡ከደጉ ይልቅ ክፉው ወሬ ወዲያው እውቅና አጊኝቶ “ … ህዝቡም በዚያ ሌሊት አለቀሱ … በግብጽ ምድር ሳለን ምነው በሞትን ኖሮ! …አሉ”፡፡(ዘኁ.14፥1-3) ነገር ግን ክፉውን ወሬ የሰሙና ያመኑ ሁሉ በዚያ ምድረ በዳ ረግፈው ቀሩ፡፡መልካሙን ወሬ ያመጡቱ ኢያሱና ካሌብ ብቻ በህይወት ተቀመጡ፡፡(ዘኁ.14፥38)
   በእርግጥ እናውቃለን፤ አለሙ በክፉ የተያዘ ነው፡፡(1ዮሐ.5፥19) ከእውነተኛው ይልቅ ሐሰተኛው እንደገነነ እናውቃለን፡፡ይህ ሁሉ ግን እውነተኛው ፀሐይ ክርስቶስ እንኪወጣ ነው፡፡ኢያሱና ካሌብ ከአሥሩ አንጻር በቁጥር ትንሽ ናቸውና ላይታመኑ ይችላሉ፡፡ጌታ ሲመጣ ግን ጥቂቶቹ ምድርንና በረከቷን ህይወትንም ይወርሳሉ፡፡እውነት በቲፎዞ ብዛት ቢሆን ኖሮ ገና “ያኔ” ነበር ያበቃልን፡፡እውነት ግን ከአንዱ ከክርስቶስ ጋር ብቻ መኖር ነውና ደስ ይበለን!!!

ይቀጥላል…

1 comment: