Wednesday, 16 April 2014

ጌታ ለምን የደቀ መዛሙርቱን እግር አጠበ?

መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገዋል የሚባሉ  ልማዶች በየጊዜው ባለመሰልቸት ሊመረመሩና ሊጤኑ፤ ግድፈት ሲገኝባቸው ሊስተካከሉ፤  መጽሐፍ ቅዱሳዊውን እውነት እንደጨበጡ ያሉ ከሆኑ ደግሞ በፀሎትና በቃሉ ቅጥርነት ሊጠበቁ ይገባቸዋል፡፡ በቤተ-ክርስቲያን ቀኖና  መሠረት ከበዓለ ሥቅለት በፊት ባለው ሐሙስ እግር  የማጠብ ልማድ ስላለ ከታላላቆች ሊቃነ - ጳጳሳት “እንደማዕረጋቸው” እስከታች ያሉቱ የሌሎች “ታናናሾቻቸውን” እግር ያጥባሉ፡፡በዕለቱም ስለትህትና ተገልጦ ይሰበካል፡፡ በእርግጥ እውነተኛ  ትህትና ትልቁ ትንሹን ሲያገለግል እንጂ ትንሹ  ትልቁን ሲያገለግል ብቻ አይደለም፡፡
 በእኛ ማህበረሰብ ውስጥ  “ትልቅ” የተባሉት አካላት ትልቅነታቸውን እንዳስከበሩ መኖር እንጂ ፈፅሞ  ዝቅ ብለው ማገልግል አይሆንላቸውም ቢያደርጉትም በዓመት አንዴ እንደበዓል እንጂ የዕለት ተዕለት በጎ ምግባር ሲሆን አይስተዋልም፡፡ ጌታ ግን ይህ የእግር ማጠብ ሥርዓትም እንደበዓል  በዓመት አንዴ ሳይሆን በየእለቱ እንድናደርገው በፍቅር አዝዞን ነበር፡፡(ዮሐ- 13፥15) ይሁን እንጂ ዘመናችንን ሙሉ ባልጀራችንን እየተጠራጠርን፤ በኑሮዐችን ሁሉ በክፉ ቅንዐት ነቅዘን ያለቅነው፤ ከእኔ ይልቅ የባልንጀራዬ ጥቅም  ይቅደም(ፊሊ.2፥4) ከማለት የተስገበገብነው... የልማድ እግር ማጠብ እንጂ እውነተኛ ትህትና በውስጣችን ስለሌለ ነው፡፡ በተለይ የቤተ-ክርስቲያን መሪዎች፣ የሀገር መሪዎችና  ባዕለሥልጣናት የሾማቸው እግዚአብሔርና አደራ አሳልፎ የሰጣቸውን ህዝብ ሲገዳደሩና ሲዘባነኑበት እንጂ ዝቅ ብለው በትሁት ልብ ሲያገለግሉት ማግኘት እንደ ዔሊ ዘመን የእግዚአብሔር ራዕይና ቃል ብርቅ ነው፡፡ (1ሳሙ.3፥1)

ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ በምድር በተመላለሰበት በገዛ ዘመኑ(1ጢሞ.2፥1) የኖረውና በህይወት የተመላለሰው የአባቱን ፈቃድ ደስ በማሰኘት ነው፡፡አዎ! እርሱ ከሰማይ የወረደው የአባቱን ፈቃድ ለመፈፀም  (ዮሐ.6፥38)፤ የሁል ጊዜ ረሀብና ጥማቱም የአባቱን ፈቃድ በመፈፀም እንደሆነ “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈፅም ዘንድ ነው” በማለት በግልጥ ተናግሯል፡፡      (ዮሐ.4፥34)፡፡  ጌታ ኢየሱስ የአባቱን ፈቃድ ከመፈፀምና እንደልጅ ከመታዘዙ የተነሣ አብ ሁሉን በእጁ አሳልፎ ሰጥቶታል፡፡ “ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል” (ማቴ- 11፥27)፡፡ ክርሰቶስ አባቱን ዝቅ ብሎ እስከውርደት ሞት(ፊሊ.2፥8)፤ ወላጆቹንም በእሺታ መንፈስ ስላገለገለ “በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚእብሔርና በሰው ፊት ያደገ” ነው፡፡ (ሉቃ.2፥52)፡፡  ከዚህ መታዘዙም የተነሳ አብ ለእኛ  ያለውን ፍቅሩን (ዮሐ.3፥16) በእርሱ ገልጦ የእግዚአብሐር እቅድ በኢየሱስ ህይወት ስለተፈፀመና ኢየሱስም ይህን ስላወቀ የደቀ-መዛሙርቱን እግር ሊያጥብ ተነሣ፡፡ (ዮሐ.13፥3)
   ዘወትር  ከእግዚአብሔር ይልቅ የሰውን ሐሣብ ደስ ለማሰኘት መጣር ጭው ባለ በምድር በዳ ዓለም ምቹ ጥላ አለ ብሎ የመከራከር  ያህል ከንቱ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰዎችን የታዘዝንበትና የሰማንበት ዘመናችን የከሰርንበትና “በወይኔ ምነሁ ባልሰማሁ ኖሮ?” በሚል ፀፀት እንደሳማ ልብላብ ህሊናችን የተለበለብንበት ጊዜ ነው፡፡  እግዚአብሔርን መስማት ከመከራ ያሳርፋል፤ በእርጋታም ያስቀምጣል፡፡ (ምሳ.1፥33) ቤተ ክርስቲያን ከፖለቲካ መሪዎች ጋር እየተቋመረች፤ ከዘፋኖችና አመንዝሮች ጋር እየተመቻመቸች... ከእግዚአብሔር ይልቅ ወደዚያ እያደላች… የፖለቲካ መሪዎቹ የሚመሩትን ህዝብ ሳይሆን ጠንቋይና አስማተኛ ደባትር እየሰሙ ከመሳት እግዚአብሔርን ቢሰሙ እግዚአብሔር “ሁሉን” በእጃቸው አሳልፎ  ይሰጣቸዋል፡፡ (በእርገግጥ ግን ክፉውን ዓለምና ጠንቋይ እየሰሙ እግዚአብሔርን አለመስማት እንዴት ልብ ይሠብራል?!)
   ሁለተኛው ክርሰቶስ ኢየሱስ የደቀመዛሙርቱን እግር ያጠበበት ምክንያት “ከእግዚአብሔር እንደወጣ ወደእግዚአብሔርም እንደሚሄድ ስላወቀ” ነው፡፡  (ዮሐ.13፥3) አዎ! እርሱም “ከአብ ወጥቼ ወደዓለም መጥቻለሁ፤ደግሞ ዓለምን እተወዋለሁ ወደአብም እሄዳለሁ፡፡”(ዮሐ.16፥28)ብሎ ተናግሯል፡፡ክርስቶስ መነሻው ሰማይ መድረሻውም ሰማይ ነው፡፡ደቀ መዛሙርቱም ምንም እንኳ ዛሬ በአስጨናቂውና በክፉ ዓለም የተከበቡ ቢሆኑ፤ቢያለቅሱም፤ቢያዝኑም(ዮሐ.16፥20) በኋላ ግን በፍጻሜው በሰማይ ያላቸውን ዘላለማዊ ደስታ እንዲያስቡና እንዲያምኑ ወዷል፡፡ከዚህም የተነሳ ትልቁ ጌታ “ከእራት ተነሳ ልብሱንም አኖረ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብ በታጠቀበት ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ፡፡”(ዮሐ.13፥4-6)ብዙ ጊዜ በነውርና በበደል በድፍረትም ኃጢአት የምንጨመለቀው የአድራሻ ስህተት ስላለብንና ሰማይና የሰማያት አባታችንን ስለምንዘነጋ ነው፡፡
     እናንተ “በዓመት አንዴ” እግር የምታጥቡ ሊቃነ ጳጳሳት፣ጳጳሳት፣ኤጲስ ቆጶሳት፣ቆሞሳትና ቀሳውስት … መምህራንና ወንጌላውያን ሆይ …
v ኢየሱስ የአባቱ ፈቃድ በእርሱ ስለተከናወነ ደስ እየተሰኘ
v ከአባቱ እንደወጣ ወደአባቱ እንደሚሄድ ስላወቀ ጎንበስ ብሎ የአገልጋዮቹን እግር አጠበ፡፡እናንተስ? እኛስ ይህ ምስጢርና እውነት ገብቶን ይሆን?
ጌታ ማስተዋሉን ያብዛልን፡፡አሜን፡፡
 



No comments:

Post a Comment