Monday 31 March 2014

መልካም አገልጋይ ማን ነው ?


    ሳያነቡ የሚመረምሩ ፤ ሳይመረምሩ የሚተቹ ፤ በልማድ እውቀት የሚመላለሱ ፤ በደቦ ለስድብና ለድብደባ የሚጠራሩ ፤ ሳያምኑ የሚመሰክሩ ፤ በክርስቶስ ማዳንና ወንጌል ላይ  እልፍ አማራጭ የሚያኖሩ፤  ከልባቸው ሳይሆኑ አሜን የሚሉ፤ “ስለብልጥግና  ወንጌል” የፀጋውን ወንጌል የሚክዱ፤ እንኳን  ሳያዩ እያዩ እያነበቡ እየሰሙ የማያምኑ፤ በመልካም መሸነፍን  በባርነት  እንደመገት ጠልተው በክፉ  የሚሸንፉ፤ ስለእግዚአብሔር  መሳደብን  እንደፅድቅ  የሚቆጥሩትን ፤  “አንዳንዴ  በዋልድባም ይጨፍራል” በሚል ተረት  በእግዚአብሔር ጉባኤ በሥጋ አምሮት የሰከሩ … በእግዚአብሔር  አምልኮ ላይ እያመነዘሩ በአፋቸው ግን  እኔ ‹‹የጌታ መልካም ባርያ ነኝ›› የሚሉ  አማኞችን አይናችን ማየት ከጀመረ  ሰነባብቷል፡፡ 
    በፀሎት  ሳያጥሩ  የተዝረከረከ መታጠቂያቸውን  ጨብጠው   የሚቸኩሉ ፤  የእዩልኝና  ስሙልኝ  ድምፀትና ፉጨጽ ለማሠማት የሚንቀለቀሉ፤ በንግድ ብልሐት ካሴትና መፃህፍቱን  የሚሽጡ  ‹‹መንፈሳዊያን ነጋዴዎችን››፣ የደመቀ  መድረክና ኪስ የሚያሞቅ በጀትና አበል ያለበት እንጂ ለአንድ ነፍስ የማይገዳቸው ወሮ በል አገልጋዮችን፤ በህዝብ ጫንቃ እየኖሩ በህዝብ ላይ የሚቀማጠሉ፤ ፍትፍት ጎርሰው ምርቅ ስብከታቸውን የሚሰንጉ ፤ ድኃ ሲያዩ ቀሚሳቸውን ሰብሰብ አድርገው ፊታቸውን  አጨልመው  የሚራመዱ ባዕለጠጋ ሲያዩ  ደግሞ ቀሚሳቸውን  አንዘርፈው ጌታዋን እንዳየች ውሻ የሚቅበጠበጡ፤ ባዕለጠጋና  እግዚአብሔር  የተምታታባቸው… ስለገንዘብና  ክብራቸው ወንጌል የሚሸቃቅጡ ……  ከአፋቸው ግን ‹‹እኔ የጌታ አገልጋይ ባርያ ነኝ›› የሚሉ ለቁጥር  የሚታክቱ  አገልጋይ ካህናት ፤ ዲያቆናት፤  ሰባክያን፤ ዘማርያንን … እያየን ያላረርን ያልከሰልን ጥቂት አይደለንም፡፡
      ደቀ መዛሙርት በጻፉት መልዕክታት መግቢያ ላይ ራሳቸውን ‹‹የኢየሱስ ክርስቶስ ባርያ›› ብለው አስቀምጠዋል፡፡(ሮሜ.1÷1፤ፊሊ.1÷1፤ቲቶ1÷1፤2ጴጥ.1÷1፤ያዕ.1÷1፤ይሁ.1÷1)፡፡ባርያ የሚለው ቃል በግሪኩ ሁለት ትርጉሞች ያሉት ነው፡፡


1-     የራሱን ኑሮ ለመኖር ነጻነት የሌለው ሙሉ ለሙሉ ለጌታው ፈቃድ የተሰጠና
2-    በራሱ ፈቃድ ጌታውን ለማገልገል የመረጠ(ምርጫ ያደረገ)ማለት ነው፡፡
መልካም አገልጋይ በራሱ ፈቃድ ወይም ምርጫ ትልቁን ጌታ ሊያገለግል ራሱን ለይቶ ያጨ ነው፡፡በራሱ ፈቃድ ራሱን ለትልቁ ጌታ እንዲያጭና እንዲለይ የሚያደርገው በቂና ትልቅ ምክንያት አለው፡፡የመስቀሉ ሞት፡፡
     ቀድሞ ይገዛን ከነበረው ‹‹ጌታ›› የተነሳ ሁላችን በደለኞችና ኃጢአተኞች የቁጣ ልጆችም ነበርን፡፡(ኤፌ.2÷1፤ሮሜ.5÷12)በዚህም የቀደመው ‹‹ጌታ›› ምንም ሳይራራልን ለሞት አሳልፎ ሰጠን፡፡ መልካም አገልጋይ እንድንሆን የወደደው ፈጣሪው ጌታ ግን ከድካማችንንና ከኃጢአታችን ነጻ አውጥቶ ወደህይወት መንገድ መራን፡፡የቀደመው ‹‹ጌታ›› ለኃጢአትና ለሞት አሳልፎ የሰጠን ብቻ አይደለም፡፡ዘላለማችንን በገሀነም የቀጠረልን እንጂ፡፡የኋለኛው ጌታ ግን ኃጢአታችንን አስተሰርዮ ሞታችንን ሞቶ ዘላለማችንን በዘላለም ደስታና ህይወት እንኖር ዘንድ ኪዳን ሠጠን፡፡ማንም ቢሆን ከጠዋት እስከእኩለ ሌሊት በብዙ ድካም ያለዕረፍት እያሠራው በወር አንድ ሺህ ብር ከሚከፍለው ጌታ ይልቅ ከጠዋት እስከሠርክ አሰርቶ በወር ሦስት ሺህ  የሚከፍለውን ጌታ እንዲመርጥ አይካድም፡፡
   ዲያብሎስ በቀደመው ዘመናችን የገዛን አስጨንቆንና በብዙ ጣዕር ነው፡፡እርሱ እየገዛን በነበረበት ዘመናችን ውስጣችን እየተጠየፈ እንኳ ኃጢአትን እንፈጽም፤እናደርገውም ነበር፡፡ መለየት እየፈለጉ በጽኑዕ ትብታብ ተይዞ ለማይወዱት ጌታ እንደመኖር ያለ ባርነት እንዴት ያለጽኑዕ ባርነት ነው!!! ብዙዎቻችን እንዲህ ነበርን፡፡አስጨንቆ ለሚገዛን፤ሞትንም ለደገሰልን ባሮች ነበርን፡፡ጌታ ግን ድንቅ ነው! ቀድሞ በእንዲሁ ፍቅር ወደደን፤ በልጁም ሞት ታረቀን፤ የዘላለምንም ርስት በልጁ በኩል እንወርስ ዘንድ በደም ማህተም አተመልን፡፡
   የቀደመው “ጌታ” አስጨንቆ የኋለኛው ጌታ ፍቅሩን ሰጥቶ፤የቀደመው “ጌታ” አዋርዶን የኋለኛው ጌታ አለልክ ከፍ ከፍ አድርጎን ፤የቀደመው “ጌታ” ከሰው በታች በእንሰሳ ባህርይ አኑሮን የኋለኛው ጌታ የእርሱን መልክ እንይዝ ዘንድ ወንድሞቹም እንባል ዘንድ ሳያፍርብን የተዛመደን … የዘላለምን ክብርና አክሊል የሸለመን … በአባቱም ዘንድ ብዙ መኖርያን ያዘጋጀልን ጌታ … ነው፡፡ እንኪያስ ይህን ጌታ ማን ሊተካከለው ይችላል!? ለዚህ ጌታ በፈቃዱ እንደመገዛት ያለተድላና ደስታስ ከወዴት ይገኛል !?
    ይህ ነገር ስለገባቸው መናንያን በከተማና በዱር መንነውለታል፤ ሰማዕታት በእሳትና በስለት ተቃጥለውለታል፤ተመትረውለታል፤ ባህታውያንን ይህንን አለምና የዚህን አለም ክብር ሁሉ ንቀው አንድ እርሱን መርጠውታል፤ መምህራን የትምህርታቸውም የህይወታቸውም ርዕስ አድረገውታል፤ አማኞች ላያፍሩበት ጮኸው ዘምረውለታል ዞረው ሰብከውታል፤ ዛሬ ግን ያገኘን ነገር ያስፈራል፡፡መልካም አገልጋይነታችን በሁኔታዎች ኃይሉን ተሰልቧል፡፡ገንዘብ ከትልቁ ጌታ በልጦብን “ሞቅ አድርገው ወዳልከፈሉን” ላንሄድ ተማምለናል፡፡ አገልግሎቱንና አገልጋይነቱን ላገለገለን ጌታ ሳይሆን ለገዛ ሆዳችንና ለክብራችን፤ ለአውሮፓና ለአሜሪካ ቪዛ ማግኛ አድርገነዋል፡፡
     በወንጌሉ ስም የተሰበሰበው ብር ትዳር ማሞቂያ ጎጆ መውጪያ ሆኖ እልፍ ድሆች ተራቁተዋል፤ ወንጌሉ በሩቅ ላሉት እንደዳይደርስ እግሩን አስረነዋል፡፡አዎ! ጌታ የሚዘገይ መስሎን ተግተን በመልካም ባናገለግል ታማኙ ጌታ ድንገት የሰጠንን ዲናርና መክሊት ሊሰበስብ ይመጣል፡፡ ጽዋችን ከግብዞች ጋር እንዳይሆን፣ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት እንዳገኘን፣ ከሁለትም እንዳይሰነጥቀን … እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ” እንዳይለን (ማቴ.24÷48፤25÷14፤41) አውቀን ከተኛንበትና ከድንዛዜያችን እንንቃ፡፡ጌታን በአማራጭ ሳይሆን በምርጫ የምናገለግል ትሁታን መልካም ባርያዎች እንሆን ዘንድ ጸጋ አብዝቶልናልና፡፡
የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ይባዛላችሁ፡፡አሜን፡፡
        

No comments:

Post a Comment