በቤተክርስቲያን ቀኖና መሰረት ሰባተኛዉ
ሳምንት የጌታ ፆም ስያሜ ኒቆዲሞስ ይባላል፡፡የሚነበበም የቅዱሱ ወንጌል ክፍል ደግሞ ዮሐ.3÷1 ጀምሮ ያለዉ ነዉ፡፡የዮሐንስ ወንጌል
እንደሌሎቹ ወንጌላውያን የኢየሱስ ታሪክ ላይ አያተኩርም፡፡ የኢየሱስን ክርስቶስ መሆን እያስረገጠ የአዲስ ኪዳንን የአምልኮ መገለጫና
መንፈሳዊነትን እያጎላ የተጻፈ ቅዱስ ወንጌል ነው፡፡ገና ወንጌሉን ሲጀምር አከላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስን ጨለማ የማያሸንፈው፣ ሁሉ
በእርሱ የሆነ፣ ጸጋንና እውነትን የተመላ፣ የእኛንም ሥጋ የነሳ ህይወትና ጸጋን አስገኚም ቃል እንደሆነ አበክሮ ይመሰክራል፡፡(ዮሐ.1፥1-15)
ጌታ መንፈሳዊ የማያረጅ ልጅነትን ለሽማግሌውና ለትልቁ ባለሥልጣን ለኒቆዲሞስ እንዳስተማረውም የዘገበልን የዮሐንስ ወንጌል ብቻ ነው፡፡
ኒቆዲሞስ የአይሁድ አለቃ የሆነ ፈሪሳዊ ባለሥልጣን ነው፡፡በጌታ ኢየሱስ
ዘመን ብዙ አይሁድና ፈሪሳውያን ጌታን ያሳድዱት ፤ሊገድሉትም ይፈልጉት ነበር፡፡(ዮሐ.5፥16፤7፥19) የህጉን ምንጭ ክርስቶስን
እየተቃወሙ ስለህጉ እንቀናለን ብለው ኢየሱስን ፈጽመው ጠሉት፡፡እነርሱ ከማይወዱትና የገዛ ወገናቸው ሆኖ ካልተቀበሉት (ዮሐ.1፥11)
ከዚህ ሰው ጋር ኒቆዲሞስ ብርቱ ወዳጅነትን መሰረተ፡፡ትንሹ ባለሥልጣን ትልቁ ባለሥልጣን ዘንድ ቀርቦ ያወራው የሥልጣኑን ዘለቄታነትና
የማርዘሚያውን መንገድ ሳይሆን መንፈሳዊውን እውነት ነው፡፡
ባዕለሥልጣናት የእውነተኛ ሰው ረሃብ አለባቸው፡፡የሚያስተዳድሩት ሐሰት
የነገሰባትን አለም ብቻ ሳይሆን የሐሰት ምስክር አቀናባሪዎችን፣ በመማለጃ
ምድሪቱን ያረከሱ ዳኞችን፣ በእውነት ላይ የሚደልሉ ደላሎችን፣ ከዘበኛ እስከጸሐፊቱ ያሉትን ወሬ አመላላለሾችን ፣የሐሰትና የተቀጣጠለ
ዕቅድና ሪፖርት አቅራቢዎችንና አዘጋጆችን … በዙርያቸው እያዩ ቆይተው ለብቻቸው ግን ሲሆኑ እውነቱን እውነት የሚላቸውን ውድ ወዳጅ
አመሻሽ ላይ ይፈልጋሉ፡፡የኒቆዲሞስ ጥማት ይህ ነው፡፡በዙርያው ያሉት ለድኃ የማይራሩ ፣ስስታምና ቀማኞች(ማቴ.23፥250)፣ መልክ
እያዩ እንጂ በቅን በማይፈርዱ (ዮሐ.7፥24)፣ ጻድቃን መሳይ ግን ግብዝነትና አመጸኝነት የሞላባቸው (ማቴ.23፥28) … ናቸው፡፡በእንደነዚህ
ባሉ ሰዎች መካከል መኖር በራሱ ጭንቅ ነው፡፡(2ጴጥ.2፥8)
የቤተ ክርስቲያን
መሪዎች ከባዕለሥልጣናት ጋር ያላቸውን ዝምድና በሚገባ መፈተሽ አለባቸው፡፡ ፓለቲካዊ ሽርክና የትም እንደማያደርስ በቀደመው ዘመን
የታየ እውነት ነው፡፡ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን እውነትና እውነተኞች በማጣት ለሚቅበዘበዙ ባዕለሥልጣናት እርሷ የህይወት አብነት
በመሆን ልትመሰክርላቸው ይገባታል፡፡ፖለቲካውና አስተዳደሩ የሥልጣኑም ዙፋን የሚፈወሰው ቤተ ክርስቲያን የመዳንን እውነት ይዛ ከጎን
የቆመች እንደሆን ብቻ ነው፡፡የወንጌል መፍትሔ ሳይይዙ በፖለቲካው ብቻ አብሮ መቆም ግን ካየነው ጥፋት የባሰ እንጂ ያነሰ አያገኘንም፡፡
ኒቆዲሞስ
በሐሰተኞች መካከል ያለ የህጉ እውነተኛ ጠበቃ ነው፡፡(ዮሐ.7፥51)በአንድ ወቅት ባደረገው ተአምራትና ትምህርቱ ፈሪሳውያን
ጌታን ሊገድሉት አስበው ይዘው እንዲያመጡት ሎሌዎችን ላኩ፤የተላኩት ሎሌዎች ግን በትምህርት ጣዕም ተማርከው፤አድንቀውም መጡ፡፡በዚህ
ጊዜ ተናድደው በመራገምና በመበሳጨት ሲናገሩ ታላቁ ደቀ መዝሙር ኒቆዲሞስ በመካከላቸው “ህጋችን አስቀድሞ አንድን ሰው ሳይሰማና
ምን እንዳደረገ ሳይረዳ ይፈርድበታልን? ብሎ ተናገራቸው፡፡እነርሱ ግን በሹፈትና በስላቅ ቃል ተናገሩት፡፡(ዮሐ.7፥51-52)
ዛሬም
እንዲህ ያሉ እውነተኛ ባዕለሥልጣናት ፤ፍርድንና ህግን በሚያጣምሙ መካከል እውነተኛ የህጉ ጠበቆችና የህሊና ዳኞች አሉ፡፡ቤተ ክርስቲያን
እንዲህ ያሉት እንዲበዙና እንዳይጠፉ ልትጸልይ ፤የመዳኑን ወንጌል በማስተማር ልትተጋላቸው ይገባል፡፡ጥቂት ላልተባሉ ጊዜያት ከፖለቲካ
አመራሮች እውነት እየተነገረ ቤተ ክርስቲያን እውነት ለመናገር ያፈረችበትን ጊዜያት መኖሩን ስናይና ስናስተውል ቤተ ክርስቲያን ወደፊት
ማደግን ቸል ማለቷንና የእውነት ምስክርነትን መዘንጋቷን በሚገባ እናስተውላለን፡፡ህግ የሚያውቁ ፈሪሳውያን ለህጉ ደንቁረው ኒቆዲሞስ
ብቻ መገኘቱ እውነተኞች ከማነስም በላይ ብርቅ መሆናቸው የተገለጠ እውነት ነው፡፡ከእልፍ አገልጋይና አባት ከሚመስሉ ጎበዛዝት መካከል
ጥቂት የታመኑ እውነተኞች ብቻ መኖራቸውም የዛሬ ብቻ ሳይሆን የትላንትም ሐቅ ነው፡፡
ኒቆዲሞስ እውነቱን የተማረውና የተረዳው ፤ደፍሮም የመሰከረው በሌሊቱ ክፍል
ከጌታ ተመላልሶ ተምሮ ነው፡፡ በእርግጥም ሥልጣን ያላቸው እውነተኛ ሰዎች በግልጥ ማገልገልም መገልገልም ህመማቸው ነው፡፡ጲላጦስ
ህመሙ እውነቱን አለማወቁ ሳይሆን እውነቱን ጌታ የሚያውቁና በእውነቱ የሚያምኑ ማጣቱ ነው፡፡(ዮሐ›19፥4)፡፡አቂላና ጵርስቅላ ሥፍራቸውንና
ሥልጣናቸውን ለቀው ከሮሜ የወጡበት ምክንያት ቀላውዴዎስ አይሁድ ክርስቲያኖችን በማሳደዱ ነው፡፡(ሐዋ.18፥1-5)ባዕለሥልጣናት ፍርሐታቸው
የወገን ጠላት ፍርሐት ነው፡፡የማይታይ የወዳጅ ቁስል ከሚታየው የባዕድ ቁስል ፈጽሞ እጅግ ያማል፡፡ጌታ ኢየሱስ የቆሰለው የወዳጁ
የይሁዳን ቁስል ነው፡፡(ዘካ.13፥6)ብዙዎቻችንም እስከዛሬው ያልሻረልን ቁስል የወዳጃችንና የገዛ ወገናችን ያቆሰለን ቁስል ነው፡፡
ኒቆዲሞስ እውነተኛና
የሚበልጠውን ወዳጅ ተዛምዷል፡፡ስለዚህም የቀን የወዳጅ አቁሳዮች በማያገኙበት ሰዓት በሌሊቱ ክፍል ያገኘዋል፡፡አዎ! ኒቆዲሞሳዊ አገልጋይና
አማኝ ያስፈልገናል፡፡የወንጌሉን እውነት ጨክነው በሌሊቱ ክፍል የሚማሩ፣ በክፉዎችና በሐሰተኞች መካከል እውነትን የሚመሰክሩ፣ ሰው
በሌለበት ደግሞ ሰው ሆነው የሚገለጡ(ዮሐ.19፥39) አማኞችና አገልጋዮች ያስፈልጉናል፡፡ቤተ ክርስቲያን ባዕለሥልጣናትን ከስልጣን
ሲወርዱ የምታስጠልል ብቻ ሳትሆን ህዝቡን በእውነትና በቅንነት እንዲያገለግሉ በዙፋን ሳሉ የመዳኑን ወንጌል በግልጥ ልታሰማቸው፤ልትመሰክርላቸውም
ይገባታል፡፡
የጌታ ፍቅር ይብዛላችሁ፡፡አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment