Please read in PDF:- ከጾመም በኋላ ተራበ
ጾማችንን የልማድና መለኮታዊ ኃይል አልባ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ
ከጾምን በኋላ የመብላትና የመጠጣት ፍላጎት እንጂ መንፈሳዊነትን በመራብ መሻትና ፍለጋ በውስጣችን አለመኖሩ ነው፡፡ጌታ ኢየሱስ የይፋ
አገልግሎት ከመጀመሩ በፊት አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾሟል፡፡ጌታ እንደጾመም ተፈትኗል፡፡የተፈተነው በዲያብሎስ ነው፡፡የፈተናው መጀመርያ
ደግሞ በመብልና በመጠጥ ነበር፡፡እኛ ለመብላትና ለመጥገብ ስንጾም ጌታ ኢየሱስ ግን ለመራብና “ለትልቅ መለኮታዊ ዓላማ” ጾመ፡፡
ጌታ ኢየሱስ እንደዘመኑ አባባል ኃጢአት ስለነበረበት የኃጢአት ሥርየት ሊያገኝ
አልጾመም፡፡ ጌታ ኢየሱስ ኃጢአት የማድረግ ፍላጎትም ሆነ ዝንባሌ የሌለው፣በተግባሩ፣በንግግሩና በመንፈሱ ፈጽሞ ኃጢአት ያልፈጸመ
ነው፡፡እርሱ ኃጢአትን አያውቅም፤አላደረገምም፤ተንኮልም በአፉ ያልተገኘበት … (2ቆሮ.5፥21 ፤1ጴጥ.2፥22) ቅዱስና ያለተንኰል
ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለና(ዕብ.7፥26) በእርሱም ኃጢአት የሌለ ነው፡፡ (1ዮሐ.3፥5)
ስለኃጢአት ማንም እርሱን መውቀስ አይቻለውም፡፡(ዮሐ.8፥46)፡፡ ይህ ንጹህና ጻድቅ ጌታ ግን ከጾመ በኋላ ተራበ፡፡መራቡ ደግሞ
ግልጥ ፈተና ይዞ መጣ፡፡
የጌታ ኢየሱስ በዲያብሎስ መፈተን ለአርዓያ የሆነ ወይም የቀረበ አይደለም፤በእውነትም
እርሱ ተፈትኗል፡፡“ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደእኛ የተፈተነ …”(ዕብ.4፥17)፣ “ተፈትኖም መከራን የተቀበለ” (ዕብ.2፥15)
ነው፡፡ ዲያብሎስ በምሳሌነት ሳይሆን በእውነትም ፈትኖታል፡፡ጌታ ኢየሱስ ከሰማያት ወደእኛ የመጣው በጸጋው ቃል ለድሆች ወንጌልን
ሊሰብክ፣የታሰሩትን ሊፈታና በተአምራቱ የተጠቁትን ነጻ በማውጣት የተወደደችውን የጌታ ዓመት ይሰብክ ዘንድ ነው፡፡(ሉቃ.4፥17)
ይህ ደግሞ “መለኮታዊ ዝግጅት” ያስፈልገዋል፡፡ የቃል ኪዳኑን ሰነድ ሙሴ ሊቀበል አርባ ቀንና አርባ ሌሊት፣ኤልያስም እስከእግዚአብሔር
ተራራ ድረስ ለመጓዝ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾምን ጾመዋል፡፡ጌታ ኢየሱስም የአባቱን ፈቃድ ሊፈጽም ጾመ፡፡
ከጾማችን በኋላ ትልቅ ሥራ፤ ትልቅ የመንፈስ ቅዱስ መቀባት ከሌለ ጾሙ ልማድ
ወይም ከረሃብ አድማ ያለፈ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ ሙሴም ኤልያስም ከጾማቸው በኋላ ታላላቅ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡(ዘፀ.34፥28፤1ነገ.19፥8)
ከእግዚአብሔር ቅዱሳን የምናየው ትልቁ እውነት ከዝግጅት በኋላ ትልቅ ድል በሠራዊት ጌታ ጉልበት እንደሚቀዳጁ ነው፡፡መርዶክዮስ፣
አስቴርና በሱሳ ግንብ ሥር የነበሩት አይሁድ ከጾሙ በኋላ ታሪክ ገለበጡ፡፡(አስ.8፥4) የነነዌ ሰዎች ከጾሙ በኋላ ቁጣ በረደላቸው(ዮና.3፥10)
… ብዙ ቅዱሳንና የእግዚአብሔር ህዝቦች ከጾምና በፊቱ ከመማለድ በኋላ የተወደደ መልስን ከጌታ ዘንድ አጊኝተዋል፡፡እኛ በጾም ተርበን
ሳንፈተን በራሳችን እጅ በዶሮና በበሬ ሥጋ፤በዝሙትና በሙዚቃ ኮንሰርት
የኃጢአቱን ፈተና በሰይጣናዊ ንስሐ እንመልሳለን፡፡
ጌታ ኢየሱስ በአርባ ቀኑ ጾም “ልጅ ነውና ኪዳኑን በማሰላሰል መታዘዝን
በመማር” (ዕብ.5፥7)ራሱን ያዘጋጅ ነበር፡፡ የጌታ የእስካሁን አገልግሎቱ የዝምታ አገልግሎት ነበር፡፡ሠላሳ አመት ሙሉ ህዝብን
ስለማገልገሉና ስለማስተማሩ መጽሐፍ ቅዱስ አልገለጠልንም፡፡ከሠላሳ ዓመት በኋላ ግን ወደአደባባይ በመውጣት ሊያገለግል፤ ለጠላትም
ሊገለጥ ነውና ብርቱ ዝግጅት አደረገ፡፡ስለዚህም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በመጾም የአባቱን ሃሳብ ብቻ ሊያገለግል በመጨከን ተዘጋጀ፡፡በመጾምም
ተራበ፡፡
ጌታ ኢየሱስና የእግዚአብሔር ቅዱሳን ከጾሙ በኋላ የእግዚአብሔርን ጽድቅ
ተርበዋል ወይም ፈቃዱን ለመፈጸም ትልቅ የሥራ በር ተከፍቶላቸዋል፡፡ዛሬ ግን ይህ እውነት ሰማይ
ከምድር የሚርቀውን ያህል ከመካከላችን በብዙ እጅግ ርቋል፡፡ከጾም በኋላ ስለሚበሉት ዶሮና ጥሉል ምግቦች እንጂ በጾሙ “ስለተዘጋጀንበት” (እርሱም እንደመታደል ቀድሞ ጾማችን ርዕስ
ያለው ከሆነ!?) ከእግዚአብሔር ጉልበት እንዳገኘንና እንደተቀበልን ሰዎች የምናስብ አይደለንም፡፡ “ጾሙ ተፈታ” የተባለበት ቀን
እንኳ የሚያልፈው በቁንጣንና በስካር ነው፡፡
ልናፍርበትና አንገት ልንደፋበት ከሚገባን ነገሮች አንዱ “የእስልምና እምነት ተከታዮች ጾማቸውን” በሚፈቱበትም ሆነ በማግስቱ “የአስረሽ ምቺው የሙዚቃ ኮንሰርትና ምንትስ ቅብርጥስ” የጾም ፍቺውን ተከትሎ ተዘጋጅቷልና ኑ የሚል ጥሪ በዕድሜዬ አልሰማሁም፡፡ (ከናዝሬት መልካም ነገር ተገኘ!!!) በእኛ ግን “የፋሲካን በዓል ምክንያት በማድረግ የሙዚቃ ኮንሰርትና የኃጢአት አዋጅ” በግልጥ ይታወጃል፡፡ “ጾሙ ተፈቶ” በማግስቱ ያው “ጾሜያለው” ያለው ህዝብ ሲያብድ ጨርቁን ጥሎ በነውር ሲራቆት ማየት የአደባባይ እውነት ነው፡፡ (ከዚህ የበለጠ አመንዝራነትና በእግዚአብሔር ላይ መዘበት ይኖር ይሆንን?!)
… “የእግዚአብሔር ቸርነት ወደንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና
የመቻሉን የትዕግስቱንም ባዕለጠግነት ትንቃለህን?”(ሮሜ.2፥4)፡፡ጌታ ግን የታገሰን ከጾም በኋለ በነውር እንድንያዝ አይደለም፡፡የሚያሳዝነውና
በጣም ልብ የሚሰብረው ከጾም በኋላ “ታላላቅ” ካቴድራሎችና ገዳማት ፣አድባራት ሳይቀሩ የእግዚአብሔርን ቃል ከመናገር ቦዝነው “በጾም
ፍቺ” ሰበብ ጎባኤ ሲያስታጉሉ ማየት እየተለመደ መምጣቱ ነው፡፡ ጾም ከተፈታ በኋላ ቃሉን ከማንበብና ጮኾ ከመናገር ቸል ማለት እንዴት
ያለ ልብ የሚደፍንና ዓይን የሚይዝ አዚም አጊኝቶን ይሆን? “ነጻነት” ምናለ ለኃጢአት ባይውል?
ቤተ ክርስቲያን ቀኖና ሠርታ ጹሙ ብላ ካወጀች፤ ልጆቿም ከጾሙ በኋላ ደግሞ
ለትልቅ መለኮታዊ ሃሳብና ሥራ ማዘጋጀት ሲገባትተዘልላ ተቀምጣ ልጆቿ ለኃጢአት ተፈትተው በኃጢአታቸው እግዚአብሔርን ሲገዳደሩ ዝም
በማለቷ ቁጣንና ፍርድን በራሷ ነው የምታከማቸው፡፡የጌታን ጾም እንጾማለን ምንል ከሆነ ከጾማችን በኋላ መንፈሳዊ ረሃብ ሊሰማን ፤ለበጎና
እግዚአብሔር ለሚወደው ሥራ ልንቀና ፤ልንተጋም ይገባናል፡፡በእውኑ ከመንፈሳዊ ጾም በኋላ አለልክ መብልና አለልክ መጠጥ ፣ ጭፈራና
ዳንኪራ፣ አመንዝራነትና ዘፋኝነት ፣ለኃጢአት የተፈታ መሆንን ከየት ነው የተማርነው? ጾሙን ከጾመው ከኢየሱስ ነውን? … ክብር ይግባውና
እርሱ በሰውም በእግዚአብሔርም ዘንድ ጻድቅና ቅዱስ ነው፡፡ እኛ ግን የተማርነው ከሌላ ነውና በንስሐ መመለስ ይሁንልን፡፡ አዎ!
መንፈሳዊነት ጊዜያዊ ቁጥብነት አይደለም፡፡
“የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደሆነ
ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ
እንጂ ይህን አለም አትምሰሉ፡፡” (ሮሜ.12፥2)
ጌታ ከጾም በኋላ በመንፈስ መራብን ይስጠን፡፡አሜን፡፡
ወንድሜ ይህን ጽሑፍህን ሳነበው ብዙ ጉድለቶች እንዳሉት ተረዳሁ፡፡ አንድ ጌታ የጦም ለእና አብነት ሊሆን እንደሆነ በቀጥታ ባትናገረውም ኃጢአት ስላለበት አይደለም የጦመው በሚለው ቃልህ ተናግረኸዋል፡፡ ታዲያ መፈተኑ እናንተም የእግዚአብሔር ልጆች ስትሆን ከሰይጣን ፈተና አለባችሁ በሰይጣን የምትፈተኑት በእነዚህ በእነዚህ ነው ሊል እንጂ በእውን እንዴት ፍጡር ፈጣሪውን ሊፈትን ይቻለዋልን? እንዴት ብላችሁ ጌታን እንደምትረዱት የምትገርሙ ናችሁ፡፡ ለማንኛውም ይህ የቅድስት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አይደለም፡፡
ReplyDelete