Monday 3 March 2014

ለሰዎች እንደጦመኛ አትታዩ (ማቴ.6÷16)




       ጾም ለእግዚአብሔር መንፈሳዊ አምልኮአችንን ከምንገልጥባቸው መንገዶች አንዱ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም በዓላማ ከምናደርጋቸው ዝግጅቶችም አንዱ የጾም ዝግጅት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ጾምን በማያሻማ መልኩ መጾም እንደሚገባን አስረግጦ ይነግረናል፡፡ጌታ ይህን ትምህርት በሚያስተምርበት ወራት በአይሁድ ዘንድ ጾም የታወቀና የተረዳ ነገር ነበር፡፡ ምንም እንኳ መንፈሳዊ መልኩና ለዛው ፈጽሞ በግብዝነት የጠወለገ ቢሆንም፡፡
     አይሁድና አህዛብ ራሳቸውን በእግዚአብሔር ፊት ለማዋረድ የቀናውን መንገድ ለመለመን (ዕዝ.8÷21፤መዝ.69÷10)፣ ስለህዝብና ስለዓለም ሁሉ ስለራስም በደልና ኃጢአት በማዘንና በመጸጸት ለመናዘዝ (ነህ.9÷1-2)፣ ንስሐ ለመግባትና እግዚአብሔር ሊያመጣ ያለውን ቁጣ እንዲተወውና በምህረትና በይቅርታ ህዝቡን ይቅር እንዲል (ኢዩ.2÷12፤ዮና.3÷5-10)፣ የእግዚአብሔርን ሃሳብና ፈቃድ ለማወቅ ፣መገለጥንና ጥበብን ለማግኘትም (ዳን.9÷3) … ለተለያዩ ብዙ ምክንያቶች አይሁድ ጾመዋል፡፡

     ቤተ ክርስቲያንም በክርስቶስ ኢየሱስ የተከፈለላትን ትልቁን ውለታና ማዳን በማሰብና ለሁልጊዜም ባለመዘንጋት ለአዲስ ሥራ ፀጋን ለመሻትና ለእግዚአብሔር መለየታችንን እንደገና ለማረጋገጥ (ማቴ.4÷2)፣ ጌታ እግዚአብሔርን በመቅረብ እርሱን ለመፈለግና ተቃዋሚ የመናፍስት ኀይሎችን መታገል ይቻል ዘንድ በጸሎት ለመጽናት(ሉቃ.18÷3፤ሐዋ.9÷10)፣ ሰዎችን ከክፋት እስራት ለማዳንና ለመፍታት እንዲሁም ለእውሮች ማየትን የተጠቁትንም ነጻ በማውጣት ለመስበክ(ማቴ.17÷14፤ሉቃ.4÷18)፣ መንፈስ ቅዱስ እንዲወርድና ክርስቶስ ለህዝቡ ወደምድር ዳግም እንዲመጣ መንገድ ለመክፈት (ማቴ.9÷18) እና ለሌሎችም ዓቢይና ንዑስ ምክንያቶች ቤተ ክርስቲያን ልትጾም ከሁሉ በፊት ይገባታል፡፡
    ቤተ ክርስቲያን በክፉ ከተያዘው ከዚህ አለም ፊት እንድታመልጥ ክርስቶስ በደሙ አስጊጦአታል፡፡ ይህን በደም ያጌጠ የጽድቅ ልብስ እንዳያድፍና እንዳይረክስ የመጠበቅ ኃላፊነት አለባት፡፡ እንዳትረክስ ራስዋን የምትጠብቅበት አንዱ ጋሻ በመንፈስ ቅዱስ የሆነ ጾም ነው፡፡ቤተ ክርስቲያን ጾሟ ሊገለጥና ሊታይ የሚገባው  በእግዚአብሔር ፊት ብቻ እንጂ በሰው ፊት ሰው እንዲያያት ሊሆን አይገባውም፡፡
    የጾማችን ደም ግባቱ በእግዚአብሔር ፊት ሲታይ እንጂ በሰው ፊት ሲመሰገን አይደለም፡፡ስለዚህም አይሁድ ሲጾሙ በራሳቸው አመድ ነስንሰው ማቅ ለብሰው ተዋርደው በሐዘን መሄዳቸውን በሰው ፊት ለመመስገን አድርገውታልና ከሰው ስለተቀበሉት ዋጋቸው ተነቅፈውበታል፡፡ይልቁን አይሁድ በደስታ ጊዜ እንደሚያደርጉት ፊትን በመታጠብ፣ ራስን በመቀባት፣ የጌታ ሞቱ ህይወታችንን ፣ ውርደቱ ክብራችንን ፣ጉስቁልናው የጸጋ ልብሳችንን …  ስለመለሰልን ያለግብዝነት በሙሉ ደስታ፤ ፊታችን እየበራ፤ ደስም እያለን ልንጾም ይገባናል፡፡
     ለሰዎች ፊታችን በርቶ ፈጽሞ ጿሚ ሳንመስል በጌታ ፊት በፍርሐትና በመገዛት ጾማችንን ብንጾም ይሻለናል፡፡እንደዛሬው ዘመን አገልግሎት የጾማችንን ዋጋ ከሰው መቀበል አይገባንም፡፡ ዛሬ አገልጋዮች ስላገለገሉበት አገልግሎታቸው ደመወዛቸውን ( አበል፣ ደመወዝ፣ መኪና፣ የወርቅና የብር መስቀል፣ ቤት፣ የቅንጦት ሞባይሎችና ቀሚሶች፣ያማሩ ምግቦች … ) በዚህ ምድር ሳሉ ተቀብለውበታል፡፡የሚያሳዝነው ስላገለገሉበት አገልግሎታቸው “ይህን ሁሉ” ተቀብለው በሰማይም ሽልማት እንዳላቸው ካሰቡ ነው!!! ምናለ ሙሉ ዋጋችን በሰማይ እንጂ በምድር እንደሌለ ባስተዋልን!?
     የጾም ወራት ሲመጣ አብዛኛው ሰው የልማዱን ሥርዓት ሳያጓድል ይፈጽመዋል፡፡ወጭቶች በአጃክስና በፈላ ውኃ ተቀቅለው ይታጠባሉ፣ጥሉላት ምግብና መጠጦች የደረሱበት ላለመድረስ ብርቱ ጥንቃቄዎች ይደረጋሉ፡፡ግና ሁሉም ነገር በጊዜ ገደብ ተጠብቆ ነው፡፡ለመርከስ ቀጠሮዎች ከጾም በኋላ ተይዘዋል፡፡ ጾመን ለሚበልጥ ትልቅ የቅድስና ሥራና አገልግሎት የማንነቃው ጾማችን ጊዜያዊ ቁጥብነትና በሰው ዘንድ ብቻ የሚታይ ስለሆነብን ነው፡፡እንጂማ ከአርባ የቀንና የሌሊት ጾም በኋላ ዳግመኛ በኃጢአት የተፈታን ባልሆንን ነበር፡፡በእግዚአብሔር ፊት እውነተኛውን ጾም ከጾሙ በኋላ ብዙ ቅዱሳን ታላላቅ መንፈሳዊ ሥራዎችን ሰርተዋል እንጂ ከቶውንም ለመብልና መጠጥ ራሳቸውን አላዘጋጁም፡፡
     ጾማችንን እግዚአብሔር እንደሚያየው ያለነቀፋ የምንጾም ከሆነ ከመብልና መጠጥ ብቻ ሳይሆን ከሚያረክሰው ክፉ መሻትና ከዓለማዊነት ህይወት ልንርቅ ይገባናል፡፡ “ … በኃጢአት መኖርንና አለማዊ ምኞትን ክደን በአሁኑ ዘመናችን ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ ፣በእውነተኛ መንፈሳዊ ህይወት ለመኖር” (ቲቶ.2÷11-12) ዛሬላይ ጾማችን መጨከን ካልቻለ እውነት ለመናገር ጾማችን ገና ... ሌላ እውነተኛ ጾም፣ ሌላ እውነተኛ ጸሎት፣ ሌላ እውነተኛ ንስሐ ያስፈልገዋል፡፡ዋጋቸውን በሰው ፊት እንደተቀበሉት ግብዞች ጸሐፍት ፈሪሳውያን ሳይሆን ሙሉ ዋጋቸውን በሰማያት ባለው አባታችን ፊት እንደተቀበሉ ቅዱሳን  ተግተን ከጸሎት ጋር ጾማችንን በመንፈስ ቅዱስ ጉልበት እንፁም፡፡
የጌታ ቀኙ ትርዳን ፡፡አሜን፡፡


3 comments:

  1. amen geta yirdan.

    ReplyDelete
  2. Amen lehulachnm Egzabher Amlak yirdan

    ReplyDelete
  3. ወንድሜ በጣም በጣም ነው የገረመኝ ሳነበው... እውነተኛው ከሆነው ከእግዚአብሔር ቃል በእጅጉ ርቀን በልማድ ምን ያህል እየሄድን እንዳለን በግልጽ አስቀምጠኸዋልና እግዚአብሔር ፀጋውን አብዝቶ ይጨምርልህ... ለሁላችንም እርሱ የሁሉ ባለቤት የሆነው ጌታ ማስተዋልን ይስጠኝ፡፡ መመለስ ይሁንልን፡፡

    ReplyDelete