Sunday 16 March 2014

ግብረ ሰዶማዊነት - የዘመናችን መጻጉዕ(ክፍል -1)


Please Read in PDF    
  
አንድ ማታ ስልኬ ምሽት አራት ሰዓት ገደማ ጮኸች፡፡ለማንሳት እያቅማማሁ ስልኬን አነሳሁት፡፡ “Hello” የሚለውን ቃል ከአንደበቴ ከማውጣቴ ተጨንቆ የሚያለቅስ የወንድ ልጅ የሲቃ ድምጽ ወደጆሮዬ አቃጨለ፡፡“ወንድ ልጅ ሳይሸነፍ እንዲህ እንደማይሆን” ውስጤ ሊደመደም አልዘገየም፡፡ከብዙ የማጽናናት ቃል በኋላ “ማታ ማታ ድቁና እናጠና ሳለን አንድ ወንድም በተለያየ ጊዜ ሲነካካኝ በወንድማዊ ፍቅር አስቤ ዝም አልኩት፡፡በሌላ ቀን ግን በጣም አጥንተን ደክሞኝ ስለተኛሁ ፈጸመብኝ፡፡ከዚያ ቀን በኋላ ሲደጋገምብኝ ከእርሱ ጋር ብቻ ሳይሆን እኔም ከሌላ ሰው ጋር ለመፈጸም ተነሳሳሁ፡፡እናም አንድ ቀን ሌላ ወንድሜን እየነካከሁት ሳለ ያልጠበቅሁት ቁጣ አገኘኝ፡፡ “ባልመለስ ለቤተሰቤም እንደሚናገር አስጠነቀቀኝ፡፡እናም ቀኑን ሙሉ ሳለቅስ ነው የዋልኩት፡፡ቢጨንቀኝ አንተ ጋ ደወልኩኝ፡፡እባክህን ምከረኝ፡፡ምን ላድርግ? … ”
      ብዙ የሚያለቅሱ አይኖች ፣መታበስ የሚፈልጉ የእንባ ዘለላዎችን አሰብሁ፡፡እናም ውስጤን አንዳች ነገር ሲንጠኝ ታወቀኝ፡፡ለአፍታ በመካከላችን ዝምታ ሆነ፡፡ይበልጥ እንዳይጨንቀው ፈርቼ “የእግዚአብሔርን ምህረትና ይቅርታ፤የሰውንም ልጅ ኃጢአተኝነት” አወራለት ገባሁ፡፡ዛሬ በእግዚአብሔር ጉልበት ይህ ወንድም ተመልሶ በቤቱ አለ፡፡
     ብዙ ጊዜ በተለያየ መንገድ ከሚደርሱኝ አስተያየቶች ትልቁን ስፍራ የሚይዙት “ጽሑፎችህ በጥናታዊ ይዘት ተደግፈው ስለማይቀርቡ የመረጃ እጥረት ይታይባቸዋል፤ ከወሬም ያላለፉ ናቸው” የሚለው ነው፡፡ የሚያሳዝነው ነገር ኃጢአትን በተመለከተ ምን አይነት ጥናት ቢካሄድ እንደሚወዱ አልገባኝም፡፡እውነት እንናገር ከተባለ ቅዱስ ጳውሎስ የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን “በአጭር ቃል በእናንተ መካከል ዝሙት እንዳለ ይወራል የዚያም ዓይነት ዝሙት በአሕዛብስ እንኳ የማይገኝ ነው፥ የአባቱን ሚስት ያገባ ሰው ይኖራልና።”(1ቆሮ.5÷1) በማለት ሲናገር ከሰማው ነገር ተነስቶ እንጂ ምንም ስለኃጢአት በሰራው ጥናታዊ ጽሁፍ አይደለም፡፡ምነው ጥናታዊ ጽሁፍን ለኃጢአት ከማሰብ ለሌላ ነገር ብናውለውስ?

    ግብረ ሰዶማዊነት የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን ትልቁ የቤት ሥራ ነው፡፡ አርነታችንን ካልተጠነቀቅንለትና በጌታ ጉልበት ካልጠበቅነው ለኃጢአት ምክንያትን የሚሰጥ ነው፡፡ “ትልልቅ የምድራችን ነውሮች መነሻቸው የእግዚአብሔርን ፍቅር ከቀመሱ በኋላ ወደኋላ በሚመለሱ አማኞች” ነው፡፡ እውነትን ረግጦ ከኃጢአት ጋር ተባብሮ ወደኋላ ማፈግፈግና ወደኋላ መመለስ ልብን ያደነድናል፡፡ግብረ ሰዶማዊነት የእግዚአብሔርን ጽድቅ በመቃወም የሚሰራ ኃጢአት ብቻ ሳይሆን ቅዱሱን የሰውን ሰብዓዊ ተፈጥሮ የሚያቃውስ ታላቅ ኃጢአት ነው፡፡
     “… የፊንጢጣ ካንሰርና የፊንጢጣ ከልክ በላይ መስፋት ፣የአንጀት ጨብጥና ቂጥኝ … በስፋትና በብዛት የሚያጠቁት ግብረሰዶማውያንን ብቻ እንደሆነ”(አብዱልጃፋር ሸሪፍ የተባሉ በአፍሪካ ቲቪ የስነ ልቦና ምክር አቅራቢ) አስረግጠው ይናገራሉ፡፡አንዱ የቤት ሥራ ሳያልቅ ሌላው በአናት በአናት የሚጨመረውና ውልና መቋጠሪያው ይህን ያህል የጠፋብን እኛም የኃጢአቱ ተካፋዮችና ተባባሪዎች ስለሆንን ነው፡፡
    ብዙ ጊዜ የምመላለስባት የክፍለ ሀገሯ የአቅራቢያዬ ከተማ የታወቁ ጥቂት ሴት ግብረ ሰዶማውያን በግልጥ ይንቀሳቀሱባታል፡፡በቡድን ይመገባሉ፣በቡድን ይወጣሉ፣በቡድን ይገባሉ፣ተለምዶ ዕውቅና እንዳገኘ ነገር ያለተጽዕኖ ይራመዳሉ፡፡በህሊናዬ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ እንደሴተኛ አዳሪዎቹ “ተኳኩለው” የሚወጡ “ሴትና ወንድ ግብረ ሰዶማውያኑ” ከፊቴ ድቅን አሉ፡፡
“የአመጻችን ብዛት ከገደቡ ሰፋ
ወንዱ ወንዳገረድ ሴቱም ሴት አገባ፡፡”
(አቤቱ የኃጢአትን ህይወትና ጉልበት በልጅህ ደም ገድለኸውና ሰብረኸው ሳለ እኛ በአመጻችን አለምልመነዋልና አቤቱ ልባችንን መልስልን፤ በበጎነትህም ወዳንተም እንመለሳለን!!!!)
    ከመናፍቅነት ያላነሰው አመንዝራነታችን ዛሬ “እንደፍቅር መግለጫ” በወጣቱና በወጣትነታቸው ላይ ሰላሳና አርባ ዓመት በደረቡ (የደራሲ በዕውቀቱ ስዩም አገላለጥ ናት) አረጋዊ መሳይ አመንዝራ ጎልማሶች ዘንድ መታየቱ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡የጀመርነው የአመንዝራነት “የቤት ሥራ” ጠባሳው ሳይሽር፤ ገና በበሽታው የደቀቁትና የተኙት ሳያገግሙ፤ የግብረ ሰዶማውያኑ ቁጥሮች ከመቶዎች ቤት ወደብዙ ሺዎች አሻቅቧል፡፡
      የወንጀል ህጋችን በአንቀጽ 629ና ተከታዮቹ አንቀጾች ግብረ ሰዶማዊነት ወንጀልና ህገወጥ ድርጊት እንደሆነ ቢያሰፍረውም አፈጻጸም ላይ ግን የመደገፍ ያህል ትኩረት ሲሰጠው አይስተዋልም፡፡በአንድ ወቅት “ሮዝ” የተባለው መጽሔት ስለልቅ የወሲብ ንግድና ዕርቃን ጭፈራ ቤቶች ሲዘግብ ምናልባት አንድ ምዕራባዊት የገጠር ቀበሌን እንጂ የየኢትዮጲያዋን አዲስ አበባ ማንም እንደማይጠብቅ እገምታለሁ፡፡በሁለተኛ ዙር ዘገባው ግን ብሶ እንጂ ተሽሎ እንዳልተገኘ በትዝብት አስነብቦናል፡፡እንግዲህ ይኸኔ ነው ቤተ ክርስቲያን፣ “ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮጲያዊ መልኩን…” የሚለው ሽለላችን፣ መንግስትና ህግ፣አኩሪውና አይነኬው ባህላችን … ወዴት ናቸው? የሚል ለብላቢና የማያሳርፍ ጥያቄ የምናነሳው፡፡በዚህ ሳያበቃ በአንድ ሌላ ወቅት ግብረ ሰዶማውያን አለም አቀፍ ስብሰባ ሊያደርጉ እንደተሰማ የኃይማኖት አባቶች ለመቃወም ቢወጡ አንድ የመንግስት ባለስልጣን “ፖለቲካውና በጊዜው የነበረው ስብሰባ እንዳይበላሽ ” በሚል ስብሰባውን ለመቃወም የተሰበሰቡት የኃይማኖት አባቶች መበተናቸውና ግብረ ሰዶማውያኑም ቦታ ቀይረው ስብሰባ ከማድረግ አልፈው አባላቶቻቸውን በሚገባ መልምለውና አሰማርተው መሄዳቸው የማይካድ ሀቅ ነው፡፡(ነገ ደግሞ የእኛው ዜጎች ይህን ስብሰባ በግልጽ ላለማድረጋቸው ምን ይሆን ዋስትናው?)
ጌታ በምህረቱ ጥላ ከነውረኝነት ይጠብቀን፡፡አሜን፡፡
ይቀጥላል…

1 comment:

  1. ያሳዝናል!!!! በጣም በጣም

    ReplyDelete