Monday, 10 March 2014

ምኩራብ



ቅዱስ ያሬድ የጌታን ጾም ሳምንታት በሠየመበት ስያሜው ሦስተኛውን ሳምንት ምኩራብ ብሎ ሰይሞታል፡፡ጌታ በምኩራብ ማስተማሩን፤መስበኩንና መፈወሱን ለማስታወስ፡፡ምኩራብ የእስራኤል ልጆች ወደባቢሎን በንጉስ ናቡከደነጾር በተማረኩ ጊዜ ጎበዛዝት ተግዘው፤ኢየሩሳሌም ባድማ ሆና መቅደሷም ፈርሶ ተፈታ በነበረችበት ወቅት በባዕድ ምድር እግዚአብሔርን ለማምለክ የሰሩት የአምልኮ ሥፍራ ነው፡፡የሄዱባት ባቢሎን ጣኦትና ቤተ ጣኦት እንጂ እግዚአብሔርና ቤተ መቅደስ አልነበሩባትምና አይሁድ የእግዚአብሔርን ፊት ለመፈለግ ፣ቃሉን ለማጥናትና ለጸሎት እንዲያመቻቸው በየሥፍራው ምኩራብን መሥራት ጀመሩ፡፡
   የእስራኤል ልጆች ከባቢሎን ምርኮ ተመልሰው ወደደሀገራቸው በተመለሱ ጊዜም ከመቅደሱ ጎን ለጎን ምኩራብን ሠሩ፡፡ምኩራብ በጌታ ዘመን ለአይሁድ ዋነኛ የአምልኮ ሥፍራ በመሆኑ ቅዱሳት መጻህፍትን በውስጡ በማከማቸት ፣ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በማንበብና በመተርጎም እንዲሁም እግዚአብሔርን ማምለክ የሚያዘወትሩበት ሥፍራ ሆነ፡፡
    በአንድ ሥፍራ ላይ ከሰባት እስከአስር ብዛት ያላቸው አባወራዎች ካሉ ምኩራብን እንዲሰሩ ይፈቀድላቸዋል፡፡ዋና አላማው በአንድ ሥፍራ ያሉ ወገኖች በቅርብ በመገናኘት ቅዱሳት መጻህፍትን እንዲያጠኑና እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ ማድረግ ነው፡፡ የምኩራቡ አገልጋይም ዋና ሥራው ልጆችን ማስተማር፣ የቅዱሳት መጻህፍትን ጥቅልሎች ማቅረብ ፣ሌሎችንም ሥራዎችን መስራት ነው፡፡(ሉቃ.4÷20)
    አገልግሎቱ ስለማቋረጥና ብዙ ምኩራቦችም ስለነበሩ(ሐዋ.9÷2፤13÷3)በየቀኑና በየሰንበቱ ህዝቡ ሁሉ በአቅራቢያው ወዳሉት ምኩራቦች ይሰበሰብ ነበር፡፡(ሐዋ.13÷14፤17÷17)፡፡ የሚሰበሰቡት ሁልጊዜም ከላይ  ለሠፈረው ዓላማ ብቻ ነው፡፡ ምኩራብ ከመቅደስ ያነሰ መስዋዕት የማይቀርብበት የአምልኮ ሥፍራ ነው፡፡ጥቂት አባወራዎችና መንገደኞችም ጎራ እያሉ ቃሉን በማጥናት እግዚአብሔርን የመፍራት ጥበብ ይማሩበታል፡፡ 

     ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ጊዜ ወደእነዚህ ምኩራቦች በተደጋጋሚ በመገኘት አስተምሯል፤ የመንግስትንም ወንጌል ሰብኳል፤ በህዝብም ሁሉ ያለውን ደዌና ህማም ፈውሷል፡፡ (ማቴ.4÷23፤ ማር.1÷39)፡፡ በአንድ ምኩራብ የሚሰባሰቡት ሰዎች ጥቂት ሰዎች ስለሆኑ ለማስተማር ቀላልና የእያንዳንዱን አማኝ ሐሳብና ራዕይ ለማወቅም አያደክምም፡፡ጌታ በአንድ ምኩራብ በተደጋጋሚና ባለመሰልቸት ከመቅደስ ይልቅ እየተገኘ ማስተማሩን ወንጌል ይመሰክርልናል፡፡“እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገባ፥ ሊያነብም ተነሣ።”(ሉቃ.4÷16)፡፡ሐዋርያትም እንደጌታ ልማድ እንዲሁ በመቅደስ እየተገኙ በተደጋጋሚ አስተምረዋል፡፡“በስልማናም በነበሩ ጊዜ በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ”(ሐዋ.13÷5)፡፡“ በአንፊጶልና በአጶሎንያም ካለፉ በኋላ ወደ ተሰሎንቄ መጡ፥ በዚያም የአይሁድ ምኵራብ ነበረ።ጳውሎስም እንደ ልማዱ ወደ እነርሱ ገባ፥ ሦስት ሰንበትም ያህል ከእነርሱ ጋር ከመጻሕፍት እየጠቀሰ ይነጋገር ነበር …”(ሐዋ.17÷1-2)፡፡
    ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን መምሰል ካለባት አገልግሎቷ እርሱ ያገለገለው እንጂ ሌላ አገልግሎት ሊኖራት አይገባም፡፡ምንም እንኳ ምኩራቡን የሰሩት አይሁድ ቢሆኑም ጌታ ግን በምኩራባቸው ተገኝቶ አስተምሯል፡፡እንዳለመታደል ከጎረቤት ክፉ ነገር እንጂ መልካም ነገር መውሰድ አይሆንልንም፡፡ከጥቂት አመታት በፊት የወንጌላውያን ህብረት አማኞች ቁጥር እጅግ በጣም ጥቂት ነበር፡፡ዛሬ ግን ያ ቁጥር ታሪክ ሆኖ ብዙ ሚሊዮኖችን አፍርተዋል፡፡ ያፈሩት በተዓምራዊ መንገድ አይደለም፡፡በጥቂት አባወራዎች መካከል መገኘት በመቻላቸውና ለዚህም በመድከማቸው ነው፡፡
        በአገልግሎት ዓለም የአማኙን ልብና ፈቃድ ሃሳብና ምኞት አጊኝቶ እንደማገልገል የሚያረካ ነገር የለም፡፡የምኩራብ ዋና ዓላማ ይህ ነው፡፡አባወራዎቹን በአድራሻቸው ማግኘት፡፡እነርሱ በተሰበሰቡበት በመንደራቸው ምኩራብ በዚያ አገልጋዩ አብሯቸው ሊገኝ ይሄዳል፡፡የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን የመቅደስ እንጂ የምኩራብ አገልግሎት የላትም፡፡ብዙ ፍሬና ብዙ አማኝ የነበረው ግን በመቅደሱ ሳይሆን በምኩራቡ ነበር፡፡ጌታም ብዙ ነማስተማር የደከመው ከመቅደሱ ይልቅ በምኩራቡ ነበር፡፡የምኩራብ አገልግሎት ለህዝቡ የቀረበ ነው፡፡ይህ ደግሞ ትልቁ የወንጌል ሥራ ነው፡፡
     የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን የምኩራብ አገልግሎት ያስፈልጋታል፡፡በቤተ መቅደሱ አንድ ሺህና አምስት መቶ ሰው ሰብስቦ በቅዳሴ ማሳተፍና በጉባኤ ማስተማሩ ባይከፋም ፍሬው ሲመዘን ግን ገለባ ይበዛዋል፡፡ብዙ ሰው ከኃጢአት ርቆ ከክርስቶስ ሥጋና ደም ከመሳተፍ ይልቅ የራሱ ምክንያት ይበልጥበታል፡፡እንዲህ ያሉ ሰዎች ቁጥራቸው ደግሞ ሚሊየንን ያልፋል፡፡እኒህን ነው አማኝ ብለን  ዕድሜ ልክ ተሸክመን የኖርነው፤አሁንም ያለነው፡፡እንዲህ ያሉ ሰዎችን ግን ከመቅደሱ ይልቅ በምኩራብ ማግኘት ይገባናል፡፡በአድራሻቸው ሄደን የተቸገሩበትንና የታሰሩበትን እስራት ልንፈታላቸው ይገባናል፡፡አስራት በኩራት ለመሰብሰብ የሰው በር እያንኳኩ ከማሰልቸት አማኙ ወዶ እንዲሰጥ ቤቱን ምኩራብ አድርገን ከሚስቱ ከዘመዶቹና ከልጆቹ ጋር ልናስተምረው ይገባናል፡፡በመቅደሱ አውደ ምህረት ላይ ብቻ ከመጮህ ወደምኩራብ ዝቅ ብለን ህዝቡን በያለበት አድራሻው ፈልገን እናገልግለው፡፡
      አንዳንዴ በአካል፤ብዙ ጊዜ በቲቪ መስኮት “ታላላቆቹ መሪዎቻችን” የሥልጣን ዙፋናቸውን ጥለው በህዝቡ መካከል “የተሰራውን ልማት” ለማየት ወደገጠር ሲወርዱ አያለሁ፡፡ያ የገጠር ህዝብ ትልቅ መሪ ሊያይህ መጣ ሲባል በልቡ የሚሰማውን ደስታ በቃል ለመግለጥ ይቸግራል፡፡አለማውያኑ የዚህ አለም መሪዎች ወደታች ወርደው የህዝቡን ሥራ በማየት ካመሰገኑና ስህተቱን ከነቀሱ ቤተ ክርስቲያንን የሚመሩቱ “ታላላቆቹ ጳጳሳትና ሊቃነ ጳጳሳት” መች ይሆን ከመቅደስና ከካቴድራል ወደጥቂት አባወራዎች ምኩራብ ዝቅ ብለው ባያስተምሩ ከህዝቡ ጋር አብረው የሚታዩትና የህዝቡን ብሶት በማድመጥ እናባውን የሚያብሱት?
  አዎ! የህይወት አገልጋይና አማኝ ለማፍራት የምትሻ ቤተ ክርስቲያን መቅደስ ብቻ ሳይሆን ምኩራብም ያሻታል፡፡ማደግ በየጥቂቱ ነው፡፡ ስለዚህም ለጤናማ መንፈሳዊ እድገት ከምኩራብ ወደመቅደስ ማደግን እንደግ፡፡ጊዜያችንን በድንጋይ ብቻ “መቅደስን” በመስራት አናባክነው፡፡የዳኑ ነፍሳት ያሉባቸውን ጥቃቅን ምኩራቦችም ይልቅ ይሁኑልን፤ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ነውና የምትታነጸው፡፡ ጌታ በማስተዋሉ ማስተዋላችንን ያድስልን፡፡አሜን፡፡

1 comment:

  1. "ጌታ በማስተዋሉ ማስተዋላችንን ያድስልን፡፡አሜን፡፡"..... አ ሜ ን

    ReplyDelete