Monday 24 March 2014

ጸሎት - አሜን ሆይ በቶሎ ናልን! (ራዕ 22፣ 20)



    በቀደመው ብሉይ ኪዳን  ልጄ ወዳጄን እልክላችኋለሁ፤ መጥቶም ሰዎችን ሁሉ ከኃጢአታቸው ሁሉ በፀጋው ያድናቸዋል ብለህ ኪዳን ሠጥተህ እንደኪዳንህ ቃልህ ያልታበለ አብ አባት ሆይ ስግደት፤ አምልኮ ፤ሽብሸባ፤ ዝማሬ ፤ እልልታና ውዳሴ ከፍጥረት ሁሉ ተጠቅልሎ ለገነነው ድንቅ ስምህ ይሁን፡፡
    አቤቱ ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ አንተ የፍጥረት ሁሉ ናፍቆት፤ “ያልተሠራ ልብስ ፤ ያልተፈተለ ቀሚስ ፤ ወደአባቱ ለመድረስ ጎዳና ፤ ወደወለደው ለመግባት የሚሆን በር እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው”  (ቅዳሴ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ) የተባለልህ መድኃኒታችንና ቤዛችን ሆይ እንዳንተ የሆነልን፤ ዋጋ ላልነበረን ዋጋችን ሆነኸን፤በሰማይና በምድር አግነህ ተወዳጆች ላደረገን፤ ወንድምና አባታችን ሆይ አንተን የምናመሰግንበት ብዕርና ቃል ገና አልተፈጠረምና በአርምሞና  በተመስጦ ምስጋናችንን በመንፈስ በበገና ቅኔ እንደረድርልሐለን፡፡
    መዳናችንን ያስታወቅኸን፤ ልጅነታችንን ለመንፈሳችን የመሰከርክልን፤ የክርስቶስን የመስቀል ሥራ በልባችን ፅላት ላይ የቀረፅክልንና እናየውም ዘንድ የረዳኸን፤ በሐዘናችንንና በስብራታችን ሁሉ ያፅናናኸን ወጌሻ ሆነህ የዳስስከን ማህየዊ መንፈስ ቅዱስ ሆይ ለፍጥረት አለቆችና ለምድር መላዕክት የሰጠነውን ስግደትና ምስጋና ውዳሴና ቅዳሴ ክብርና አምልኮ ነጥቀን ጰራቅሊጦስ ለምትሆን ላንተ፤ ለሥላሴ መንግስት ባለመታከት እናቀርባለን፡፡ አሜን፡፡
    አቤቱ ሆይ ! ጎረቤትነት በቂም መርዝ ተመርዟል፤ባልንጀርነት በሐሜትና በክህደት ተፈቷል፤  ወንድማማችነት በዕላቂ ገንዘብና በውርስ እዳሪ ደም ተቃብቷል፤ ቅስናው ልማድ፤ ድቁናው ወግ፤ ጵጵስናው ሹመት (ሺህ-ሞት) እንጂ ለመንጋህ መራራትን አላስተማረንምና፤ ሐሰት እንጂ እውነት ከክብሯ ተራቁታ ዕርቃንዋን ቀርታለችና…….. አቤቱ ጨርሰን ሳንጠፋ ናልን!

     ጌታ ሆይ ክፋት እንደቡቃያ በመካከላችን አብባ እንደፍሬ ጎምርታ ላንተ መታመንን ነውር በኃጢአት መደሰትን ቁምነገር አድርገን እነሆ ምድሪቱ ከእኛ የተነሣ እጅጉን ተጎሳቁላለችና የማታን እንጀራ አዳዩ ጌታ ሆይ ምሬታችን ሳይብስ ናልን!
    ጌታዬና መድኃኒቴ ሆይ ሀገሬ ኢትዮጵያን ዘረኝነት አዙሮ ሊደፉት አንድ ሐሙስ ቀርቷታል፤ ጉበኝነት አይነ አውጥቶ ድኃ ተገፍቶባታል፤ ባዕለጠጋ በገንዘቡ በመቅደስህ ናዝዞበታል፤ እንግዳና ነውር ነገር በአህዛብ እንኳ ያልተሠማ ግብረ ሰይማዊነት በመካከላችን በቅሏልና፤ አቤቱ ይህ የክፋት ቡቃያ በፍሬው እንዳናየው አሜናችን ሆይ በቶሎ ናልን፡፡ የኃጢአት ዕድሜ እንዳይለመልም ፤ ከቡቃያው አልፎ እንዳያፈራ፤ በምድሪቱ የክፋት መከር እንዳይታጨድ፤ ኃጢአተኞች በፃድቅህ ደም እንዳይታጠቡ፤  የጨለመው በብርሃንህ እንዲፈካ፤ ድንበሩ ሩቅ የሚመስለው የኃጢአት አዝመራ በአጭር እንዲከተት፤ የማያባራ የሚመስለው የጦርነት፤ የእልቂት  የመሬት መናወጥ፤ የጎጠኝነቱና የዘረኝነቱ ክፍፍል፤ የጉበኝነቱና የአመንዝራነቱ፤ የመከራውና የሰቆቃው፤ የረሃብና የጥሙ፤ የመታረዝና  የእንባው …. ሁሉ ፍፃሜና ድንበሩ ዳርቻና መከተቻው አንተ ነህና ማራናታችን ኢየሱስ ፈጥነህ ናልን! ጌታ ሆይ አፍሪካ ምጥ እንደያዛት ሴት በብዙ ተጨንቃለች፡፡ እንኳን መፍትሔው በውል ባልተለዩ ብዙ ችግርና ጥልፍልፍ መሰናክሎች ተተብትባለችና አቤቱ ሳይመሽ  ተገለጥላት፡፡
    ጌታ ሆይ እንማልድሐለን ለአፍሪካ ብርሐንዋን አቅርብላት፡፡ ህዝቧን ከእርስ በርስ ጦርነት፤ ልጆቿን ከረሃብና ከእርዛት፤ ወጣቶቿን ከነውርና ከዝሙት ጠብቅላት፡፡ ሽማግሌዎቿ በክብር እንዲያርፉ ሽበታቸውን አክብር፡፡  አቤቱ ከተሞቿ በቦንብና በጥይት እሩምታ፤ አፍንጫን ከሚሰነፍጥ ከክፉ ሽታ ብቻ ሳይሆን ህሊናንና መንፈስን ከሚያረክስ ከኃጢአትና ከበደል እንዲያርፉ ፈጥነህ ናልን! አቤቱ ሆይ ለዓለሙ ሁሉ በቶሎ ናለት፡፡ለምናምንህ ለእኛ ለልጆችህም ናልን፡፡ አቤቱ ከአለሙ ርኩሰት ሳንጨመር ከክፋቱም ሳንተባበር ወዳንተ  መምጣቱንም ስጠን ፡፡ አሜናችን ሆይ ሁሉን እንደፍቃድህ ስለስማኸን ተባረክልን፡፡ አለምን በተዛመድክበት አማኑኤል በተባለው ህያው ስምህ፡፡ አሜን፡፡

1-   

No comments:

Post a Comment