Please Read in PDF
አማኝ አለን ብለን እንደምንመካበት ትምክህታችን ሳይሆን ከአፍሪካ ምድር መሪ በመጥላትና ለመሪ ባለመጸለይ እንዲሁም ሰው በቁም የማይከበርባትና ሲሞት የሚገንባት ሀገር ኢትዮጲያ ከግምባር ቀደሞቹ አንዷናት ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ ሁልጊዜ ብዙ ሰው ሀገርን ስለመውደድ ሲጠየቅ ወገንና መሪን መውደድ ትልቁን ሥፍራ እንደሚይዝ ጭራሹን ያስተዋለው አይመስልም፡፡ ከሁሉ ይልቅ ቤተ ክርስቲያን የሞቱ መሪዎችን በክብር ስማቸውን አንስታ እየጠራች ስትጸልይላቸው በህይወት ያሉትን ግን ከመጥራት ተዘልላ መቀመጧ እጅግ መንፈስን ያውካል፡፡
ትውልድን የመቅረጽና ለመልካም ነገር የማንቃት ትልቁ ኃላፊነት የወደቀው
የእግዚአብሔር መንግስት በሆነችው ቤተ ክርስቲያን ላይ ነው፡፡ቤተ ክርስቲያን በቅድስና ከቆመች ዓለምን ያለንግግር መውቀስ ትችላለች፤በነውር
ግን ከተመላለሰች የተቀደደና የተነወረ ልብሷን አይተው አለማውያንና አህዛብ ይጠቋቆሙባታል፤ይሰድቧታልም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ትልቁ
የቅድስና ልብስና ራሷን የምትጠብቅበት የዝናርና የትጥቅ መሳርያዋ ደግሞ ቅዱሱ ወንጌል ነው፡፡
እጅግ የሚያሳዝነው
ነገር ቤተ ክርስቲያን ወንጌል ለመስበክ ያልደከመችበትን መሪና ህዝብን ለመቅበር “ትልቅ ሥነ ሥርዓትን” በማሳየት መድከሟ ነው፡፡
ዛሬ ከማለዳ ጀምሮ ሲካሄድ የነበረውን የኦሮሚያ ክልል ፕረዘዳንት የቀብር ሥነ ሥርዓት በአይኖቼ ትክ ብዬ አየሁት፡፡ ከዚያም የቀደሙት
ጠቅላይ ሚኒስትርን የቀብር ሥነ ሥርዓት በህሊናዬ አሰናሰልኩ፡፡በኋላ ላይ ግን ወደውስጤ የመጣው፦
“ቤተ ክርስቲያን ለምን ነው መሪ አድምቃ መቅበር
እንጂ በህይወት እያለ የማትማልድለትና ስሙን ጠርታ የማትጸልይለት???!!! ቤተ ክርስቲያን ለመሪዎች ወንጌል ለመስበክ እንደነዚህ
ያሉ ታላላቅ ዕድሎችንስ አጊኝታ ለምን ነው እንኳን ወንጌሉን ተንትና ለማስተማር ይቅርና ንባቡን እንኳ በአግባቡ እንዲሰማ ተደርጎ
ለህዝቡና ለሀገሪቱ መሪዎች የማታነበው? ስንት ነገር በቃል “ሸምድደን” የምናጠና ወንጌል አጥርቶ ማንበብ ምነው አፋችን ተሳሰረ?
ቀብር ላይ ብቻ የምንሰማው ስመ ክርስትና መቼ ነው በቅዳሴውና በጸሎቱም ላይ “መሪያችን እገሌን አስብልን ” ብለን መጥራት የሚሆንልን?
... ”
እያልኩ በመንፈስ ተቃጠልኩ፡፡
ሰው እኮ ጸሎትን የሚሰማውና አብሮ ለመጸለይ በመንፈስ የሚነቃቃው ወንጌሉን
በአግባቡ መስማት ሲቻለው ነው፡፡ጸሎት ቃሉን በእምነት ከመስማትና በመንፈስ ቅዱስ ከተቃኘ ልብ የሚወጣ እንጂ ልማድ ስለሆነ ብቻ
የሚፈጸም ሥራ አይደለም፡፡ ቃሉን ያልሰማ ወይም እንዲሰማ ዕድል ያልተሰጠው ሰው ጸሎትን ይሳተፋል ብሎ ማሰብ ለዘመናት ያልተማርንበት
መንገዳችን ነው፡፡በህይወት እያለች ቃሉን ለማስተማር ያልደከምንላትን ነፍስ በቀብር ሽኝት ደማቅ ሥነ ሥርዓት ለመፈጸም መሮጡ ግብዝነት
ነው፡፡ሟችን የሚጠቅመው የደመቀው የአራትና የአምስት ሰዓት የቀብር ሥነ ሥርዓት ሳይሆን በህይወት እያለ ወደልቡ እንዲመለስ የነገርነው
የአራትና የአምስት ደቂቃ የመዳን ወንጌል እንደሆነ ማን በነገረን?!
ምነው ለቀብር ድምቀት ከመሮጥ ወንጌሉ ለፍጥረት እንዲዳረስ ብንቻኮል?
እውነት ሟች መርጦ ያልኖረውን እኛ እንደኖረው አድርገን ቀብሩ ላይ ስናወራው ህሊናችን አይታዘበን ይሆን? ማረፍ ማለትስ ቃሉን ሰምታ
በህይወት ለኖረች ብጽዕትና ህያው ነፍስ ወይስ ቤተ ክርስቲያን ለቀበረቻቸው ሁሉ ነው? በአንድ ወቅት በዝሙት ጽሁፎቹና ክርስቶስን
በመካድ የሚታወቀውን አንድ የዚህ ዓለም ደራሲ ቤተ ክርስቲያን “በክብር ትልቅ ሥራ እንደሰራ” አድርጋ ስትቀብር ላየ ምነው እንዲህ
መቅበር የሚቀረው መቼ ነው? ያሰኛል፡፡
መቼ ነው ከቀብር ድምቀት የመዳን ወንጌል ስብከት የሚቀድመው? መቼ ነው
ቤተ ክርስቲያን ሀገርን መውደድ ማለት ጋራ ሸንተረሩን ማፍቀርና ድንግል መሬት እያሉ መፎከር ሳይሆን መሪ በህይወት እያለ ስሙን
ጠርቶ መጸለይና ማሰብ ማለት እንደሆነ እርሷ አሳይታ ሌሎችም እንዲያደርጉ የህይወት አብነት የምትሆነው? ትልቁ የታሪክ ስህተት ከታሪክ
አለመማር ነውና ቤተ ክርስቲያን በህይወት ለሌሉ ሙታን ከምታደርገው ክብርና ድምቀት ይልቅ ቃሉን ባለመስማት በኃጢአት ሞተው ላሉ
ሙታን እጅግ በመራራት ወንጌሉን ብትሰብክላቸው መልካም ነው፡፡ ሞት እንደሁ አደላዳይ ነው፤ሁሉን ያስተካክላል፡፡ ህይወት ግን በእግዚአብሔር እጅ ናት እንጂ
እኛ በግብዝነት የምንቸራት አይደለችምና ቃሉን ለመስበክ መትጋቱ ይሻለናል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ልጆቿ “ወደማያልፈው ዓለም” ሲሄዱ ብቻ ሳይሆን በዚህኛውም
ዓለም ስብሰባ መምከርና ንስሐ እንዲገቡ፤ ፊታቸውንም ወደእግዚአብሔር ዘወር እንዲያደርጉ ወንጌሉን አሰምታ ልትነግራቸው ይገባታል፡፡
አልያ ግን ያሸበረቀ የቀብር ሽኝት ሰውን እንጂ የህይወትን ጌታ ደስ አያሰኝምና ቤተ ክርስቲያን ለሚበልጠውና ክብር ለሚገባው መንፈሳዊ
ሥራ ልታደላ ይገባታል፡፡አዎ! ሲሞት ሳይሆን በህይወት እያለ መሪና ወገንን መውደድ ይሁንልን እንጂ “አድምቆ መቅበር” ብቻ አይሁንልን፡፡
ጌታ ወገኖቻችንንና ቤተ ሰቦቻቸውን ያጽናናልን፤ለእኛም ማስተዋሉን ያድለን፡፡አሜን፡፡
wendime beente kidisat tselot lay "Tseliyu beente mefqere amlak" Yemilwe sile meri new. Yedirow Tsihuf degimo "Tseliyu bente Nigusine ..." bilo sim Yitera neber. Yemeriwochu amelekaket (Yezemenu rieeyote alem )Eyete qeyere simeta gin bewel sim Eyeteqeyere hede Enji Ahunim Betekrstiyanachin Sile agerina meriwocwa metsley Alaqomechime. Egzio kuneneke habo lenigus yil Yeneberewins ataqewim??
ReplyDeleteግሩም ማስተዋል፡፡
ReplyDelete