በመጽሐፍ ቅዱስ ካልተጻፉ ነገር ግን እንደተጻፉ ተደርገው በየመድረኩ ከሚጠቀሱልን ጥቅሶች መካከል አንዱና ዋናው ጥቅስ ቅዱስ ጳውሎስ ለቅዱስ ጢሞቴዎስ የጻፈው “መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋ ጅቶልኛል፥ …” (2ጢሞ.4÷7) የሚለው ቃል ነው፡፡
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በህይወት ዘመናቸው በዙርያቸው ካሉትና ከሩቁ ብዙ ስድብ ፣ነቀፌታንና ትችትን የጠገቡ አባት ናቸው፡፡እንዳለመታደል እነዚያ ይጠሏቸውና በድብቅ በስድብ ይዘምቱባቸው የነበሩት ሰዎች ቅዱስ ፓትርያርኩ በቁም ሳሉ ያልተናገሩትን ሲሞቱ ቁጣቸውን፣ ተግሳጻቸውን፣ ምክራቸውን ወጣ ወጣ ሲያደርጉ አይተናል፡፡ (በእርግጥ እሳቸውም ሰው ናቸውና ይደክማሉ፤ደክመውም ይዝላሉ፡፡ ስህተት አይቶ ከመርገም፦ እንዲመለሱ ፣እንዲታነጹ ያኔውኑ ነበር በግልጥ መግለጡ … ሳይመክሩና መንገድ ሳያሳዩ ቁጣ እንዴት ያለ ስንፍና ነው?) ወደሐሳቤ ልመለስ፡፡
እሳቸው ባረፉ ሳምንት በ“ታላቁ” የአራት ኪሎው የሥላሴ ካቴድራል ላይ የተለጠፈው “ትልቅ ስቲከር” እንዲህ ይላል፦
“መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫዬን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን
ጠብቄአለሁ፤ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥” (2ጢሞ.4÷7)፡፡
ምናልባት እሳቸው ናቸው የጻፉት ወይም የፊደል ግድፈት ነው እንዳንል በየትኛውም ቤተ ክርስቲያን ጀርባ ዘወር ብላችሁ የተጻፉ የመቃብር ላይ የዚህን ክፍል ጽህፈቶች ብትመለከቱ ተመሳሳዩን ለማየት አትቸገሩም፡፡ እንደውም አንዳንዶቹ “ሃይማኖትን ጠብቄያለሁ” የሚለውን ቃል ጭምር “ሃይማኖቴን ጠብቄያለሁ” ሲሉም ይደመጣሉ፡፡ (የእኔ ብቻ ለማለት ይሆን ክርስትናውን?)
ይህን ተመልክተን በመጨረሻ የምንደርስበት ድምዳሜ ከታላቁ እስከታናሹ ፣ከሰባኪው እስከተሰባኪው … ቃሉን በህይወት ከመተርጎም ባሻገር በንባቡ እንኳ ያለማስተዋል ከባድ ችግር እንዳለብን ነው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ልጁ ቅዱስ ጢሞቴዎስን በብዙ ምስክር ፊት የሰማውን ቃል እንዲመሰክርና መከራን በመቀበል ከሙታን የተነሳውን፣ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በማሰብ በትጋት እንዲያገለግል ሊመክረው ከተጠቀመበት ምሳሌዎች አንዱ ሩጫ ነው፡፡(1ጢሞ.2÷2-8)፡፡
በእሽቅድምድሙ ሥፍራ ሁላችንም የማይጠፋውን አክሊል እናገኝ ዘንድ ልንሮጥ እንደሚገባን ተነግሮናል፡፡ (1ቆሮ.9÷24)፡፡የሩጫ ውድድር እንግዳ ባልሆነባት ቆሮንቶስ ተወዳዳሪው ሮጦ ሲያሸንፍ የሚሸለመው ከጥቂት ቀናት በኋላ የሚረግፈውንና የሚጠፋውን የአበባ ጉንጉን ነበር፡፡ቅዱስ ጳውሎስ በሚያውቁት ሩጫ የመንፈሳዊውን ዓለም ሩጫ ይነግራቸዋል፡፡እነዚያ ለሚጠፋው ሲሮጡ እናንተ ግን ለማይጠፋው አክሊል ሩጡ፡፡
ሯጭ የሚሮጠው ሩጫ ቀድሞ የተወሰነና የታወቀ ነው፡፡የማያውቀው ነገር በምን ያህል ሰዓትና ደቂቃ እንደሚገባ ነው፡፡መንፈሳዊው ሯጭም የሚሮጠው ሩጫ በታላቁ ጌታ በእግዚአብሔር ቀድሞ የተወሰነና የታወቀ፤የተረዳም ነው፡፡መንፈሳዊውን ሩጫ የምንሮጠው በራሳችን መም(መስመር) ውስጥ አይደለም፤ ይልቁን ሩጫችንን በትንሳኤ ደምድሞ በክብር ባረገው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ መም ውስጥ እንጂ፡፡
ጌታ ኢየሱስ የእኛን መተላለፍ የቆሰለ፣ህመማችንን የተሸከመ፣ሞታችንን የሞተ፣ደዌያችንን የተቀበለ፣ ስለበደላችንም የደቀቀና እኛን ተገብቶ መከራችንን የወሰደ፤ነጻ አውጥቶም የዋጀን ነው፡፡የተጠራነውም እርሱን በስም ብቻ ሳይሆን በህይወትም እንመስለው ዘንድ ነው፡፡
“ክርስቶስም በሥጋ ስለ እኛ መከራን ስለተቀበለ፥ ከእንግዲህ ወዲህ በሥጋ ልትኖሩ በቀረላችሁ ዘመን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሰው ምኞት እንዳትኖሩ፥እናንተ ደግሞ ያን አሳብ እንደ ዕቃ ጦር አድርጋችሁ ያዙት፥ በሥጋ መከራን የተቀበለ ኃጢአትን ትቶአልና።”(1ጴጥ.4÷1)፡፡የተጠራነው እርሱ ያየልንንና ያሰበልንን ሕይወት በእምነት በማስተዋል ሩጫውን እንድንሮጥ ነው፡፡
የዕብራውያን መልዕክት ጸሐፊም “…የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤… ”(ዕብ.12÷2) ይለናል፡፡ሩጫው በምን ያህል ሰዐት እንደሚያልቅ አይታወቅምና ክርስትና ሳንታክት የምንሮጠው ረዥም ሩጫ ነው፡፡ሩጫውን ጀምሮ የፈጸመው ራስ የሆነው አልፋና ዖሜጋ ክርስቶስ ነው፡፡ክርስትናው የተጀመረው በእርሱ ነው ፈጻሚውም እርሱ ነው፤እርሱ ከሁሉ በፊት ሮጦ ያሸነፈ ታላቁ ምስክራችን ነው፡፡ይህን ያላስተዋለ አገልጋይ ሩጫውን ትቶ የግሉን ሩጫ ሩጫዬን ብሎ ሲሰብክ ውሎ ነፍስ ባይማርክ ይደንቅ ይሆን? ሲጀመር ክርስቶስ የሌለበት ሩጫ ምኑ ሊማርክ?
ስለዚህም በመታገስ መስቀላችንን ተሸክመን ልንሮጠው የሚገባን ሩጫ የእርሱን እንጂ የራሳችን አይደለም፡፡ብዙዎች ሩጫቸውን ሲጨርሱ “ሩጫዬን ጨርሻለሁ” ቢሉ ትክክል ናቸው፡፡የመሸታ ቤትና የአዝማሪ ቤት፣የጥንቆላና የምዋርት ቤት፣የስድብና የአሽሙር … ሩጫ በእርግጥም “ሩጫዬን” እንጂ “ሩጫውን” አያስብልምና፡፡አዎ! እኛ የምንጀምረው ሩጫ የለም፤ጌታ በሄደባትና በረገጠባት የእግሮቹን ፋና ተከትለን እየረገጥን እንሮጣለን እንጂ፡፡ከአምላክነት በቀር የእርሱ የሆነው ሁሉ የእኛ የሚሆነውና የክብሩ ተካፋዮች የምንሆነው እርሱ የሮጠውን ሩጫውን በእርሱ ጉልበት ታግሰን ስንሮጥ ነው፡፡ሯጭ መድረሻ መሙን ትክ ብሎ እያየ እንዲሮጥ እኛም የእምነታችንን ራስና ፈጻሚ የሆነውን ጌታ ኢየሱስን እንመልከትና ሩጫውን በትዕግስት እንሩጥ፡፡የዝሙት፣ የዘፈን፣ የሐሜት፣ የክርክር፣ የአድመኝነት፣ የማንሾካሾክ፣… ሩጫችንን ሳይሆን የጌታን ሩጫውን ታግሰን እንሩጥ፡፡ያኔ ነው፦
“መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥
ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥”
የሚለው ቃል ደምቆ የሚታየን፡፡
ጌታ ሩጫውን እንድንሮጥ በማስተዋሉ ይርዳን፡፡አሜን፡፡
thanks i have recently reached this blog .....kale hiwot yasemaln
ReplyDeleteI love this blog God bless you.
ReplyDeleteI LOVE THIS BLOG GOD BLESS YOU
ReplyDeletethank you sharing the word of God and may God bless your ministry.
ReplyDeleteቃለ ሕይወት ያሰማልን
ReplyDelete