Tuesday 26 November 2013

ሳይሰሙ መጋል

     ከሸክላ ምጣድ ጠባያት አንዱ ሳይሰማ አለመጋሉ ነው፤ መስማት (መሞቅ) የክርስቲያን ልዩ ጠባዩ ነው፡፡ በክርስትና መቀዝቀዝ አይቻልም፤ ዳግመኛ ወደኃጢአት ቆፈን ወደባርነት እንድንገባ አልተፈቀደልንም፤ (ገላ.5፥1)፡፡ ለማንም የማይመች ለብታም አይሆንልንም፤ ወይ በአግባቡ መስማት (መሞቅ) ወይም ደግሞ ቀዝቅዞ በገዛ እጅ ራስን ከእግዚአብሔር መለየት፡፡ ከብርሐንና ከጨለማ አንዱን መምረጥ እንጂ ሌላ ሦስተኛ ምርጫ አልነበረም፤ አይኖርምም፡፡
      በአንድ ወቅት እንዲህ ሆነ ይባላል፥ ሦስት እንደሰሙ የሚግሉ ሰዎች ነበሩ፡፡ ስለምናኔ ሲነገር መናኝ፣ ስለቅዱስ ጋብቻ ሲነገር ማግባት፣ ስለሰባኪ ሲነገራቸው ሰባኪመሆን የሚያምራቸው በተጣዱበት ሁሉ የሚሰሙ ነበሩ፤ በመጨረሻም መናኝ መሆን አማራቸውና፥ እንደተነገራቸው ሽንብራ ይዘው ወደገዳም ገቡ፡፡ ከብዙ ጾምና ጸሎት ጋር በቀን በሥላሴ ምሳሌነት ሦስት ፍሬ ሽንብራ ሊበሉ ወሰኑ፤ ነገር ግን አልቻሉም፡፡ በሚቀጥለው ቀን በስድስቱ ቃላተ ወንጌል ምሳሌ አሉና፥ ስድስት ስድስት ፍሬ ቢበሉም አልቻሉም፤ በሚቀጥለው ቀን በአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት፣ ቀጥሎም በሐያ አራቱ ካህናተ ሰማይ እንዲህ እያሉ ቢሄዱም ስላልተቻላቸው፥ በመጨረሻ በእልፍ አዕላፋት መላዕክት ብለው የያዙትን ጨርሰው ወደቤታቸው ተመለሱ ይባላል፡፡

     ሳይሰሙ መጋልና እንደሰሙ መጋል፥ የሰነፍ ክርስቲያን ልዩ ጠባያት ናቸው፡፡ እንደሰሙ የሚግሉ ሰዎች ቃሉን እንደሰሙ ወዲያው የሚወስኑ፣ መሃላ የሚደረድሩ ወዲያው በቅለው፤ ፈጥነውም የሚከስሙ ናቸው፡፡ እንደሰሙ የሚግሉክርስቲያኖችወዲያው አገልጋይ እስከመሆን ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን አንዳች ሳያፈሩ ሙሉ አድራሻቸውን በሚብስ ክፋት ይቀይሩታል፡፡
    የብዙ ሰንበት ትምህርት ቤትና ስብከተ ወንጌል አባላትን የመዘገቡ መዝገቦችን ብታዩ እንደሰሙ የጋሉት፣ እንደተነገራቸው ወዲያው መጥተው የተመዘገቡት፣ ሳያምኑ በሰው እምነት የሚጸድቁ የሚመስላቸው ብዙ አባላቶቻቸው ወደኋላ ማፈግፈጋቸውን  ያለትዝብት ያወራሉ፡፡ እንደሰሙ መጋል የዛሬ ዘመን ትልቁ የክርስትና ፈተና ነው፡፡ እልፍ አብያተ ክርስቲያናት በአንዲት ጥቅስ ዶግማቸውን የመሰረቱ አማኞች የሚበዙባቸው ናቸው፤ እንደተጣዱ የሰሙ ክርስቲያኖች በጠባያቸው የሚበዙቱ ግልፍተኞች ከመሆናቸው በላይ ከእነርሱ የሚበልጥ እምነትና እግዚአብሔርን የሚፈራ እውቀት ያለው ሰው ቢገጥማቸው እንኳ ጆሯቸው የማይሰማ፣ ዓይናቸው የማያይ ነው፡፡ በተጣዱበት ሁሉ ይሰማሉና ላዩት እንጂ ለተጠሩበት ጥሪና  የተሰጣቸውን መክሊት አያስተውሉትም፡፡ ልበ ሰፊ ቤርያዊነት በጣም ይጎድለናል፤ (ሐዋ.17፥10)
     የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን ብዙ አማኞቿ እንዲህ ናቸው፡፡ በተጣዱበት ሁሉ ይሰማሉ፤ ምንም እንደማይሳናቸው ያስባሉ፡፡ ሌላውና እጅግ የሚብሰው በርዕሳችን የጠቀስነው ሳይሰሙ መጋል ነው፡፡ ነገርን ትክ ብለው ሳያዩ መናገር፣ የሚመሰክሩለትን በትክክል ሳያውቁ መጮህ፣ ለእውነት ሳይታዘዙ የእውነት ጠበቃ እንደሆኑ ራስን መሾም፣ ጥቂት ሰምተው ሐቲት መስራት የሚናፍቁቁጥራቸው ለሰሚ ይከብዳል፡፡
    ስለቅዱስ አጵሎስ እንዲህ ተጽፏል፦
     “በወገኑም የእስክንድርያ ሰው የሆነ ነገር አዋቂ የነበረ አጵሎስ የሚሉት አንድ አይሁዳዊ ሰው ወደ ኤፌሶን ወረደ፤ እርሱም በመጻሕፍት እውቀት የበረታ ነበረ።እርሱ የጌታን መንገድ የተማረ ነበረ፥ የዮሐንስንም ጥምቀት ብቻ አውቆ በመንፈስ ሲቃጠል ስለ ኢየሱስ ይናገርና በትክክል ያስተምር ነበር፤” (ሐዋ.18፥26-27)፡፡ በተለይ በእኛ ቤተ ክርስቲያን በአሁን ዘመን ብዙዎች ስለኢየሱስ የሚናገሩት እኛም እንናገራለን ለማለት ሳይሰሙ (በመንፈስ ሳይቃጠሉ) ወዲያው በጋሏት እውቀት ነው፡፡ ስለኢየሱስ ለመናገርና በትክክል ለመመስከር በመንፈስ የምንቃጠልና በትክክል የጌታን መንገድ የምናውቅ መሆን መቻል አለብን፡፡
      ሳይሰሙ የሚግሉ ሰዎች ነውእና ተብሏልየዘለለ እውቀት የላቸውም፡፡ በእምነት ከምንቀበለው ውጪ ያለውን የጌታን ሁለንተና እንድንመረምር፣ እንድንረዳ፣ እንድናውቅ ገላጩ መንፈስ ቅዱስ እስከአለም ፍጻሜ ከእኛ ጋር ነው፡፡ነውየተባለው ለምን ተብሏልየተባለውም ሊፈከርና ሊታተት ይገባዋል፡፡ በመንፈስ ለመቃጠልና ስለኢየሱስ በትክክል ለመመስከር ከጌታ የሆነውን በትክክል መስማትና መረዳት ይገባናል፡፡      
      የዛሬዋን ቤተ ክርስቲያን ጉዞ ከድጥ ወደማጥ የሚያደርገው አንዱ አስፈሪ ነገር ሳይሰሙ የጋሉና ከሽምደዳ ውጪ በመጻህፍት እውቀት ያልበረቱ ብዙ ተከታዮችን አቅፋ መያዟ ነው፡፡ ቅንጣቱን የቤተ ክርስቲያን መሰረተ እምነት የማያውቁ፣ የቤተ ክርስቲያንን ታሪካዊ ዳራ ያላጠኑ፣ የክርስቶስን ሕይወት በሕይወታቸው ሳይሰብኩ በቃላቸው የሚደሰኩሩ፣ ወንጌሉን ሳይሰሙ ወንጌሉን የሚጠቅሱ፣ ክርስቶስን በትክክል ሳያውቁ ሌላውን አታውቁም የሚሉ፣ ዛፍና ሰው ሳይለዩ በእሳት የሚማግዱ፣በአገባቡ ሳይሰሙ የሊቅ ካባ የደረቡ፣ በአገባቡ ሳያድጉ ጎብጠው ያረጁ፣ በአገባቡ ሳይሞቁ ፈልተው የሚገነፍሉና የሚፍለቀለቁየዛሬዎቹ ብዙ አማኞች እጅጉን አስፈሪ ናቸው፡፡
     ቤተ ክርስቲያን ድንበሯን ልታስከብር ይገባታል፡፡ሳይሰሙ የሚሟገቱትን ፣ሳትናገር በአንደበቷ የሚጮኹትን፣ ሳትጽፍ በስሟ የሚያትሙትን፣ሳታውጅ ቀርነ መለከት የሚነፉትንሳይሰሙ የሚግሉትን በልካችሁ ሁኑ ልትል ይገባል፡፡ አልያ ግን ከታሪክ ያልተማርን ባለታሪክ መሆናችን አይቀሬ ነው፡፡ ሳንሞቅ አንጋል፤ “እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው”(ሮሜ.1017)ቃሉን ሰምተን እንመን፡፡ ከምስክርነታችን በፊት የምንመሰክረውን እንመነው፡፡
       በተጣድንበት ከመሞቅ፤ ሳይሞቁም ከመጋል ጌታ ይጠብቀን፡፡ አሜን፡፡ 


3 comments: