Sunday, 17 November 2013

" 'ከወይን እሾህ' ይለቀማልን?"(ማቴ.7÷16)


ከወራት በፊት  አንድ አሁንም በህይወት ያሉ ሊቀ ጳጳስ ኤርትራ ካለው "የተቃዋሚ ጦር ቀጠና" በመገኘት ኢትዮጲያን እንዲወጉ መድፍና ታንኩን መትረየስና ቦንቡን "ባርከው"መመለሳቸውን ሰምተን ነበር፡፡(ይታያችሁ አሁንም ሊቀጳጳስ ሆነው አሉ!? "የሚረግሟችሁን መርቁ" የሚለውን ቃሉን ያስተምሩ ይሆን?!!)፡፡ሰሞኑን ደግሞ ሳውዲ አረቢያ ከዜጎቿ ውጪ ባሉ የውጪ ነዋሪዎቿ ላይ በወሰደችው እርምጃ ከሐገር ቤት ከአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት አንገት የሚያስደፋ ከአንድ ክርስቲያን ማህበረሰብ የማይጠበቅ ጸሎት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ካባ አልብሰው  ሲሉና "ምላሹም እንደተገኘ" ሲናገሩ ሰምቼ ተክኜ በመንፈሴ ተበሳጭቻለሁ፡፡(ይታያችሁ ሶማሊያ፣ሳውዲ አረቢያ፣ፊሊፒንስ፣…. ከሰሞኑ በከባድ የጎርፍ አደጋ ተመተዋል፡፡ሳውዲ አረቢያ በእኛ ጸሎት እንዲህ ከሆነች ሌሎቹን "መአተኛው" እግዚአብሔር በማን ጸሎት ይሆን በጎርፍ የመታው?!)
    በሐገራችን አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ "በማዕረጉ ታች ያለ ዲያቆን" የአንዳንድ ቀሳውስትና ጳጳሳትን የጨለማን ሥራ ገልጦ ከወቀሰና ከሥራው ጋር ላለመተባበር ወስኖ አቋሙን በግልጥ ካሳወቀ(የሚበዙ “Business ተኮር" አገልጋዮችን አያካትትም) እስከመወገዝ ያደርሰዋል፡፡ውግዘት ፍራቻም ብዙዎች "ጆሮ ጭው የሚያደርግ ነውርና ኃጢአት" በመካከላችን እየተሰራ እያዩ ገለል ብለው አልፈዋል፡፡እኔም ውግዘትን ሳልፈራ ቀርቼ አይደለም ግና ስለክርስቶስ ኢየሱስ ምናልባት የተናቅሁ ሆኜ ከተገኘሁ "የይበቃናል እንመለስ" ጥሪዬን በደሙና በመንፈስ ቅዱስ ጉልበት ለመጮህና ጥቂቷን መክሊቴን መቅበር ስለሌለብኝ ነው፡፡በተረፈ የማንም ቅጥረኛና ተላላኪም አይደለሁም፡፡ከምንም በላይ ቤተ ክርስቲያን በቅድስና ያለእድፈትና ፊት መጨማደድ ክርስቶስን አጊጣ ማየት የዘወትር ናፍቆቴ ነው፡፡

     የሰው ልጆችን በኃጢአታቸው ሊቀጣና ሊቀስፍ ሳይሆን ሊያድንና ሊቤዥ የመጣው ፍቅር የሆነው አማኑኤል ጌታ በተራራው የአንቀጸ ብጹአን ትምህርቱ አንድና ውብ የሠላም መንገድን መሠረተልን፡፡ኦሪት በኮሬብ ተራራ ከተሰጠችበት ቀን አንስቶ እስከጌታ መምጣት ድረስ በኃጢአታቸው ብዙዎችን ገድላለች፡፡ ህጉ ደካማውን ሰው እንጂ ኃጢአትን ግን መግደል አልተቻለውም፡፡
       ጌታ ግን ህጉን ፈጽሞ(አድርጎ) ብቁአን(የበቃን) ካደረገን በኋላ በእርሱ ጽድቅና ቅድስና መፈጸም የሚቻለንን አዲስ የህይወት ህግ፣ አዲስ የወንጌልና የርህራሄን ትዕዛዝ ሰጠን፡፡ ዳቦ ለለመንን ድንጋይ፣ዓሣ ለለመነን እባብ እንዳንሰጥ፣ የምንወደው እንዲደረግልን ሳይሆን ለሌሎች ቀድመን እንድናደርግ፣ ክፉውን በክፉ እንዳንቃወም፣ ለሚለምነን ሁሉ እንድንሰጥ፣ጠላቶቻችንን እንድንወድ፣የሚረግሙንን እንድንመርቅ፣ ለሚጠሉን መልካም እንድናደርግ፣ስለሚያሳድዱን እንድንጸልይ፣የሚወዱንን ብንወድ ብልጫ እንደሌለን ፣ወንድሞቻችንን ብቻ እጅ ብንነሳ ከአህዛብና ከቀራጮች እንደማንሻል በግልጥ መድኃኒታችን በፍቅር አስተምሮናል፡፡
      በእርግጥም እርሱ የመጣው በመንገድ ሰው ለማያሳልፉ እብዶች(ማቴ.8÷28)፣ጋኔን ላደረባቸው ዲዳዎች(ማቴ.9÷33)፣ለእውሮች፣ለአንካሶች፣ለለምጻሞች፣ለደንቆሮች፣ለሙታን፣ወንጌል ለሚሰሙ ድሆች(ማቴ.11÷4-7)ለግፈኞች(ማቴ.11÷12) … ነው፡፡አንዱ ጌታ ለሁሉ ጥላ የሆነ የህይወት ዛፍ ነው፡፡ አንዱ ኢየሱስ ሁሉን ያጠበገ የህይወት እንጀራ ነው፡፡አንዱ ክርስቶስ ለእኛ ጠላቶችም የሚስፈልግ እውነተኛ አንድ ወዳጅ ነው፡፡
      የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ወይን በማለት እስራኤል ዘሥጋን ጠርቷታል፡፡(ኢሳ.5÷1፤ኤር.2÷21)፡፡ በስሙ የምናምን የጌታ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እኛም የወይን ተክል ቅርንጫፎች ተብለናል፡፡ (ዮሐ.15÷5)፡፡ከወይኑ ተክል ማንኛውም ቅርንጫፍ ቢለይ ፍሬ ማፍራት አይችልም፡፡በክርስቶስ ኢየሱስም የማይኖርና በህይወትነቱ የማይደገፍ እንዲሁ በህይወት አይኖርም፤ተቆርጦም ይጣላል፡፡
      ከተክሉ የተጣበቁ ግን አብዝተው ያፈሩ ዘንድ ይገረዛሉ፡፡በክርስቶስ ኢየሱስ ያመኑቱም በወይኑ አትክልተኛ በአብ ይገረዛሉ፡፡ይህም ማለት " … ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ይለብሱ … "(ኤፌ.4÷24) ዘንድ አብ ማንኛውንም አስተጓጓይ ነገር ከህይወታቸው ያርቀዋል(ይገርዘዋል) ማለት ነው፡፡በዚህም ቅርንጫፉ እንደተክሉ ያማረ፣የተወደደና ድንቅ ጣዕም ያለው ይሆናል፡፡ሁላችንም እንዲህ እንጣፍጥና ወደተክሉ እናድግ ዘንድ ነው የተጠራነው፡፡
   የክርስትና ልዩ ጠባዩና ባህርይው ይህ ነው፡፡አንድ ጊዜ ከድቅድቅ ጨለማ ወደሚደነቅ ብርሐን ከተጠራን በኋላ እርፍ ጨብጠናልና ወደኋላ መመለስ አይቻልም፡፡እንደሚያፈራው ወይን እንጂ ወይን ያፈራሉ ስንባል እሾህን የምናፈራ  ከሆንን ሰማያዊውን ፍርድ ከመዝገቡ እንዲወጣ እያስቸኮልን ነው ማለት ነው፡፡
    እኛ በስሙ ያመንን ክርስቲኖች ነን፡፡ሰዎች በእኛ ስህተት እናዳይደበቁና ከንስሐ እናዳይዘገዩ ለተደረገብን ክፋት መልሱ ክፋት ሳይሆን በጎነት ነው ሊሆን የሚገባው፡፡ሰው ራሱን ማየት የሚችለው ላደረገብን ክፋት መልካም ስንመልስለት ነው፡፡ከአንገት ማህተም ይልቅ ሌሎችን ወደክርስቶስ የሚስበው ምልክታችን ለእርግማኑ መመረቅ ስንችል፣ለአሳዳጁ መጸለይ ስንችልነው፡፡የወርቅና የብር መስቀል አንግተን የተራበን "እግዚአብሔር ይስጥህ" ብሎ ማለፋችን ክርስትናችንን አጠንዝቶብናል፡፡
     አዎ! ጳጳስ ጦር ሜዳ ተገኝቶ "በመስቀል" ታንክ ሲባርክ ማየት ያሳፍራል፡፡አፍሪካ የምትሻው ዳቦና የወንጌል ጉባኤ የሚባርክላትን ነው፡፡ከጳጳስ መለኮታዊ መፍትሔ እንጂ ፖለቲካዊና ጄኔራላዊ መላ አንፈልግም፡፡ለዚህ ለዚህ ሌሎች ምን አሉን? አዎ! የእግዚአብሔር ህዝብም በሩቅ ላለው ምህረትና ይቅርታን ሲለምን እንጂ መዓትን ሲለምን አያምርበትም፡፡ክፉ ላደረገብን ክፉን ከተመኘን  ሰይጣን ታዲያ ምን አጠፋ? ብዙ ተምረን፣ምህረት በዝቶልን የቆምነው የተሻልን ነን በማለት ፈራጅ እንድንሆን አይደለም፡፡በሚብስ ክፋት ተይዘናልና ህዝቤ ሆይ በንስሐ እንመለስ!!! ኢትዮጲያ ሆይ! "ርጉም ተረጋግሞ ያልቃል" ያልሽ አንቺው ነሽና አንቺው ረጋሚቱ እናዳታልቂ "ለጠላትሽ" ፍቅርን ፣ለአሳዳጅሽ ጸሎትን ልመጂና የጥላቻና የእርግማን ሰይፍሽን ወደአፎቱ መልሺው !!! ወይን ሆይ! እሾሁ ከወዴት ነው ፍሬሽ ሆኖ የመጣው?
 ኢትዮጲያ ሆይ! አይን ልቡናሽን ያብራልሽ፡፡ አሜን፡፡               


5 comments:

  1. God bless you my brother.

    ReplyDelete
  2. AMEN KALE HYWETN YASEMALN!!!

    ReplyDelete
  3. ባለቤት የሌለው ታሪክ ሆነብኝ ስለማን እንደሆነ ፅሀፉ በግልፅ ካልተናገረና እናንተው እወቁት ወይም ይህንን ማወቅ እንዴት ያቅታችሁዋል ከተባለ ጉዳዩ በተወሰኑ የሚተዋወቁ ግለሰቦች ዙሪያ ብቻ ያጠነጠነ ቤተሰባዊ እንጂ ለብዙሀኑ መረጃ የሚያቀብል አልመሰለኝም፡፡ መረጃ አልባ የሆነ ፅሁፍ ደግሞ ሌላ ተመጣጣኝ ስም አለው፡፡ ይህንን መጥቀስና ማለት አይገባኝም፡፡ ግን ለማንበብ ጊዜዬን በከንቱ ወሰዳችሁብኝ ፡፡ አዝናለሁ፡፡

    ReplyDelete