Monday, 4 November 2013

ለተበተኑ



       Please read in PDF 
  ነገሩ ለምድር ያልተሰማና እንግዳ ነው፡፡ኢየሩሳሌም አዲስ ነገር አስተናግዳለች፡፡እነዚያ የተናቁና ፊደል ያልቆጠሩ የገሊላ ሠዎች(ሐዋ.2÷7)በቅዱስ ጴጥሮስ መሪነት የሰበኩት ስብከት ፍሬው በግልጥ ታይቶ ብዙ አማኞችን ወደመንግስቱ አፍልሷል፡፡ሐዋርያት ከዚህ ቀን የበለጠ ሌላ ደስታ ይኖራቸዋል ብዬ አልገምትም፡፡በእርግጥም ሰው ሲድን እንደማየት ያለታላቅ ደስታ ከወዴት ይገኛል?! በዚህ ሳይበቃ "ጌታም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር።"(ሐዋ.2÷47)፡፡በክርስቶስ ደም የተመሰረች ቤተ ክርስቲያን በዚህ ቃል መሰረት ራሷን ልታይ ይገባታል፡፡ክርስቶስ ያለባት ህያው ቤተ ክርስቲያን  የሚድኑ ነብሳት ሊበዙና ሊጨመሩባት እንጂ አንድ እያስገባች አስር በሌላ በር መሸኘት የለባትም፡፡ሥርና ልምላሜ ያለው ነገር ያድጋል፡፡እንኪያስ የሚያጸና ቃሉንና የሚያለመልም ደሙን የጨበጠች ቤተ ክርስቲያን በምንም አይነት መልኩ ልትጠወልግና ልትታወክ አይገባትም፡፡ጠውልጋ ከታወከች ግን ራሷን ህይወት ባለው ንስሐ ዳግም ማደስ ይገባታል፡፡
         እኒህ ያመኑና የበዙ ነፍሳት በኢየሩሳሌም በአንድነት ተቀምጠው ሳለ መነቃቀፍና ማንጎራጎር ስለጀመሩ(ሐዋ.6÷2) ሐዋርያት እስጢፋኖስንና ሌሎች ስድስት መጋቢዎችን ሾሙላቸው፡፡ወንጌሉን ከሚቀብሩ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ ተሟሙቆ መቀመጥ ነው፡፡በዚህ ሁኔታ መቀመጥ ደግሞ ሌላ ችግሩ ሐሜትና መነቃቀፍ ይበዛዋል፡፡ብዙ ጊዜ በጾም ወራት ለጸሎትና ቃሉን ለማጥናት የመሰብሰብ ልማድ ነበረን፡፡በዚህ ጊዜ ግን የሚበዛው ሰዓት ከዝግጅቱ በኋላ ላለው አገልግሎት ሳይሆን በፌዝና በቧልት ነበር የሚያልፈው፡፡የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ይህ ችግር ተከስቶባት ነበር፡፡


       ዛሬ ያለችው ቤተ ክርስቲያንም አንዱና ከባድ ችግሯ ይህ ነው፡፡በ"ታላላቅ" ከተሞች ላይ ተሟሙቆ መቀመጥ፡፡እስከ ገጠር ያለችውን ቤተ ክርስቲያን መድረስ ትተን በመሐል ከተማ በብዕር ሾተል እየተወጋጋን ስንበላላና ስንነካከስ ፣ምቹና ቅንጡ ጉባኤያትን ስናማርጥ፣አሜሪካና አውሮፓን አሻግረን እያየን ለቁጥር የሚታክቱ አብያተ ክርስቲያናት ተዘጉ፣ በሚሊየን የሚቆጠሩ ተበትነው በእንግዳና ልዩ ልዩ የአህዛብ ትምህርት ተጠልፈው ወደቁ፡፡ለብታን መርጦ መኖር ለወንጌል አገልግሎት አይመችም ፡፡
የአገልጋይና የስጦታም ችግር የለብንም፡፡ገና ሲናገሩ ሰዎችን ወደልባቸው የሚመልሱ ፣ስለኃጢአታችን በእንባ እንድንታጠብ የሚያደርጉ፣ቆርጠን ከኃጢአታችን አለም እንድንወጣ የሚያስጨክኑ፣ለእግዚአብሔር ፍቅር ብቻ እንድንገዛ የሚማርኩ ድንቅ አገልጋዮችን በአይኔ አይቻለሁ፡፡አዎ! ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ከገጠር እስከከተማ ፣ከአጥቢያ እስከገዳም ማሰማራት የቻለችበት አይመስለኝም፡፡በቀደመው ዘመን አንድና ሁለት አባ ወራ ባለበት ገጠር ይናኝ የነበረውን ወንጌል ዛሬ በትዝታ ነው የሚተረክልን፡፡
        አዎ! ወንጌሉን ትተን ተሟሙቀን መቀመጣችን ሥራ ፈትና ቧልተኛ አድርጎናል፡፡አንዳንዶች ደግሞ አለዋጋ የተሰጣቸውን ወንጌል በከንቱ መስጠት ሲገባቸው (ማቴ.10÷8)ከዕለት ጉርስና ከአመት ልብስ አልፈው የሚጠይቁትን የወርቅና የብር መጠን ስንሰማ ይኼ "የጥቁር ቀሚስ ኢንቨስትመንት"  ወዴት እየመራን ነው? ያሰኛል፡፡ተሟሙቀን መቀመጣችን ትንሽ ሰርቶ ብዙ በመሰብሰብ የሥጋውን ኑሮ አጣፍጦልናል፡፡ስለዚህ ወንጌሉን በመከራ ደስታና በመገፋት ተድላ ውስጥ ሆነን መስበክን ጠልተነዋል፡፡
ሁላችንም በሥራችን ብንሰማራ ፣አንዱ የሌላውን ጸጋ አክብሮ ነብሳትን ለማዳን ብንፋጠን፦በእውኑ መባላትና መነካከሱ ከወዴት ይመጣ ነበር?ደግሞስ መነቃቀፍና ማንጎራጎር ይሰማ ነበርን?
        ተሟሙቀው በተቀመጡባት በኢየሩሳሌም ከተማ በእስጢፋኖስ ሞት ምክንያት ታላቅ ስደት ተነሳ፡፡ በአንድነት የነበሩት ተበተኑ፡፡የእስጢፋኖስ ሞት ሁለት ነገር ለውጧል፡፡
1-     ቅዱስ አውግስጢኖስ እንዳለው እስጢፋኖስ ሲወገር በጸለየው ጸሎቱ ቤተ ክርስቲያንን ያፈርስ የነበረው ሳውል ወደቤተ ክርስቲያን ዘወር እንዲል ማልዷል፡፡ምልጃውም ተሰምቷል፡፡
2-    በሞቱ ምክንያት ተሟሙቀው የተቀመጡት ሁሉ ወደይሁዳና ወደሰማርያ ሐገሮች ተበተኑ፡፡(ሓዋ.8÷1-7)፡፡
        ሁሉ በየራሳቸው ቃሉን ተሸክመው እየዞሩ መስበክ ጀመሩ፡፡ ዘር የሚያፈራው በመልካም እርሻ ላይ ሲበተን ነው፡፡ያልተበተነ ዘር አያፈራም፡፡መልካም ዘር የእግዚአብሔር ቃል (ማቴ.13÷23)ካልተዘራ ካልተበተነ ሠላሳ ሥድሳ መቶ አያፈራም፡፡ሊያፈራ መበተኑ ግድ ነው፡፡ቤተ ክርስቲያን በምድር ላይ ልታብብና ልታፈራ ግድ ዘሩን ሳታቋርጥ መበተን አለባት፡፡የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ስትበተን በሥጋ አይን ላየ ነገር ያበቃ ያከተመ ይመስላል፡፡ጌታ ግን ነገሩን ለበጎ አድርጎታል፡፡ስለዚህም መበተናቸው ግድና አስፈላጊ ነበር፡፡ከዚህ በኋላ መልዕክታት ሲጻፉ ይህ የተወደደ ቃል አብሮ ተቀምጧል፡፡(1ጴጥ.1÷2፤ያዕ.1÷1) "ለተበተኑ" የሚል የተወደደ ቃል፡፡
         መቼም ለዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን መበተን ጠማማ ትውልድ ተነስቶ አንድ ብርቱ ሰው ገድሎ ማየት አለብን እንደማንል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችንና ለተግሳጽ እንዲሆነን ተጽፏል፡፡(2ጢሞ.3÷16)እንኪያስ የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ታላቅን ነገር ታስተምረናለች፡፡ወንጌሉ በኢየሩሳሌም ላሉ (ለዳኑት ብቻ) አይደለም፡፡በይሁዳና በሰማርያ እንደተገለሉና እንደተናቁ እንደተተው ለሚያስቡም አህዛብና መናፍቃን ለምንላቸውም ወንጌሉ ያስፈልጋቸዋል፡፡ተሟሙቀን ከተቀመጥንበት ምንም እንኳ የሚመችና የሚደላ ነገር ባይኖርም በመከራና በስደት ውስጥ ሆነን በመበታተን ወንጌሉን ለመዝራት እንነሳ፡፡ፍሬው እንዲህ ነውና የሚጎመራው፡፡
                         ይቆየን፡፡አሜን፡፡

1 comment:

  1. AMEN kale hywetn yasemaln
    endh bewstachin yemiyabseleslen sinegerln sitawejiln betam des ylal ye geterun abyate krstiyan yetemeleketew yelem yetemola ye haymanot tmhrt lemagignet gdeta ketema bota menorn eyeteyeke new wendmachin berta EGZIABHER YAGZH!!!!

    ReplyDelete