Tuesday 13 April 2021

አባባይ “shows”

 Please read in PDF

የስህተት መምህራን “የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ ምን ያህል የጽድቅ አገልጋዮች እንደሚመስሉ (2ቆሮ. 11፥13-14)፣ ምን ያህል ውስጠ ተኵላነታቸውን ደብቀው የበግ ለምድ እንደሚለብሱ (ማቴ. 7፥15) … ጃፒ ከኬፋ ሚደቅሳ ጋር ያደረገው ቃለ መጠይቅ ጥሩ ማሳያ ነው[በእርግጥ እንዲህ ዓይነት አባባይ ቃለ መጠይቆች፣ ከዚህ በፊት ብዙ ተደርገዋል]።

ራእይ 13 ላይ ኹለት ዓይነት አውሬዎች አሉ፤ አንደኛው የለየለት ፍጹም አውሬ ሲኾን፣ ኹለተኛው ግን፣ “የበግ ቀንዶችን የሚመስሉ ኹለት ቀንዶችም ነበሩት እንደ ዘንዶም ይናገር ነበር።” (ቊ. 11) የተባለለት ነው፤ በግ ይመስላል ግን እንደ ዘንዶው ይናገራል፤ እንዲያውም በግ መሳዩ ሥራው ምን እንደ ኾነ ሲናገር፣ “ለፊተኛው አውሬ ምድርና በእርሱ የሚኖሩት እንዲሰግዱለት ያደርጋል።” (ራእ. 13፥12)። በግ መሳዮች ኹሌም ለግል አምላካቸው መሥዋዕትና ክብርን አስገቢ ናቸው።

ሐሰተኛ መምህራን እንዴትም ቢቀባቡ፣ ቢኳኳሉ፣ ሽሙንሙን ያሉ ቃላትን ቢጠቀሙ፣ ቅልስልስ ያሉና ጨዋዎች ቢመስሉም፣ ትሑታንና በሴትና በገንዘብ የማይታሙ ቢኾኑም … የስህተት መምህራንና አስተማሪዎች መኾናቸውን አያስቀረውም። ለጊዜው በጎችን ስለሚመስሉ፣ ተኵላነታቸውን ሰዎች ላያስተውሉት ይችላሉ። ነገር ግን ከበጎች ጋር እንዴትም ቢጣበቁና ፍጹም ተመሳሳይ ቢመስሉም፣ መለየታቸውና መታወቃቸው አይቀርም።

ዘወትር የሚያሳዝኑኝ ግን እኒህን የስህተት መምህራን የሚያባብሉ[እሹሩሩ እያሉ] ጥያቄ አቅራቢዎችና የ“show” አዘጋጆች ናቸው። በእነርሱ “ሾው” ጠላት ጠላትነቱን፤ የስህተት አስተማሪም ስህተቱን የሚተው ይመስላቸዋል። የ“show” አዘጋጆች የስህተት አስተማሪዎች ስሑታን መኾናቸውን ቢያውቁም፣ ሊቀባቡላቸው፣ ሊያለሳልሱላቸው፣ ሊሸፋፍኑላቸው ብዙ ይጥራሉ፤ ለኹለት ቤት የሚሠሩ ዘወትር፣ የራሳቸው ቤትና እምነት የላቸው። ሚዛናዊነት ማለትም የታወቀውን ስህተትና ነውር፤ ኑፋቄ በለቀቅተኛ መንፈስ ማለባበስና ማንኳሰስ አይደለም!

ሚዛናዊነት በቅዱስ ቃሉ ላይ ሳያወላውሉ መቆምና ለቃሉ ብቻ መታመን ነው፤ ይህ ለአንዳንዶች ግትርነትና አጉል ሐቀኝነት ነው፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ልጆች ለአንዱ ጌታ የመታዘዝ ኹነኛ ምልክት ነው። አማኞችና አገልጋዮች በዚህ ዓለም ሲኖሩ፣ ከአንዱ ጌታ በቀር ማንንም ማስደስትና መታዘዝ አይችሉም፤ ከዚህ ውጪ ለኹለተኛው ዐሳብና ጌታቸው ለመታዘዝ ከጣሩ፣ ማመቻመች ከጀመሩ ግን ወደለየለት ግብዝነት ከመግባታቸው ባሻገር፣ ከቃሉ ይልቅ ለቃላቸው የሚተጉ እርባና ቢሶች ይኾናሉ! ለክርስቶስ ለቃሎቹና ለሕይወቱ ብቻ መታዘዝና ሕይወት ነው!

የጌታ ጸጋና ሰላም ኢየሱስን በፍጹም ልባቸው ከሚወዱት ጋር ይኹን፤ አሜን።

No comments:

Post a Comment