Thursday 1 April 2021

የኮቪድ 19 ክትባትና ውርጃ

 Please read in PDF

“ስለ ምንስ መልካም እንዲመጣ ክፉ አናደርግም? እንዲሁ ይሰድቡናልና አንዳንዱም እንዲሁ እንድንል ይናገራሉና።” (ሮሜ 3፥8)

ክርስትናና ሳይንሳዊ ግኝቶች

ክርስትናና ሳይንስ እርስ በርሳቸው ጥዩፋን አይደሉም፤ ሳይንስ በብዙ መንገዱ ከእግዚአብሔር ባገኘው ጥበብ፣ መልሶ እግዚአብሔርን ተቃዋሚና ተጠያፊ ቢኾንም፣ ክርስትና ግን ለሳይንስ ፍጹም ጀርባውን የሰጠ አይደለም። ክርስትና ለሳይንስ ጀርባውን የማይሰጠውና በእግዚአብሔር መግቦታዊና ሉዓላዊ ጌትነት ሥር ኾኖ የሚቀበለው ግን፣ ሳይንስ ለእግዚአብሔር ፍጥረት አክብሮት ሲሰጥና ራሱ እግዚአብሔርን የሚቃወም እስካልኾነ ድረስ ብቻ ነው። የእግዚአብሔርን ፍጥረት የሚቃወምና ፍጥረት የሚገዛበትን ሥርዓት የሚቃወም እርሱ እግዚአብሔርን ይቃወማልና።



የኮቪድ 19 ክትባት የተቀመመው፣ ከሕጻናት ውርጃ በተገኘ ዘረመል መኾኑን ከአጥኚ ታላላቅ ሰዎች እስከ የሃይማኖት መምህራን በአንድ ቃል ተስማምተው ተናግረውታል።[1] በመጽሐፍ ቅዱስ ውርጃ ፍጹም ርኩሰትና በእግዚአብሔር መልክና ምስል ያለውን ክቡር ፍጥረት መግደል እንደ ኾነ በአንድ ቃል ጮኾ ይናገራል። ሕይወታችን ውድና የእግዚአብሔር ቅዱስ ስጦታ ነው፤ የሚጀምረውም ከጽንስ እንደ ኾነ መጽሐፍ ቅዱስ እጅግ አጽንኦት ሰጥቶ ይናገራል (ኢዮብ 31፥15፤ መዝ. 127፥3፤ 139፥13፡ 16፤ ኢሳ. 49፥1፤ ኤር. 1፥5፤ ሉቃ. 1፥15፡ 41)።

የእግዚአብሔር ልዩ ትኵረት!

እግዚአብሔር አምላክ በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸመውን የትኛውንም ዓመጻና ርኩሰት ከቶ ቸል አይልም። እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ልቡ የሚራራ፣ ሆዱ የሚላወስ፣ አንጀቱ የሚንሰፈሰፍ ቅዱስና ድንቅ አምላክ ነው። እግዚአብሔር ስለ የትኛውም ኀጢአተኛ ይኹን የሰው ዘር ይገደዋል። ሰውን የፈጠረና ያጸና (ዘዳግ. 32፥6)፤ ደግሞም በዔደን ገነት ውብ መኖሪያን በውበት አዘጋጅቶ ሰውን በዚያ ያኖረው (ዘፍ. 2፥8) ቅዱሱ አምላክ ነው። ስለዚህም የትኛውም የሰው ዘር ለእግዚአብሔር ፍጥረቱና ገንዘቡ፣ የገዛ የእጁ ሥራው ነውና ይሳሳለታል።

እርሱ ለማያመሰግኑ ለክፉዎችም ቸር ነውና።” (ሉቃ. 6፥35) ተብሎ እንደ ተነገረ፣ እግዚአብሔር ለክፉዎች እንኳ ከጻድቃን እኩል በመግቦቱ ዝናም ያዘንምላቸዋል፤ ፀሐይንም ይሰጣቸዋል፤ (ማቴ. 5፥45)። እግዚአብሔር በሉዓላዊነቱና በመግቦቱ ለመላለሙ ስፍስፍ አፍቃሪና ውድ መጋቢው ነው!

ኮቪድ 19ን ለማዳን ሰዎች ምን አደረጉ?

ሰዎች ኮቪድ 19ን ለማዳን የእግዚአብሔርን ዐሳብና ዘላለማዊ ዕቅዱን በሚቃወምና “የሰውን ዘር መብዛትና መስፋት” ኪዳናዊ ቃል (ዘፍ. 1፥28) በሚቃወም መንገድ ተገለጡ። በውርጃ ዘረመል በተገኘና መሠረት ባደረገ መንገድ መድኃኒትን ቀምመው አዘጋጁ። ነገ የተባለውን ቀን ውብና መልካም ለማድረግ፣ ሰዎች ዛሬ መልካምና እግዚአብሔር በማይፈቅደው መንገድ ቆሙ።

በርግጥ ኮቪድ 19 ብቻ ሳይኾን ሌሎች በሽታዎችም ከውርጃ ጋር በተያያዘ መንገድ በሚቀመሙ መድኀኒቶች እንደሚሠሩ አያሌ ጥናቶች ያመለክታሉ። እንግዲህ ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ነው፣ የእኛ ነገ መልካም እንዲኾን ዛሬ ክፉ ልናደርግ ይገባናልን? በማለት የሚሞግተው። ነገ መልካም ኾኖ እንዲመጣ፣ ነገ ብሩህ ቀን እንዲኾን፣ ነገ የተሻለ ዓለም ለመፍጠር … በሚል ሰበብ ዛሬ የዓመጻን መንገድ መከተል በፍጹም ትክክል አይደለም። እግዚአብሔር ይቅር እንደሚለን ብናምንም፣ የምንኖረው ዛሬን እንጂ በማናውቀው በነገ ላይ ተደግፈን ኀጢአት መሥራት አይደለምና፤ “ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል።” ተብሎ ተነግሮአልና።

ምን እናድርግ?

በእግዚአብሔር ሉዓላዊነትና መግቦት እናምናለን፤ እርሱ ለየትኛውም ፍጥረት የሚጨነቅና ደግሞም የሚያገባው፤ የሚገደው አምላክ ነው። በዓለም ላይ ያለውን የትኛውንም ነገር ያውቃል፤ ይሰማዋልም። ክፋትን በተመለከተ እርሱ የትኛውም ክፋት ለክብሩ ሊያደርገው ይችላል፤ እርሱ በቂሮስ፣ በናቡከደነጾር፣ በዮሴፍ በጥላቻ መሸጥ፣ በጲላጦስና በአይሁድ ካህናት … የዘላለም ሥራውንና ዕቅዱን ከመፈጸም የከለከለው አንዳች የለም። ክፉውን ለክብሩ መጠቀም ይችልበታል፤ አማኞች ግን ይህን ከማመን በቀር፣ በዚህ መንገድ ይጓዙ ዘንድ አልተፈቀደላቸውም። እኛ በቅዱስ ትእዛዙና ፈቃዱ ብቻ እንድንመራ ታዘናልና። ስለዚህም ውርጃን ከሚደግፍና ከሚያበረታታ ተግባር፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን ሕይወትና እውነተኛ ትምህርት ከሚቃወምና የሰውን ልጅ ክቡር ሕይወት ከማያከብር ተግባር አማኞች መጠበቅና መከልከል አለባቸው፤ ይህ አለማድረግ ከእውነተኛ ስብዕና እጅግ የራቀ እኩይ ተግባርም ነውና! ክትባቱን ከመውሰዳችሁ በፊት ቀድማችሁ እንድታስቡበት፣ ደግሞም ለእግዚአብሔር በማድላት እንድትቆሙ ይህን አልኩ!

ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ፤ አሜን።

 



[1] https://www.youtube.com/watch?v=qlp1DOO0BVA እንዲሁም https://www.youtube.com/watch?v=cwWjf86FiCg መመልከት እና በተጨማሪም https://fiec.org.uk/resources/responding-to-the-ethics-of-the-covid-vaccine የሚለውን ማንበብ ይቻላል፡፡

1 comment: