Saturday 17 April 2021

ኒቆዲሞስና ነገረ ዳግም መወለድ

 Please read in PDF

ኒቆዲሞስ፣ ኢየሱስን እጅግ በብዙ ከሚንቁት ፈሪሳውያን ወገንና ከአይሁድ አለቆች መካከል አንዱ የነበረ ሰው ነው። በዚያ ዘመን ፈሪሳዊ መኾን ሕጉን እንጠብቃለን፤ ሕጉን በመጠበቅም እንጸድቃለን ለሚሉ ሃይማኖተኞች ብርቱ ትምክህት ነው። ፈሪሳውያን ለሕጉ እጅግ ቀናተኞች ከመኾናቸው የተነሣም፣ ከመካከላቸው ቀራጮችንና ኀጢአተኞችን ፍጹም በማግለል ራሳቸውን እንደ ፍጹም ጻድቃን ይቈጥሩ ነበር።

እንግዲህ እንዲህ ካሉት መካከል ኒቆዲሞስ፣ እጅግ የተናቀውንና በፈሪሳውያን ወገኖቹ ዘንድ እምብዛም ተቀባይነት የሌለውን ኢየሱስን ፍለጋ ሌሊት፤ ሌሊት ወደ እርሱ ይመጣ ነበር፤ (ዮሐ. 3፥2)። ኒቆዲሞስ፣ የአይሁድ አለቃ ወይም ታላቅ ባለ ሥልጣን ነው፤ ነገር ግን ሥልጣኑን ንቆ ኢየሱስን ፍለጋ ዝቅ ብሎ የመጣ አስተዋይም ነው። ሥልጣንና ምድራዊ የሰው ክብር እያለ፣ ለጌታ ዝቅ ማለት ታላቅ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ይፈልጋል። በእርግጥም አብ ካልሳበው በቀር፣ ማንም ወደ ኢየሱስ መምጣት አይችልም፤ (ዮሐ. 6፥44)፡፡

የኢየሱስ ትምህርት

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እርሱን ከልብ ለሚሹት ሰማያዊ ምስጢር በመግለጥ የሚተካከለው የለም፤ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፥” (ማቴ. 13፥11) በማለት ለደቀ መዛሙርቱ እንደ ተናገረ። ጌታችን ሰው ወደ እርሱ መቅረብ የሚችለው ዳግመኛ ሲወለድ ብቻ እንደ ኾነ ለኒቆዲሞስ ሲናገረው፣ ኒቆዲሞስ ዳግመኛ መወለድን የተረዳው ከእናት ማኅፀን እንደገና ገብቶ ስለ መወለድ ነበር። የአይሁድ አለቃና መምህር የነበረው ኒቆዲሞስ፣ የኢየሱስ ነገር የሞኝ ትምህርት ሳይመስለው አልቀረም። “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ኹለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን?” በማለት የጠየቀውም ለዚሁ ነበር

ጌታችን ኢየሱስ ግን፣ ዳግመኛ ካልተወለደ ወይም ከላይ ከሰማይ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከቶ ሊገባ እንደማይችል አበክሮ ነገረው፤ ጌታችን ኢየሱስ፣ ኒቆዲሞስ ብቻ ሳይኾን ሰው የተባለ ኹሉ፣ ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር ወደ መንግሥቱ እንደማይገባ ሲናገር እንዲህ አለ፣ “ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል”፤ ስለዚህ ዳግመኛ መወለድ ወይም ከላይ ከሰማይ መወለድ ግዴታም፤ አስፈላጊም ነው። ኒቆዲሞስ ነገሩን ለመረዳት በጥቂቱ ዘግይቶአል፤ ወይም መረዳት አዳግቶታል፤ ስለዚህ ኢየሱስ የሚያውቀውን ምሳሌ ነገረው። ምሳሌው የሚያውቀውን የነፋስ ምሳሌ ሲኾን፣ እርሱም ስለ መንፈስ ቅዱስ ነበር።

ነገረ መንፈስ ቅዱስ

በብዙ መገረም ለተሞላው ኒቆዲሞስ፣ ጌታ ኢየሱስ እንዲህ አለው፤ “ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው።” (ዮሐ. 3፥7)። ነፋስ አይታይም፤ ሥራውን ሲሠራ ግን ይታያል፤ ድምፁ ይሰማል፤ ከየት እንደ መጣ ወዴትም እንደሚሄድ አይታወቅም። ከመንፈስ የሚወለድም ሰው እንዲኹ ነው፤ ማለትም መንፈስ ቅዱስ ኀያል ነውና እንደ ወደደና እንደ ፈቀደ ይሠራል።

እርሱ እኛን ሲወልደን እንዴት እንደ ኾነ አናውቀውም፤ ግን ምስክርነቱና እውነተኛ ፍሬው በምልአትና በእውነት በውስጣችን አለ፤ ሲናገረን እንሰማዋለን፣ ሲታዘበን ወይም ሲወቅሰን እንፈራዋለን፤ መገኘቱ በውስጣችን በትክክል ይታወቀናል፤ ይህም የኾነው በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በማመናችን እኛን የወለደበት ኹለተኛ መውለዱ አብሮን ስላለ ነው። መንፈስ ቅዱስ ካልገለጠለት በቀርም ይህን እውነትና ዘላለማዊ መዳን ማንም ማስተዋል አይችልም። ስለዚህም ዳግመኛ መናገር ይገባናል፤ በክርስቶስ ርኅራኄ እንዲህ እለምናችኋለሁ፤ ከመንፈስ ቅዱስ የተነሣ፣ “ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል”።

የጌታችን ኢየሱስ ጸጋና ሰላም እርሱን ከሚወዱት ጋር ለዘላለም ይኹን፤ አሜን።

 

 

2 comments:

  1. May the SPIRIT be your guide and strength for days to come.

    ReplyDelete
  2. ወዳጄ ፍየል ወዲያ ቅዝምዝ ወዲህ ሆነ መለኪያው መፅሐፍ ቅዱስ ነው የሚለኩት ደግማ የመናፍቃን ሃሳባች ስለዚህ አንተ ከየት ወገን ነህ

    ReplyDelete