Saturday 19 March 2016

ባለፉት ሦስት አመታት ...

   

     ባለፉት ሦስት ዓመታት ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ ከእግዚአብሔር ቃል አንጻር ወቅታዊ ጽሁፎችን ስብከቶችን ትምህርቶችን ግጥሞችን ...ከተወሰኑት ጊዜያት መቋረጥ በቀር በተከታታይ ለማቅረብ ጥሬያለሁ፡፡ በእነዚህ ሦስት ዓመታት ውስጥ ለእግዚአብሔርና ለቃሉ እንጂ ወደማንም እንዳላደላሁ ሕሊናዬ ይመሰክርልኛል፡፡ ከእግዚአብሔር በቀር ማንንም ደስ ለማሰኘትም ሆነ በከንቱ ለመውቀስ እንዳልተጋሁም እንዲሁ፡፡
   በእነዚህ ጊዜያት የተላለፉት መልዕክታት ለብዙዎች እንደደረሱ ብዙ ማሳያዎች አሉ ከእኒህም ማሰያዎች አንዱ በጽሁፎቹ ዙርያ ብዙዎች ተከራክረዋል ተወያይተዋል ብዙ የድጋፍና የማበረታቻ ሃሳቦች ደርሶኛል፡፡ የዚያኑ ያህል ደግሞ የበረታ የተቃውሞ ድምጽም ነበር፡፡ ከተቃውሞውም ብርታት የተነሳ ብዙ ጊዜ፥በስድብ በንቀት በአድመኝነት በፍጹም ነቀፌታ በጥላቻ ... የሚገለጥመንፈሳዊነት አለን?!” በማለት ራሴን ሞግቻለሁ፡፡ በእርግጥም አገልግሎቱን ለምን ተቃወሙት? ብዬ ጥያቄ ሳበዛ፥አትነጫነጭ፥ አገልግሎቱ ፍሬ እያስገኘ ስለሆነ ነው ዝም ብለህ ሥራውን ሥራ፡፡በማለት የመከረኝ ወንድሜ ምክር ሁሌም ያበረታኛል፡፡
    በብዛት ተግሳጽ ላይ ማተኮሬ፥በጎ የሆነው የማይታየኝ አላስተዋይ ሆኜአይደለም፡፡ ግና እውነታውንና የቤተ ክርስቲያንን ጠንካራ ጎንም በማስታወስ እንድንማርበት በማንሣትም ከመጠቆም አላረፍኩም፡፡
     የጡመራ መድረኳ በብዙዎች ዘንድ እንድትነበብ ለማድረግ ብዙ ጥረት የማደርገውን ያህል፥ ሰፋፊና ጥልቅ የሆኑ ተከታታይ ትምህርቶችንም ለማዘጋጀትና በጡመራ መድረኳላይ ለመልቀቅ ወደፊት በጌታ ጉልበት እበረታለሁ፡፡ በጸሎታችሁ በማበረታቻ ቃላችሁ በበጎ የምክር ቃላችሁ ጽሁፎችን በማረምና የተለያዩ ሃሳቦችን በማካፈል አዳዲስ መረጃዎችን በማቀበል ዋቢ የሚሆኑ መጻሕፍትን በመጠቆም ለመንፈሳዊ ሕይወቴ ማደግ በቅርብ የማላገኛቸውን መጻሕፍት በመስጠት የጡመራ መድረኳን ሎጎዎችን በማዘጋጀትና ይዘቶቹንም በማስተካከል ከጎኔ ለነበራችሁ ወንድሞችና እህቶች አባቶችና እናቶች ከፍ ያለ አክብሮታዊ ምስጋናዬን ከልብ አቀርባለሁ፡፡
     በሚቀጥሉት ጊዜያት ለማቀርባቸው አገልግሎቶች የበረታሁ እሆን ዘንድ በጸሎታችሁ አስቡኝ ይልቁን ከዚህ ክፉ ትውልድ በማምለጥ ሌሎች እንዲያመልጡ የሚረዳውን ብርቱውን ቅዱስ ቃል ያለአንዳች ፍርሃት እገልጥ ዘንድ ደግሜ እላለሁ፥ በጸሎታችሁ አስቡኝ፡፡

  የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ማስተዋሉን ለሁላችን ያብዛ፡፡ አሜን፡፡  

No comments:

Post a Comment