Please read in PDF
የዓቢይ ጾም ፊተኛው ሳምንት መጠርያ ዘወረደ ይባላል፡፡ ይህም ክርስቶስ ኢየሱስ ከሰማየ ሰማያት የሰው ልጆችን ለማዳን በእርሱ ፤ በአባቱና በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ መምጣቱን ቤተ ክርስቲያን በአምልኮዋ ትዘክረዋለች፡፡ እርሱ የወረደው እኛን ለማዳን ነው፡፡ ምክንያቱም ከሰው ወገን ወይም ከፍጡር ወገን ማንም እኛን ማዳን ስላልተቻለው አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ በገዛ ፈቃዱ ሊያድነን መጣ፡፡ ዛሬ ይህ እኛን ለማዳን ከሰማያት የወረደው ጌታ፥ ስለመውረዱእየተነገሩ ያሉ ብዙ ክህደቶች አሉ፡፡
የዓቢይ ጾም ፊተኛው ሳምንት መጠርያ ዘወረደ ይባላል፡፡ ይህም ክርስቶስ ኢየሱስ ከሰማየ ሰማያት የሰው ልጆችን ለማዳን በእርሱ ፤ በአባቱና በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ መምጣቱን ቤተ ክርስቲያን በአምልኮዋ ትዘክረዋለች፡፡ እርሱ የወረደው እኛን ለማዳን ነው፡፡ ምክንያቱም ከሰው ወገን ወይም ከፍጡር ወገን ማንም እኛን ማዳን ስላልተቻለው አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ በገዛ ፈቃዱ ሊያድነን መጣ፡፡ ዛሬ ይህ እኛን ለማዳን ከሰማያት የወረደው ጌታ፥ ስለመውረዱእየተነገሩ ያሉ ብዙ ክህደቶች አሉ፡፡
ከግኖስቲካውያን እስከ ዶሴቲክስ ፤ ከአርዮስ እስከ ንስጥሮስ ፤ ከሞርሞናውያን
እስከ ኦንሊ ጂሰሶች ፤ ከይሖዋ የመንግሥት አዳራሽ ምስክሮች እስከ ዘመነኞቹ የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ (New age
Movement) ፤ የእምነት እንቅስቃሴ (Faith Movement) እና Biblical Unitarian እስከሚባሉት ድረስ ለዘመናት
መናፍቃን መልካቸውን እየቀያየሩ በጌታ ኢየሱስ ላይ እጅግ አጸያፊ ክህደቶችን አውርደዋል ፤ አሁንም አላባሩም፡፡ ከሚያደርሱትና እያደረሱ
ካሉት ጥፋት አንጻር ግን ቤተ ክርስቲያን ሥራዋን በአግባቡ እየተወጣች ነው ለማት አያስደፍርም፡፡
መናፍቅ ማለት
መናፍቅ
ማለት ደግሞ በቁሙ ናፋቂ ፣ አናፋቂ ፣ የማጠራጠር ፣ የሚያጠራጥር ፣ ጠርጣሪ አጠራጣሪ ፣ ሃይማኖቱ ሕጹጽ፥ ሙሉና ፍጹም ትክክል ያይደለ ፤ መንፈቁን አምኖ
መንፈቁን የሚክድ ማለት ነው፡፡ [1]
ይህም ግማሽ እውነቱን ይዞ ግማሽ ውሸቱን የሚጨምርበት ማለት ነው፡፡
በሌላ ትርጉም፦ “ … ነፈቀ … ከኃይማኖት የወጣ
፣ እምነተ ሰንካላ፣ ተጠራጠረ ፣ መናፈቅን ፣ ከሀዲን ኾነ ነፈቀ፡፡” በማለት ይፈታዋል፡፡ [2]
በአዲስ ኪዳኑ ግሪክ፦ “መናፍቅ” የሚለውን የቃል
ትርጉም፥ “ክፍፍል ፤ ልዩነት” (ሐዋ.24፥14፤ ገላ.5፥19-20) ብሎ ሲተረጉመው፥ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ይህን ቃል
የተጠቀመችው፥ “መሠረታዊውን የክርስትና እምነትን ለሚክድ ግለሰብ (ቡድን) በመጠቀም ፤ እንዲህ ያለውን አካል ከሕብረቷ መለየት
እንደሚያስፈልግም ጭምር ታስተምር” ነበር፡፡ (ሐዋ.24፥14)
አሁንም ፦ “መናፍቅ ፤ በአንድ ሃይማኖት ውስጥ
የተለየ ትምህርትን ተከታትሎ፥ በመጠራጠር መለያየትን የሚፈጥርና የሚወግን (2ጴጥ.2፥1፤ ቲቶ.3፥10፤ 1ቆሮ.11፥19)” በማለት
ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላቱ ይፈታዋል፡፡ [3]
እንግዲህ ከዚህ በኋላ መናፍቅ የምንላቸው አካላት
ትክክለኛውን እምነት በመጣል ወይም ወደጎን በመተው ትክክለኛውን እምነት የሚጠራጠሩ ፤የማይቀበሉ ፤ የሚዋዥቁ ናቸው ማለት ነው፡፡
የመጀመርያዎቹ መናፍቃንና ጠባያቸው
መናፍቃን በአብዛኛው ዘመናቸው ራሳቸውን የሚጠሩት በሌላ ስም፥ ማለትም በእስልምና፣
በሒንዱ፣ በሻንቶ፣ በቡሂድ … ሳይሆን በክርስትና ውስጥ ሆነው፥ ራሳቸውን “እኛ ነን ትክክለኞች” ብለው ስለሚጠሩ ይህን ሥያሜ ሊያገኙ
ችለዋል፡፡ ሁሉም መናፍቃን ከክርስትና አካል የነበሩና በኋላ ግን በእንግዳ ትምህርት (ኤፌ.4፥14 ፤ ዕብ.13፥9) ተጠላልፈው
የወደቁ ፤ የተለዩ ናቸው፡፡
መናፍቃን የሚታወቁበት ልዩ ባህርያቸው መሠረታዊውን
የክርስትና መሠረተ እምነት በግማሽ(መንፈቁን) በመካድ ወይም ሙሉ
ለሙሉ ባለመቀበል ነው፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ ጉባኤ ሠርታ የማውገዟና የመለየቷ ምክንያትም መሠረተ እምነትን “በመናዳቸውና”
ባለመቀበላቸውም ጭምር ነው፡፡
መናፍቃን በጌታ አጠራር፦ “ጸራዊ” ፤ በሐዋርያት
አነጋገር፦ “ቢጽ ሐሳውያን(የሐሰት ወንድሞች)” ሲባሉ በሊቃውንት ግን፦ “መናፍቃን” ተብለዋል ቢባልም ፤ በሐዋርያትም ዘመን ግን
መናፍቃን ይባሉ እንደነበር ማሳያዎች አሉ፡፡(ገላ.5፥19)
የመጀመርያዎቹ የቤተ ክርስቲያን መናፍቃን በመባል
የሚታወቁት ግኖስቲካውያን (ግኖሲሳውያን) [4] ናቸው፡፡ “ግኖሲስ”
ማለት በግሪኩ “ዕውቀት” ማለት ሲሆን፥ የእምነቱ ተከታዮች ስያሜ የሆነው “ግኖስቲዝም” ማለት ደግሞ፥ ትርጉሙ “አዕምሮዐዊ ፤ ዕውቀታዊ
፤ መዳን በዕውቀት የሚሉ ፤ ዕውቀታውያን” የሚል ሃሳብን የያዘ ነው፡፡
ግኖስቲካውያን በክህደታቸው የመጀመርያይቱ ቤተ ክርስቲያን
ፈተናዎች ነበሩ፡፡ ፈተናዎች ብቻ ሳይሆኑ ቤተ ክርስቲያን ካሳለፈችበት ከየትኛውም ጊዜ ፈተናዎቿ በእነዚህ መናፍቃን የደረሰባት ጥቃትና
ጥፋት የሰፋና መልኩን እየቀያየረ ዛሬም ድረስ የዘለቀና ብዙዎችን ጠላልፎ የጣለ አደገኛ ትምህርት ነው፡፡
ስለነዚህ መናፍቃን ሁሉም ሐዋርያትና ደቀ መዛሙርት
ክህደታቸውን ጠቅሰው እንደቃሉ መልስን በመስጠት አሳፍረዋል፤ ሃይማኖትን ጠብቀዋል፡፡ የቅዱሳን ሐዋርያት የአዲስ ኪዳን መልዕክታትን ለመጻፍ
ሲነሱ፥ በሁሉም ህሊና የመጀመርያዎቹ የቤተ ክርስቲያን መናፍቃን ግኖስቲካውያን በቤተ ክርስቲያን የሚያደርሱትን ጥፋትና የበጎችን
ስርቆት በመቃወም በወንጌል እውነት ላይ በመቆም የተጻፉ መልዕክታት ናቸው፡፡
ሐዋርያት መናፍቃንን በጽሁፎቻቸውና በትምህርታቸው በግልጥ ተቃውመዋል፡፡
የሐሰት ትምህርቶቻቸውን ገልጠው ከመንፈስ ቅዱስ በተሠጠ ስለታማ የወንጌል ቃል ቆራርጠውታል፡፡ ለምሳሌ፦
አሁን በዘመናችን ያሉት የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ ፣ የእምነት እንቅስቃሴና
Biblicla Unitarian የሚባሉ መናፍቃን ከግኖስቲካውያን የተቀዳውን ትምህርት እንዲህ በማለት ዛሬ ያስተምሩታል ፤ “ክርስቶስ እርሱ
አምላክ አይደለም ፤ የአብ ሙላት ነው እንጂ፡፡ እርሱ ከዘላለም አምላክ አይደለም ሥጋን ለብሶ ከመጣ በኋላ እንጂ፡፡ ኢሳይያስ ከተወለደ
በኋላ የዘላለም አምላክ ይሆናል አለው እንጂ ነው አላለም፡፡ እርሱ እኛን ለማዳን በአብ ሃሳብ ውስጥ የነበረ እቅድ እንጂ እርሱ
አካል ኖሮት አምላክ የሆነ አይደለም ፤ እርሱ አምላክ ቢባልም አምላክ አይደለም” ይላሉ፡፡
ለኒህ
ግኖስቲካውያን መናፍቃን ቅዱስ ጳውሎስ በቀደመው ዘመን፦ የክርስቶስ ሙላት ማለት የእግዚአብሔርን ኀይሉን ባህርይውንና ሁለንተናውን
የሚገልጥ፥ እንዲሁም የአብ የባህርይ ልጁ ክርስቶስ ኢየሱስ፥ ሁሉን የፈጠረና ከሁሉ በላይ መሆኑን በግልጥ ተናገረ፡፡ (ቆላ.1፥15-21
፤ 2፥9 ፤ 21) መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ፤ ከሥጋና ከደም ሃሳብ ርቆ ለሚያጠና ሰው ከላይ የተጠቀሰው ክህደት
ከተረት የሚዘል አይደለም፡፡
ሰይጣን በክርስቶስ ላይ ያለንን እምነትና እውነት ሊያስጥለን በብርቱ
የሚታገለውና ብዙዎችንም ያስጣለው ክርስቶስ የሁሉ ነገር መሠረት መሆኑን ስለሚያውቅ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከዘላለም አምላክ ነው፡፡
ነቢዩ በቤተ ልሔም ስለሚወለደው ሕጻን ሲናገር እንዲህ አለ፦ “ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ
ከዘላለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል።” (ሚክ.5፥2) ፤ ደግሞም ወንጌላዊው ሎጎስ [5]
የሆነውን ቃል፥ “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።” (ዮሐ.1፥1) በማለት
ተናገረ፡፡
የግኖስቲካውያንንና የአርዮስን ትምህርት ያወገዙት ሦስት መቶ አሥራ
ስምንቱ ሊቃውንትም በ325 ዓ.ም በኒቂያ እንዲህ አሉ፦ “ዓለም ሳይፈጠር
ከእርሱ ጋር በነበረ፥ ቀዳሚና ተከታይ የሌለው የአብ ልጅ በሚሆን፥ በአንድ ጌታ፥ በኢየሱስ ክርስቶስም እናምናለን፡፡ እርሱም ከብርሃን
የተገኘ ብርሃን፥ ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ፥ የተፈጠረ ያይደለ የተወለደ፥ በመለኮቱ ከአብ ጋር አንድ የሚሆን ነው፡፡
ሁሉ በእርሱ የሆነ፥ ያለእርሱ ግን በሰማይና በምድር ምንም ምን የሆነ የሌለ ነው፡፡ ...”
አዎን! ኢየሱስ
ክርስቶስ አልፋና ኦሜጋ ነው ፤ የመጀመርያና የመጨረሻ፡፡ (ራእ.1፥8) እርሱ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አምልኮን የሚቀበል ፤
ያለ የነበረ የሚኖር ያሕዌ ነው፡፡ መናፍቃን የሥላሴን አስተምህሮት ፍጹም ስለሚክዱ በአንዱ እግዚአብሔር ባሕርይ ውስጥ ሦስት አካላት
ማለትም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ እንዳሉ ፈጽመው ይቃወማሉ፡፡ ነገር ግን አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ናቸው ስንል አምላካዊ
ተመሳሳይ ባሕርይ አላቸው ማለታችን ነው፡፡ መጽሐፍ ይህን በግልጥ ይመሰክራል፡፡ ለምሳሌ፦
·
በሁሉ ቦታ አብ (1ነገ.8፥27) ፤ ወልድ (ማቴ.28፥20) ፤ መንፈስ ቅዱስ (መዝ.139፥7) ይገኛል
፤
·
አብ ሁሉን ያውቃል (መዝ.147፥5) ፤ ወልድም (ዮሐ.16፥30) ፤ መንፈስ ቅዱስም (1ቆሮ.2፥10)
እንዲሁ፡፡
·
አብ ሁሉን ይችላል (መዝ.135፥6) ፤ ወልድም ሁሉን ይችላል (ማቴ.28፥18) ፤ መንፈስ ቅዱስም
እንዲሁ፡፡ (ሮሜ.15፥19)
·
አብ ዘለዓለማዊ ነው (መዝ.90፥2) ፤ ወልድም ዘለዓለማዊ ነው(ሚክ.5፥2 ፤ ዮሐ.1፥21 ፤ ራእ.1፥18)
፤ መንፈስ ቅዱስም እንዲሁ፡፡(ዕብ.9፥14) ወዘተ
ይህንን አጭር ተዛምዶ እንኳ ያየን እንደሆነ ሦስቱ ፍጹማን አካላት፥
ፍጹም በሆነ መለኮታዊ አንድነት አንድ አምላክ መሆናቸውን መካድ አንችልም፡፡ ነገር ግን ይህን እውነት የሚያስክዱ መናፍቃን ከፊት
ይልቅ ታጥቀው ተነስተዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን “በግል ነገሯ” ላይ በማተኮር የክርስቶስን የመንግሥት ሥራ ችላ ያለች ይመስላል፡፡
የክርስቶስ አልፋነት ሲወለድ ወይም በፍጥረት መፈጠር መጀመርያ የጀመረ
አይደለም፡፡ እርሱ ከጥንት አምላክ ነው፡፡ ከአምላክነት ያነሰ ባሕርይ የለውም ፤ እኛን ለማዳን ራሱን ዝቅ ያደረገው በፈቃዱ ነው
እንጂ አምላክ ስላልሆነ እንዳልሆነ መጽሐፍ “እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት
እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥” (ፊልጵ.2፥6) በማለት በግልጥ አስቀምጦታል፡፡
እንግዲህ ቤተ ክርስቲያን ንቂ! በዙርያሽ እንደአንበሳ የሚያገሳ የሰይጣን
መልዕክተኛ ያገሳልና ፤ ተግተሽ ልጆችሽን ታደጊ፡፡ ስለነዚህ መናፍቃን ሙሉ ትምህርታቸውን በሌላ ጊዜ ሰፋ አድርገን እንዳስሳለን
፤ ላሁን ግን በዚህ ልሰናበት፡፡ የመናፍቃንን ስውር ሴራ በማወቅ እንደብልኅ ሰው እንመላለስ ፤ ጌታ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ
መዋስተዋልን ያብዛልን፡፡ አሜን፡፡
ይህ እውነትና ትክክለኛ መልዕክት ነው፡፡ እንዲህ ያለው እውነትን ነው እኛ የተዋሕዶ ልጆች መስማት የምንፈልገው፡፡
ReplyDeleteWonderful Article. Please keep it up!
ReplyDelete