የኦርቶዶክስ
የት መጣ
“ኦርቶዶክስ” የሚለው ስም ስያሜ ዋና መሠረቱ ትምህርተ ክርስትና [1] ነው፡፡ ቅድመ ኒቂያና ድኅረ ኒቂያ
(pre Nicene) ማለትም፥ ከ300-325 ዓ.ም ገደማ እና ድኅረ ኒቂያ (post Nicene) ከሌሎቹ መናፍቃን ይልቅ አርዮስ
ወልድና መንፈስ ቅዱስ ላይ ጠንካራ የክህደት ትምህርቱን አሰማ፡፡ በ325 ዓ.ም ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ የቤተ ክርስቲያን አባቶች
አርዮስን [2] በክህደቱ ባወገዙበት ወቅት አርዮስን
ያወገዙበትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርታቸውን “ኦርቶዶክስ” ብለው ሰየሙት፡፡
ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት [3]
ይህን ትምህርት ከአርዮስ ክህደትና ምንፍቅና ለመለየት ስያሜውን ሲሰጡ፥ የወልድ ኢየሱስ ክርስቶስን የባሕርይ አምላክነትና ቤዛነት
፤ ፍጥረትንም በፍጹም ሰውነቱና አዳኝነቱ እንዳዳነ ፤ ከአብ ጋርም ተካካይና የማያንስ ፤ የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ በማለት በጽኑ
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት አስቀምጠውታል፡፡ የአርዮስ ትምህርት ጉባኤ ኒቂያ ሲደረግ ሊቃውንቱንና የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ሲደግፍ
የነበረውን ንጉሥ ቆስጠንጢኖስን እስከመገልበጥ የደረሰ ትምህርት መሆኑን አባ ጐርጐርዮስ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ
በሚለው መጽሐፋቸው፥ “ …ቈስጠንጢኖስ አርዮስ ከተሰደደበት እንዲመለስ፥ እስክንድርያ እንዲሄድ፥ ከውግዘት እንዲፈታና ወደቤተ ክርስቲያን
እንዲመለስ በቤተ ክርስቲያን የነበረውም የክህነት ሥልጣን እንዲመለስ አዘዘ ፤ …”በማለት አስቀምጠውታል፡፡ [4] ከዚህም ባሻገር የጉባኤ ኒቂያን
ትምህርትና ውሳኔ የተቃወሙትን ሁለት ኤጲስ ቆጶሳት [5] መወገዛቸውንም ያስቀምጣሉ፡፡
አርዮሳዊነት በዘመኑ ብቻ ሳይሆን መልኩን እየቀያየረ በዚህ በእኛ ዘመንም
ሥር ሰዶ ብቹዎችን ከእውነተኛው ትምህርት ሲያሳስት እናያለን፡፡ ዛሬም በኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ላይ ጆሮ ጭው የሚያደርጉ እልፍ
አዕላፍ የክህደት ትምህርቶች ይሠራጫሉ፡፡ ነገር ግን ክህደቱና ክህደቱን የዘሩት ሁሉ ወደመከሩ ጌታ ፊት ከመቅረብ ሳያመልጡ፥ እውነተኛውና
የተባረከው ተስፋችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፤ ትምህርቱም ግን ለዘላለም ጸንቶ ዛሬም አለ!!! ደግሞም ይኖራል!!! ክብር ይግባው፡፡
አሜን፡፡
በሁለተኛው የቁስጥንጥንያ ጉባኤም መቅዶንዮስ “የመንፈስ ቅዱስን ሕጹጽነት”
ክህደቱን ባስተማረ ጊዜ አንድ መቶ ሃምሳው የቤተ ክርስቲያን አባቶች ትምህርቱን ፍጹም በማውገዝ የመንፈስ ቅዱስን ፍጹም አካላዊነትና
አምላክነት ፤ ከአብና ከወልድ ጋር እኩል አምልኮን የሚቀበል ማኅየዊ መሆኑን መስክረው፥ የመቅዶንዮስን ትምህርት አውግዘዋል፡፡
በሦስተኛውና የኢትዮጲያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመጨረሻ
ብላ በምትቀበለው ጉባኤ ኤፌሶን ላይ “ኤጲስ ቆጶስ” የነበረው ንስጥሮስ “መለኮት ሥጋን አልተዋሃደም” ስለሚለው ክህደቱ በሁለት
መቶ አበው ሊቃውንት ተወግዟል፡፡
እንዲሁም የአትናቴዎስን አንቀጸ ሃይማኖት ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት
[6] ሁሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይቀበሉታል፡፡
ደግሜ ልበል፥ ቅድመ ኬልቄዶን የነበሩ አበው ኦርቶዶክስ የሚለውን ስያሜ አርዮስን ድል ለነሱበት ትምህርታቸው ሰጡ፡፡ ድኅረ ኬልቄዶን
ግን ከትምህርቱ ባሻገር ለተቋሙም ስያሜው እንዲሰጥ ሆነ፡፡ ኦርቶዶክሳዊነት ለቅዱሳን ሐዋርያት ትምህርትና ትውፊት ፤ ለመጽሐፍ ቅዱስም
እውነት ታማኝ መሆንን ብቻ እንዲያመለክት ነበር የተሠየመው፡፡ ጠቅለል አድርገን ስናቀርበው ኦርቶክሳዊው መሠረተ እምነት የተመሠረተባቸው
ዋና ዋና የሃይማኖት አናቅጻት፦
1. የሐዋርያት የእምነት መግለጫ [7]
፤
2. የኒቂያ የእምነት መግለጫ [8]
፤
3. የአትናቴዎስ የእምነት መግለጫ [9] ፤
4. የቁስጥንጥንያ የእምነት መግለጫ
[10]
፤
5. የኤፌሶን የእምነት መግለጫ [11]
ሲሆኑ፥ ከእነዚህ ደግሞ ተውጣጥቶ አከባቢያዊ በሆነ መልኩ የገላውዴዎስ የእምነት መግለጫ ላይ መሠረቱን ጥሎ ኦርቶዶክሳዊነት ተመስርቷል፡፡
[12]
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም ኦርቶዶክሳዊነትን ከሐዋርያትና ከትክክለኛ
አስተምህሮ ጋር እንዲሁም ከኒቂያ ጉባኤ ጋር ፍጹም በማዛመድና በማገናዘብ ተርጉመውታል፡፡ በእርግጥም፥ ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምኅሮ
ጋር ፍጹም ትስስር ያለው የሐዋርያት አመክንዮና [13]
የሦስቱ ጉባኤያት ውሳኔ ኦርቶክሳዊነት የተቀዳበት ዋና ምንጭ ነው፡፡
ታዲያ፥ ኦርቶዶክሳዊነት ከክርስትና ትምህርት የተቀዳ ከሆነ ኦርቶዶክሳዊ
ክርስቲያን አይደለም የሚለው “አዲስና እንግዳ ትምህርት” ከወዴት ተገኘ? እውነት ለመናገር ክርስቶሳዊውን ትምህርት አጽንቶ ለመናገር
“ክርስቲያን” የሚለው ስያሜ ቀጥተኛ ከመሆኑም ባሻገር የሚያሳፍር አልነበረም፡፡ይልቅ ልናፍርበት በየሚገባው ሊታፈርበት በማይገባው
በማፈራችን ነው፡፡
ለኦርቶክሳዊነት ቀዳሚው ነገር የሰው ልጅን ለማዳን የክርስቶስ መሞትና
መነሣቱን የሚያበስረው የወንጌሉ ምሥራች ትምህርት ነው፡፡ እውነተኛውና መሠረታዊው የክርስቶስ ትምህርትና የሐዋርያቱ ምስክርነት ከሌለ
325 ዓ.ም ላይ በኒቂያ የተሰጠው “ኦርቶዶክስ” የሚለው ስያሜ ፈጽሞ ሊኖር አይችልም፡፡ ምህረተ አብ! ይህን እውነት ለምን እንደሚሸሽ
ግልጽ አይደለም፡፡ ኦርቶክሳዊነትን አጉልቶ ክርስትናን ማንኳሸሽ (አይቻልም እንጂ) የኦርቶክሳዊነትን የት መጣ መካድና አለመቀበል
ነው፡፡ ይህ ደግሞ ላላዋቂ እንጂ ለአዋቂ ከተረት የዘለለ ቁም ነገር አይኖረውም፡፡
እኛ እንዲህ እናምናለን ፤ ኦርቶዶክሳዊነት መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ በተለይም
በሐዋርያውያን አበውና በቤተክርስቲያን አባቶች ዘመን ለተነሡ መናፍቃን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መልስ የሰጡና ትምህርት ያስተማሩ ቅዱሳን
አባቶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረትነት ላለው ትምህርታቸው የሰጡት ስያሜ እንጂ ክርስቲያንነትን የሚቃወም ስያሜ አይደለም ፤ ስለዚህም
ከክርስቶስ ትምህርት ያልተቀዳ ክርስትና እንደሌለ ሁሉ ከክርስትና ያልተቀዳ ኦርቶዶክሳዊነትም የለም!!! ካለ፥ ሊመረመር ፤ በታላቁ
መጽሐፍ መነጽርነት ሊዳኝ ይገባዋል እንላለን፡፡ ጌታ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ኦርቶክሳዊት ቤተክርስቲያንን ይጠብቅልን፡፡ አሜን፡፡
ተፈጸመ፡፡
[2] አርዮስ ያስተማረው ትምህርት ስያሜው
አርያኒዝም ሲባል ተከታዮቹ ደግሞ አርዮሳውያን ይባላሉ፡፡ ሰብዓሊዎስነትን ቢቃወምም ነገር ግን ወልድና መንፈስ ቅዱስን ከአብ ጋር
እኩል ነው የሚለውን ትምህርት ሳይቀበል ያልቀረ ነበር ይኸውም ወልድ የራሱ የሆነ አካላዊ ሕልውና እንዳለው ቢቀበልም፥ ወልድ ፍጡር
ሲሆን ፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ኃይል ነው ብሎ ያምን ነበር፡፡ ይህም መንፈስ ቅዱስ አካላዊ ሕልውና ያለው መለኮት አይደለም ማለት
ነው፡፡ አርዮስ ብዙ ጊዜ ትምህርቱ ወደክርስቶስ በሚያደላ ክህደቱ ቢነሣም መንፈስ ቅዱስን በትክክል ክዷል፡ የኒቂያ ጉባኤም በክርስቶስ
በካደው ክህደቱ ላይ በማተኮር ነበር ውግዘቱን ያስተላለፈው፡፡
[3] በጉባኤው የተሰበሰቡትን አባቶች ቁጥር በተመለከተ በታሪክ ጸሐፍት ዘንድ የተለያዩ አሃዞች
አሉ፡፡ ለምሳሌ፦ የቂሣርያው አውሳብዮስ 250 ናቸው ሲል፥ ሶዞሜን 320 ነበሩ ይላል፡፡ ቴዎዶሬት ደግሞ 270፡፡ ከእነዚህ አባቶች
የሚበዙቱ የሮማ አላውያን ነገሥታት በቤተክርስቲያን ላይ ካወጁት መከራና ስደት የተረፉ ከመሆናቸውም ባሻገር ሁሉም ማለት በሚያስደፍር
መልኩ የመከራው ተካፋዮች ነበሩ፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ጸሐፍት ከሊቃውንቱ
መካከል ብዙዎቹ በመከራው ዘመን ከነበረው ሰቆቃ ተካፋይ ከመሆናቸው የተነሣ አካላቸው የጐደሉና የመከራው አሻራ ያረፈባቸው እንደነበሩ
ዘግበዋል፡፡
[7] ሁሉን በሚችል ፣ ሰማይና ምድርን በፈጠረ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን፡፡ በአንድ ልጁም
በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፤ በመንፈስ ቅዱስ የተጸነሰ ፣ ከማርያም ድንግል የተወለደ ፣ በጲላጦስ ጴንጤናዊ ዘመን መከራን የተቀበለ
፣ የተሰቀለ ፣ የሞተ ፣ የተቀበረ ፣ ወደሲዖልም የወረደ በሦስተኛው ቀንም ከሙታን የተነሣ ፣ ወደሰማይም ያረገ ፣ ሁሉን በሚችል
በእግዚአብሔር አብ ቀኝ የተቀመጠ ፣ ከዚያም በሕያዋንና በሙታን ለመፍረድ በሚመለስ እናምናለን፡፡ ደግሞም በመንፈስ ቅዱስ ፣ በአንዲት
ቅድስት ሐዋርያዊት ቤተከርስቲያን ፣ በቅዱሳን አንድነት ፣ በኀጢአትም ስርየት ፣ በሥጋም ትንሣኤ ፣ በዘለዓለምም ሕይወት እናምናለን
፤ አሜን፡፡
2. ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋር በነበረ፥ ቀዳሚና ተከታይ የሌለው የአብ ልጅ
በሚሆን፥ በአንድ ጌታ፥ በኢየሱስ ክርስቶስም እናምናለን፡፡ እርሱም ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፥ ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ፥
የተፈጠረ ያይደለ የተወለደ፥ በመለኮቱ ከአብ ጋር አንድ የሚሆን ነው፡፡ ሁሉ በእርሱ
የሆነ፥ ያለእርሱ ግን በሰማይና በምድር ምንም ምን የሆነ የሌለ ነው፡፡ ስለእኛ ስለሆነች፥ ስለመዳናችንም ከሰማይ ወረደ፡፡ በመንፈስ
ቅዱስ ግብር(አሠራር) ከቅድስት ድንግል ማርያም ፈጽሞ ሰው ሆነ፡፡ ፍጹም ሰው ሆኖ በጴንጤናዊ በጲላጦስ ዘመን ስለእኛ ተሰቀለ ፤
ታመመ ፤ ሞተ ፤ ተቀበረም፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጻፈም በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ በክብር ወደሰማይ ዐረገ
፤ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ፡፡ ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታን ይፈርድ ዘንድ በጌትነት ይመጣል፡፡ ለመንግሥቱም ፍጻሜው የለውም፡፡
3. ከአብ በሠረጸ፥ ከአብና ከወልድ ጋር በአንድነት
በሚሰገድለትና በሚመሰገን ጌታ፥ ሕይወት ሰጪ በሚሆን፥ በነቢያትም በተናገረ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን፡፡
4. በሁሉ ዘንድ ባለች ሐዋርያት በሰበሰቡዋት በአንዲት
ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም እናምናለን፡፡
5. ኅጢአትን ለማስተስረይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን፡፡
6. የሙታንንም መነሣት ተስፋ እናደርጋለን፡፡
7. የሚመጣውንም የዘላለም ሕይወት አሜን፡፡
[9] ለመዳን ፈቃደኛነት ያለው ሰው ሁሉ ይህን በሁሉ ዘንድ ያለችው ቤተ ክርስቲያን የምታመነውን
ሃይማኖት ይጠብቅ ዘንድ ይገባዋል፡፡ ስለዚህም ደኅንነትን እንዳያጣ ይህን እምነት መጠበቅ ያስፈልገዋል፡፡
በሁሉ ዘንድ ያለችው
ቤተ ክርስቲያንም ሃይማኖትም አካላትን ሳትደባልቅና ሕላዌን ሳንከፍል አንዱን አምላክ በሦስትነት ሦስትነትንም በአንድነት እናመልክ
ዘንድ ነው፡፡ አንዱ አካል የአብ ሲሆን ሁለተኛው የወልድ ሦስተኛውም የመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ነገር ግን የአብና የወልድ የመንፈስ
ቅዱስ መለኮት አንዲት ናት፡፡ ክብራቸውም የተስተካከለ ነው፡፡ ግርማቸውም የአንዲት ዘለዓለማዊት ናት፡፡
አብ እንዳለ እንዲሁም
ወልድ አለ መንፈስ ቅዱስም አለ፡፡ አብ አልተፈጠረም ወልድም አልተፈጠረም መንፈስ ቅዱስም አልተፈጠረም፡፡ አብ አይወሰንም ወልድም
አይወሰንም መንፈስ ቅዱስም አይወሰንም፡፡ አብ ዘለዓለማዊ ነው ወልድም ዘለዓለማዊ ነው መንፈስ ቅዱስም ዘለዓለማዊ ነው፡፡ ነገር
ግን በዘላለማዊነት ያለ አንድ ነው እንጂ ሦስት ናቸው አንልም፡፡ እንዲሁም የማንወስነውና ያልተፈጠረ አንድ ነው እንጂ የማንወስናቸውና
ያልተፈጠሩ ሦስት ናቸው አንልም፡፡ እንደዚሁም አብ ሁሉን ቻይ ነው ወልድም ሁሉን ቻይ ነው መንፈስ ቅዱስም ሁሉን ቻይ ነው፡፡ ነገር
ግን ሁሉን የሚችል አንድ ነው እንላለን እንጂ ሦስት ሁሉን ቻዮች አንልም፡፡
እንደዚሁም አብ አምላክ
ነው ወልድም አምላክ ነው መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው ፤ ዳሩ ግን አንድ አምላክ ነው እንጂ ሦስት አማልክት አንልም፡፡ እንዲሁም
አብ ጌታ ነው ወልድም ጌታ ነው መንፈስ ቅዱስም ጌታ ነው ፤ ስለሆነም እንድ ጌታ እንጂ ሦስት ጌቶች አንልም፡፡ በክርስትና እውነትነት
እንደምንለው፦ አካል ሁሉ እያንዳንዱ በየራሱ አምላክና ጌታ ሆኖ ሳለ ሦስት አማልክትና ሦስት ጌቶች ከማለት የሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን
አምልኮ እምነት ትከለክለናለች፡፡
አብ ከማንም አልተሠራም
አልተፈጠረም አልተወለደም ፤ ወልድም በአብ ነው ፤ ስለሆነም ተወልዶ ነው እንጂ ተሠርቶ ወይንም ተፈጥሮ አይደለም፡፡ መንፈስ ቅዱስም
በአብ ነው፤ ዳሩ ግን ሠርጾ እንጂ ተሠርቶ ወይንም ተፈጥሮ ወይም ተወልዶ አይደለም፡፡
እንግዲህ አንድ አብ
አለ እንጂ ሦስት አባቶች የሉም ፤ አንድ ልጅ አለ እንጂ ሦስት ወልዶች የሉም ፤ አንድ መንፈስ ቅዱስ እንጂ ሦስት መንፈስ ቅዱሶች
የሉም፡፡ በዚህችም ሦስትነት መቅደም መከታተል የለም ፤ ከባልንጀራውም የሚበልጥና የሚያንስ የለም፡፡ ሦስቱ አካላት እየራሳቸው የአንዲት
ዘለዓለማዊት ናቸው፡፡ እየራሳቸውም የተተካከሉ ናቸው፡፡ እንግዲያውስ እንደተባለው ሁሉ ሥላሴን በአንድነት አንድነትንም በሥላሴ ማመን
ይገባል፡፡
መዳንን የሚሻ በሥላሴ እንደዚሁ ያስብ፡፡ ዳግም ስለዘለዓለም ሕይወቱ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትሥጉት በሚገባ ያምን
ዘንድ ለሰው ያስፈልገዋል፡፡
ኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖታችን
ስትባል ይህንኑ ማመናችን ማለት እንደመሆንዋ ወልድ እግዚአብሔር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና ሰው ነው፡፡ እምቅድመ ዓለም
ከአብ ህላዌ በመወለዱ አምላክ ነው ፤ ድኅረ ዓለምም ከእናቱ ህላዌ በመወለዱ ሰው ነው፡፡ በሰው ነፍስና ሥጋ ጥዩቅ ሰው ሆኖ ፍጹም
አምላክ ነው፡፡ በመለኮቱም ከአብ ጋር አንድ ሲሆን የባርያውን መልክ ወሰደ፡፡ ዳሩ ግን አምላክና ሰው እንደመሆኑ አንድ ክርስቶስ
ነው እንጂ እርሱ ሁለት አይደለም፡፡ አንድ ሰው ፤ ግን መለኮቱ ሰውነትን በመገንዘብ ነው እንጂ መለኮት ወደሥጋ በመለወጥ አይደለም፡፡
ፈጽሞ ተዋሐደ ፤ ስለሆነ በባሕርይ መደባለቅ ሳይሆን በአካል መዋሐድ ነው፡፡ ነፍስና ሥጋ አንድ ሰው እንደሚሰኝ ሁሉ አምላክና ሰው
የሆነ አንድ ክርስቶስ ነው፡፡
እርሱም እኛን ለማዳን መከራን ተቀበለ ወደሲዖልም ወረደ፡፡ በሦስተኛም ቀን ከሙታን ተለይቶ
ተነሣ፡፡ ወደሰማይም ዐረገ፡፡ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ተቀመጠ ፤ በሕያዋንና በሙታን ለመፍረድም ከዚያ ይመለሳል፡፡
እርሱም በሚመጣበት
ጊዜ ሰው ሁሉ በሥጋው ይነሣል፡፡ ባደረገውም ሥራ ሁሉ ይቈጣጠረዋል፡፡ መልካም የሠሩ ወደዘለዓለም ሕይወት ክፉ የሠሩም ወደዘለዓለም
እሳት ይገባሉ፡፡
ከሁሉ በላይ የምትሆን
የሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ሃይማኖት ይህች ናት ፤ ያላመናት ሰውም ይድን ዘንድ አይቻለውም፡፡ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና
ይሁን ፤ በመጀመርያ እንደነበረ አሁንም እንዳለ ለዘወትርም እንደሚኖር ለዘዓለም አሜን፡፡
[10]
1.. በጌታ፥ በአዳኝ ፥ከአብ በሠረጸ፥ ከአብና ከወልድ ጋር በነቢያት በተናገረ
በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን ፤ እንስገድለት እናመስግነው ፤
2. በሁሉ ባለች በሐዋርያት
ጉባኤ ፥ ባንዲት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን ፤
3. ለኃጢአት ማስተሥረያ
ባንዲት ጥምቀት እናምናለን ፤
4. የሙታን ትንሣኤን
ተስፋ እናደርጋለን ፤
5. የሚመጣውን ሕይወት
እንጠባበቃለን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
[11] የኤፌሶን ጉባኤ ቀኖናዎችን የደነገገና በዋናነት በኒቂያ ጉባኤ ላይ ምንም አይነት ንባብ
እንዳይጨመርና እንዳይቀነሱ ወስኗል፡፡
[12] ብዙዎች ይህን የገላውዴዎስን አንቀጸ ሃይማኖት በትክክል መደንገጉን አያውቁትም፡፡
ይህ ግን መሠረተ እምነትንና ቀኖናን ማዕከል ያደረገ “ምርጥ” አንቀጽ ነው፡፡ ይኸውም እንዲህ ይላል፦ “እኛ በአንድ አምላክና የእርሱ ቃል፥ ኃይሉ፥ ምክሩ ፥ ጥበቡም በሆነ ዓለም ሳይፈጠር
በእርሱ ዘንድ በነበረው በአንድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን፡፡ እርሱም ከአምላክነቱ መኖርያ ተለይቶ ሳይቀር በኋለኛው ዘመን
ወደእኛ መጣ፡፡ “ከመንፈስ ቅዱስ ግብር የተነሳ”(በራስ የተሻሻለ) ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሆነ፡፡ በሠላሳኛው ዓመት በዮርዳኖስ
ተጠመቀ፤ ፍጹም ሰው ሆነ፡፡ በጰንጤናዊ በጲላጦስ ዘመን በእንጨት መስቀል ላይ ተሰቀለ፡፡ መከራን ተቀበለ ፥ ሞተ ፥ ተቀበረ ፥
በሦስተኛውም ዕለት ተነሣ፡፡
ከዓርባ ቀን በኋላ በክብር ወደሰማይ ዐረገ ፤ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ፡፡ በሕያዋንና
በሙታን እንዲፈርድ ዳግመኛ በክብር ይመጣል፤ ለመንግስቱም ፍጻሜ የለውም፡፡ ከአብ በሠረጸ፥ ሕያው በሚያደርግ ጌታ ፥በመንፈስ ቅዱስም
እናምናለን፡፡ ለኃጢአት ሥርየት በምትሆን በአንዲት ጥምቀት እናምናለን፡፡ ለዘለዓለማዊ ሕይወት የሚነሡበትን የሙታንን ትንሳኤ በተስፋ
እንጠባበቃለን ፤ አሜን፡፡
እኛስ ቅንና እውነተኛ በሆነ በንጉሣዊ መንገድ እንመላለሳለን፡፡ ከአባቶቻችን
ትምህርት ወደቀኝ ሆነ ወደግራ ዘንበል አንልም፡፡ አባቶቻችንም ፥
አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት፣ የጥበብ ምንጭ ጳውሎስ፣ ሰባ ሁለቱ አርድእት፣ በኒቂያ የተሰበሰቡ ፥ የቀናውን ሃይማኖት የያዙ
ሦስት መቶ አስራ ስምንቱ፣ በቁስጥንጥንያ የነበሩ መቶ ኀምሳው፣
በኤፌሶን የነበሩ ሁለት መቶው ናቸው፡፡ በንግሥ ስሜ አጽናፍ ሰገድ ወልደ ወናግ ሰገድ ወልደ ናዖድ ተብዬ የተጠራሁ የኢትዮጲያ ንጉሥ
እኔ ገላውዴዎስ እንዲህ እሰብካለሁ፤ እንዲሁም ብዬ አስተምራለሁ፡፡
ሰንበት የተባለውን
መጀመርያ ቀን ስለማክበራችን “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን”(ማቴ. ፳፯ ፡ ቍ. ፳፭) ብለው ክርስቶስን እንደሰቀሉት እንደአይሁድ
አናከብረውም፡፡ እነዚያ አይሁድ፤ ውሃ አይቀዱም፣ እሳትን አያነዱም፣ ወጥን አያበስሉም፣ ዳቦን አይጋግሩም፣ ከቤት ወደቤት አይመላለሱም፡፡
ነገር ግን አባቶቻችን ሐዋርያት በመጽሐፈ ዲድስቅልያ እንዳዘዙን እኛ ቅዳሴን በመቀደስና
ግብር(ማእድ) በመሥራት ነው፡፡ የምናከብራት እንደእሁድ ሰንበት አይደለም፤ ይህችውም ዳዊት ስለእርሷ፣ “እግዚአብሔር የሠራው ቀን
ይህ ነው፣ በእርሱ ደስ ይበለን፣ ሐሴትን እናድርግ” ብሎ ስለእርሱ ተናገረ (መዝ. ፻፲፯ ቍ. ፳፩) በዚህ ቀን ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ተነሣ፡፡ በዚህ ቀን መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ ወረደ፡፡ በዚህም ቀን ዘወትር ድንግል በሆነች በቅድስት ድንግል ማርያም
ማሕፀን ውስጥ ሰው ሆነ፡፡ በዚህ ቀን ለጻድቃን ሽልማት ኃጥአንን ውርደት (ፍዳ) ሊሰጥ ዳግመኛ ይመጣልና ስለዚህ ነው፡፡
ስለግዝረት ሥርዓት
እንደአይሁድ አንገዝርም፡፡ እኛ የጥበብ ምንጭ የጳውሎስን ትምህርት እናውቃለንና፤ “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን የሆነ አዲስ
ፍጥረት እንጂ መገረዝ አይጠቅምም፥ አለመገረዝ ፍጹም አያደርግም፡፡” አለ፡፡ (ገላ. ፭ ቍ.፮ ም.፮ ቍ. ፲፭) ደግሞም ለቆሮንቶስ ሰዎች “ግዝረትን የተቀበለ ቍልፈትን አይያዝ” አለ (፩ቆሮ.
፯ ቍ ፲፰ ፥ ተገዛሪ ወደአለመገረዝ አይመለስ)፡፡ የጳውሎስ ትምህርት
መጽሐፍ ሁሉ በእኛ ዘንድ አለና ስለግዝረት፥ ስለቍልፈትም ያስተምረናል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጲያም እንደኖብያም ሰው ፊቱን እንደሚበጣና
የህንድ ሰው ጆሮውን እንደሚበሳ በእኛ ዘንድ ግዝረት እንደአገር ልማድ ነው፡፡ ይህን ስየምናደርገው በሰው ልማድ ነው እንጂ የኦሪትን
ሕጎች በመጠበቅ አይደለም፡፡
አሳማን ስለመብላት
እንደአይሁድ ሆነን የኦሪትን ህጎች በመጠበቅ አንከለክለውም፡፡ የበላውን አንጠየፈውም፣ ርኩስ ሆኖ አናየውም፤ የማይበላውንም ብላ
ብለን አናስገድደውም፡፡ አባታችን ጳውሎስ ለሮም ሰዎች እንደጻፈው፣ “እግዚአብሔር ሁላቸውን ተቀብሎአቸዋልና የሚበላ የማይበላውን
አይናቀው፤ የእግዚአብሔር መንግስት በመብልና በመጠጥ አይደለም፡፡ ለንጹሖች ሁሉ ንጹሕ ነው፤ በመሰነካከል መብላት ግን ለሰው ክፉ
ነው” (ሮሜ. ፲፬ ቍ. ፫-፲፯ ቲቶ. ፩ ቍ. ፲፭ ፩ቆሮ.፰ ቍ. ፱-፲፫)፡፡ ደግሞም ማቴዎስ ወንጌላዊ እንዲህ አለ “ከአፍ ከሚወጣ
ነገር በቀር ሰውን የሚችል የለም፡፡ በአፍ ውስጥ ያለው ወደሆድ ይገባል፥ በፀጥታ ይከተታል ፥ ይወድቃልና ይፈስሳል” (ማቴ.፩፭
ቍ. ፲፩-፲፯) መብልንም ሁሉ አነጻው፡፡(ማር. ፯ ቍ.፲፭) ይህን ቃል በመንገሩ አይሁድ ከመጽሐፈ ኦሪት የተማሩትን የስህተታቸውን
ሕንፃ አፈረሰው፡፡
ይህ የእኔ ሃይማኖትና በመንግስቴ በረት ውስጥ ያሉ በትእዛዜ የሚያስተምሩ የተማሩ ካህናት
ሃይማኖት ነው፡፡ ከወንጌል መንገድና ከጳውሎስም ትምህርት ወደቀኝ ሆነ ወደግራ ፈቀቅ አይሉም፡፡
በመጽሐፈ ታሪክ
በመጽሐፋችን ውስጥ ፥ እንዲህ ሲል የተጻፈ አለ፤ “የተጠመቁት አይሁድ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በዓል የአሳማን
ሥጋ እንዲበሉት ንጉሡ ቆስጠንጢኖስ በዘመነ መንግስቱ አዘዘ፡፡” ነገር ግን ሰው እንደልቡ አምሮት የእንሰሳን ሥጋ ከመብላት ይለያል፤
የዓሣን ሥጋየ ሚወድ አለ፣ የዶሮ ሥጋን መብላት የሚወድ አለ፣ የበግ ሥጋን ከመብላት የሚለይ አለ፡፡ የሰው ውዴታና ፈቃድ እንደዚህ
ነውና እንደልቡ አምሮት የሚወደውን ሁሉ ይከተል፡፡ የእንሰሳት ሥጋ ስለመብላት ህግ የለም፡፡ በአዲስ መጽሐፍም ውስጥ ትእዛዝ የለም፡፡
ለንጹሖች ሁሉ ንጹሕ ነው፡፡ ጳውሎስም፣ “የሚያምን ሁሉን ይብላ” አለ፡፡(ሮሜ. ፲፬ ቍ. ፳፪-፳፫)
የሃይማኖቴን
እውነተኛነት እንድታውቅ ይህን ሁሉ ለመጻፍ ተጋሁ፡፡ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በ፩ሺህ፭፻፶፭ ዓመት ዳሞት በሚባል አገር
በሠኔ ፳፫ ቀንተጻፈ፡፡ (ጽድቀ ሃይማኖት፤ ገጽ 78-81)
(አቡነ
ጎርጎርዮስ (ሊቀጳጳስ) ፡፡ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ
ክርስቲያን ታሪክ፡፡ 3ኛ ዕትም (1991 ዓ.ም) ገጽ.150)
Menfekena Menfekena Yeshetal Tsehufeh.
ReplyDeleteወዳጄ፣ይሄ፣እኮ፣ከነምህረተአብ፣ጋር፣የዘመኑ፣ነጋዴ፣ነው፣የማህበረቅዱሳን፣ደግሞ፣አካፍይ፣አጉርሰኝ፣ላጉርስህ፣ቤተክርስቲያናችን፣ለነዚህ፣ወሮ፣በሎች፣እንኳ፣ተላልፋ፣ተሰጥታለች፣የሚታደጋት፣አባትም፣ጠፋ፣ለምን፣ሁሉም፣ክብሩን፣ፈሌጊ፣ነው፣የማነቃቂያ፣የቢዝነስ፣ደወል፣ከተደወለ፣ቆይተዋል፣አባቶችም፣አልነቁም፣እነሱም፣አልጠገቡም
ReplyDelete