ከማይጠፋ ዘር ተወልደን ወንድማማች
የሆንበት ምስጢር
ጌታ ኢየሱስ ከባሕርይ
አባቱ ከአብ የተወለደ ፍጹም ልጅ ነው፡፡ በእርሱ ልጅነት እኛ ደግሞ ልጆች ተብለናል፡፡ በዓመጽና ባለመታዘዝ ፊተኛው አዳም የእግዚአብሔር
ልጅነትን ሲያጣ ሁለተኛው አዳም እግዚአብሔር ወልድ እንደልጅ ፍጹም በመታዘዝ (ዕብ.5፥8) ሁላችን ለእግዚአብሔር ልጆች እንሆን
ዘንድ እርሱ በኵር ሆነ፡፡ እኛ ወደአባቱና ወደእርሱ ክብር የምንገባው የእርሱን “አማኑኤልነት” አብነት አድርገን ነው፡፡ የቀደመው
አዳም ከኃጢአት የተነሳ ለሞት ወልዶን ነበርና፡፡
ከማይጠፋ ዘር ስለመወለድ
ወይም ስለዳግም ልደት ስንናገር በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መፈጠርን ወይም ፍጹም መለወጥን የሚያሳይ ነው፡፡ መፈጠር የሚለው ቃል
አዲስ ማንነትን ማግኘትን ያሳያል ፤ ከዚህም የተነሣ ከእግዚአብሔር የሆነ የዘላለም ሕይወት ሠርጾ በአማኙ ልብ ውስጥ ይገባል፡፡
(ዮሐ.3፥16 ፤ 2ጴጥ.1፥4 ፤ 1ዮሐ.5፥11) አማኙም በእምነት ጌታ ኢየሱስን ተቀብሎታልና ፍጹም የእግዚአብሔር ልጅ ይሆናል
(ዮሐ.1፥12 ፤ ሮሜ.8፥16 ፤ ገላ.3፥26) ፤ አዲስ ሰውነትን (2ቆሮ.5፥17 ፤ ቈላ.3፥9) የዘላለም ሕይወት (1ዮሐ.5፥20)
ያገኛል፡፡
አማኙ እንዲህ
ባለ ክብር ሲከብር ዓለምንና በውስጧም በመካድ (ቲቶ.2፥12-13) ፣ ባለመምሰል (ሮሜ.12፥2) ፣ ከኃጢአቱም ንስሐ በመግባትና
ወደእግዚአብሔር በመመለስ (ማቴ.3፥2) ፣ የጌታን አዳኝነትና ጌትነት አምኖ ሲቀበል (ዮሐ.1፥12) የዚያን ጊዜ ዳግም መወለዱን
መንፈሱ ከመንፈሱ ጋር በአንድነት ይመሰክርለታል፡፡
ይህ እውነትና ቅዱስ ምስጢር ካልገባን በቀር ጌታ የተናገረው ፈጽሞ ሊገባን አይችልም፡፡
በአንድ ወቅት ጌታችን ሲያስተምር ሰዎች ያስተምር የነበረውን እንዲያቋርጥ በሚያደርግ መንፈስ፥ “አንዱም፦ እነሆ፥
እናትህና ወንድሞችህ ሊነጋገሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል …” (ማቴ.12፥47)
ባሉት ጊዜ እርሱ፥ “... እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው? ... ብሎ እጁንም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘርግቶ፦
እነሆ እናቴና ወንድሞቼ ፤ በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ እኅቴም እናቴም ነውና አለ።”
(48-50) ወንድም መቅረብንና ፍጹም ከመደማመጥ ጋር ያለ መታዘዝን የሚያሳይ ነው፡፡
ይህን የጌታ ንግግር ሐዋርያት የመጀመርያ ስብከታቸውን እንደሰበኩና ከይሁዲነት
የተመለሱት ሦስት ሺህ አማኞች ገና ፊታቸውን ወደጌታ ዘወር እንዳደረጉ የተናገሩት ቃል፥ “ወንድሞች ሆይ፥ ምን እናድርግ?” (ሐዋ.2፥37)
የሚል ነበር፡፡ ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሳነብ እጅግ የሚደንቀኝ ነገር፥ ቅዱስ ጴጥሮስ እንዴት አድርጎ ቢያቀርብ ነው እኒህ
የመጀመርያዎቹ ደቀ መዛሙርት ሐዋርያትን “ወንድሞቼ” እስከማለት የበቁት? እውነት ለመናገር ወንጌልን እዚህ ድረስ ዝቅ ብሎ ማቅረብና
ማገልገል ብርቱ የመንፈስ ቅዱስ እገዛ ይፈልጋል፡፡ ወንጌል የሚያዘጋጀው ትውልድ ሁለ ነገሩ አዲስ ነው፡፡
ይህ አዲሱ ማኅበረሰብ ሰማያዊ ጥሪ ያለው (ዕብ.3፥1) ፤ ከዓለም ርኩሰትና
ከጨለማ ጋር ፈጽሞ የማይጋጠም (2ቆሮ.6፥16) ፤ በክርስቶስ ደም የተቤዠ (ኤፌ.1፥7) ፣ በጌታ ኢየሱስ በማመን ዳግመኛ በመወለድ
አዲስ ፍጥረት የሆነ (ዮሐ.፥16 ፤ 20፥31 ፤ ኤፌ.2፥14) “በደሙም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ
ከሕዝብም ሁሉ ያመኑትን ዋጅቶ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ ያደረጋቸው” (ራእ.5፥8) ድንቅ ማኅበረሰብ ነው፡፡
እንዲህ ያሉት፥ “ያመኑትም ሁሉ አብረው ነበሩ፤ … በየቀኑም በአንድ ልብ ሆነው በመቅደስ ይተጉ” ነበር የተባለላቸው ናቸው፡፡
(ሐዋ.2፥44 ፤ 46) በእርግጥም አንድ መንፈስ የጠጣን ፣ አንድ አካል የሆንን ፤ ቅዱስ ሕዝብ ፤ የተለየ ወገን ነን፡፡ (1ጴጥ.2፥9)
ስለዚህም በምንም አይነት በክርስቶስ ቤተ ሰዎች መካከል የዘር ፣ የወገን
፣ የብሔርና የጎሳ ፣ የደረጃና የጾታ ልዩነት ሊኖር ፤ ይህን መሠረት
አድርጎ መከፋፈል ደሙን የሚያክፋፋ ከባድ ኃጢአት ነው፡፡ ምክንያቱም ሁላችን የእግዚአብሔር ልጆች (ገላ.3፥26 ፤ ቲቶ.3፥5)
የሆንንና አንድ ጌታ ፣ አንድ መንግሥት ፣ አንድ አገርና ከተማ ያለን ነንና፡፡ (ፊልጵ.3፥20 ፤ ራእ.5፥9)
ያመንን ሁላችን የበኵራት ማኅበር (ዕብ.12፥23) ከሆንን “ሁሉን ወራሽ”
(ዕብ.1፥2) ከሆነው ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አብረን ወራሾች ነን፡፡ ጌታ ኢየሱስ በኵር ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት መጀመርያ የምናምነው
ሁላችን እርሱን እንከተለዋለን ፤ በሚኖርበት በዚያ እንኖራለንና፡፡ (ሮሜ.8፥29 ፤ ቈላ.1፥15 ፤ ዕብ.1፥6) የእግዚአብሔርን
መንግሥት የምንወርሰው በእርሱ ብኵርና፥ “እኛም የበኵር ልጆቹ” ሆነን ነው፡፡ እናም፥ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጌታችን ደም የተነሣ
“አንድ አካል አንድ አምሳል” የሆንን ፍጹም የአንዱ የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች ወንድማማቾች ነን፡፡ ይህን ሳስብ ዛሬ ግን በአለም
አቀፉ የአብያተ ክርስቲያናት ሕብረት አንድ የሆኑት ወንድሞቻችንን ወደየአገራችን ስንመለስ ለምን እንደምንገፋቸውና መጽሐፍ ቅዱስን ከሚቃወሙ ጋር ራሳችንን
ማቀራረባችንን ሳስብ፥ ለመጽሐፍ ቅዱሱ ወንድማማችነት ባዕዳን መሆናችንን ያስተዋልነው አይመስለኝም፡፡
ሌላው የራስን ዘርና ወገን ፤ ቋንቋ ተናጋሪ ፣ ጎሳና አጥንት እየቆጠሩ ፣
ወንዝና ድንበር እያካለሉ ክርስትናን ኖሬበታለሁ ፤ አውቀዋለሁ ብሎ ቃሉን ለመጥቀስ መነሣት በክርስቶስ ላይ እጅግ መዘበት ነው፡፡
ዛሬ በመንፈሳዊው አለም ከሚሠሩት ታላላቅ ኃጢአቶች መካከል አንዱ ዘረኝነት ትልቁን ሥፍራ ይይዛል፡፡ ብናውቅስ ቢሆን የክርስቶስ
ልብ ቢኖረን ሁሉን የምናውቀው በክርስቶስ ልብና በክርስቶስ ልጅነቱ ብቻ ነበር፡፡
ነገር ግን በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉት ሁሉ ለእኛ ወንድሞቻችን ናቸው፡፡
ከየትኛውም ዘር ፣ ነገድ ፣ ቋንቋ ፣ ብሔር ቢመጡ ፤ የትኛውም የትምህርት ደረጃ ፣ ቀለም አገር ፣ ቆዳ ፣ ጾታ ፣ ሃብት ፣ ዝና
፣ ክብር … ቢኖራቸው እንዳችን ከሌላችን የማንበላለጥ ወንድማማች ነን፡፡ የክርስቶስ ደም አስተሳስሮን ከማይጠፋ ዘር ልንወለድ ምክንያት
ሆኖናልና ፍጹም ወንድማማች ነን፡፡ ለዚህም ነው በእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች መካከል ባለ ፍቅርና ፍጹም እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማች
መዋደድ ፦
†
እርስ በእርስ (ሮሜ.12፥9 ፤ 1ተሰ.4፥9 ፤ ዕብ.13፥1) ፤
†
ያለግብዝነት (ሮሜ.12፥10 ፤ 1ጴጥ.1፥22) ፤
†
ፍቅርን በመጨመር (2ጴጥ.1፥7) ልንዋደድ እንደሚገባን ቃሉ የሚነግረን፡፡
ከዚህ መንፈሳዊ እውነት ተነሥተን “ወንድሜ ማን ነው?” የሚለውን ጥያቄ
የእግዚአብሔር ቃል መሠረት በማድረግ መልስ ብናገኝለት ፤ ወንድሜ፦
1.
ከማይጠፋ ዘር ከመንፈስ ቅዱስ አብራክ የተወለደው ሁሉ ወንድሜ ነው፡፡
የፊተኛው ዘርና ማንነት በዚህኛው ሙሉ ለሙሉ የተሻረ ይሆናል፡፡ በእርግጥ ከአንድ ማኅጸን የሚወለዱ ሁሉ ወንድማማች እንዳልሆኑ ነባራዊው
ዓለም ሳያፍር የሚነግረን ነውራዊ ምስክርነት አለው፡፡
2.
ጌታ እንደነገረን የአባት እግዚአብሔርን ቅዱስ ፈቃድ የሚፈጽሙ ሁሉ እነርሱ
ወንድሞች ናቸው፡፡ ለአንድ መንግሥትና ለአንዲት ሰማያዊት አገር ይምሠራ
ነንና በእርግጥም ለእርሱ በመታዘዝና ፤ ቃሉን በመፈጸም ፍጹም ወንድማማቾች ነን፡፡
3.
በአምልኮ ጊዜ ስሙ በተጠራበት በዚያ በአንድነት ነፍሱ ከነፍሴ የተሳሰረችው
ያ ወንድም ወንድሜ ነው፡፡ “ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።” (ማቴ.18፥20) የሚለው
ቃል ምንን ይሆን የሚያሳየው? በፍጹም መስማማት ያለን ወንድማማችነት አይደለም? እግዚአብሔር እንዲህ ልጆቹ አንድ ሲሆኑለት እጅግ
ደስ ይለዋል፡፡
ስናጠቃልለው ወንድሜ ፦
†
እንደቃየን የማይጠብቀኝና ለእኔ
ግድ የማይለው አይደለም ፤
†
እንደይሁዳ ለሕይወቴ ዋስ የሚሆንና
በነፍሱ የሚወራረድልኝ እርሱ ፍጹም ወንድሜ ነው፡፡
እንደጌታ ትምህርት
ደግሞ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በቅን ልብ የሚፈጽም እርሱ ከሁሉ ይልቅ ደግሞ ወንድሜ ነው፡፡ዘርና ቋንቋ ፤ የእናት ማኅጸንና እትብት
አንድ ካደረገው ይልቅ ይህ ትምህርትና እውነት አንድ ያደረገው የዘለዓለም ወንድምነት ፍጹም ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ወንድሞች እንዲበዙልን
ጌታን በፍጹም ምልጃ እንማልደዋለን፡፡ አዎን! ጌታ ሆይ እንዲህ ያለውን ወንድማማችነት አብዛልን፡፡ አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment