Monday 27 July 2015

“መለከት ድራማ”ና የመጽሐፍ ቅዱስ ይትበሐልን አጠቃቀሙ



                                                    Please read in PDF

“ምነው የ“ጥበብ” መንገድን ከፈጣሪ ቃል ጋር ካልተዘባበታችሁ በ“ጥበብነቷ” ብቻ ማሳየት አይቻላችሁምን? ስለምንስ የማሰናከያን ድንጋይ በትውልድ መንገድ  ላይ  ታስቀምጣላችሁ?”

     “መለከት” ድራማ በተከታታይነት በኢትዮጲያ ብሮድ ካስት ቴሌቪዥን በእሁድ መዝናኛ ፕሮግራም ይቀርባል፡፡  እንደመታደል ጊዜ ሰጥቶ ብዙም ድራማን የመከታተል ልማድ የለኝም ፤ ድንገት ግን እግረ መንገድ ከመጣ አያለሁ፡፡ በተለይ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስንና ጌታዬ ክርስቶስን “የሚዳስስ”ና በዚህም ዙርያ በአሉታዊም ሆነ በአዎንታዊ መልኩ የሚንጸባረቅ ከሆነ ትኩረቴን አሳርፍበታለሁ፡፡ እናም “መለከት”ን እንደዋዛ አየሁት ፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ይትበሐልን በአንዱ ተዋናይ አማካይነት ሲጠቀም አየሁትና በማስተዋል አጤንኩት ፥ ከዚያም ሁለት ነገርን ከውስጡ እንዲህ አስተውዬዋለሁ፡፡


      መጽሐፍ ቅዱስ እንደሌሎች መጻሕፍት ያይደለ ራሱን ለትችት በማጋለጡ ምንም የማይፈራ ቅዱስ መጽሐፍ ነው፡፡ ለዘመናት መጽሐፍ ቅዱስ “በቃን ፤ ነቃን ፤ ሰለጠን ፤ አወቅን” ባሉት “ልሂቃንና ምሁራን” እልፍ አዕላፍ ጊዜ በአሉታዊነቱ ቢተችም ፤ በ19ኛውና በ20ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ የነበሩት የፍልስፍናው ዓለም ነቢያትም “መጽሐፍ ቅዱስ ከእንግዲህ የመነበቢያው ጊዜ አልፏል” ቢሉም ፥ እነርሱ “ትንቢቱ”ን በተናገሩ ማግስት  “Guinness book of world record” 1988 እ.አ.አ እትም ዘገባው ከ1815-1975 እ.አ.አ ባሉት ዓመታት ውስጥ 2‚500‚000‚000 (ሁለት ቢሊየን አምስት መቶ ሚሊየን) የእንግሊዝኛ ኮፒዎችን በመባዛትና ለዓለም ሕዝብ በመሰራጨት ተወዳዳሪ ያልተገኘለት መሆኑን አስፍሮታል፡፡ ታዲያ! እኒያ “ነቢያት” እንኳንም ትንቢት ተናገሩ አያሰኝም!?
       መለከትን በተመለከተ ላነሳ የምችለው አዎንታዊ ጎን (አዎንታዊ ሆኖ ከተቆጠረ) ቀጥታ ባልሆነ መልኩና በአስተማሪነት ጎኑ የመጽሐፍ ቅዱስን ይትበሐልን አለመጠቀሙ ነው፡፡ ምክንያቱም ወንጌል ብዙ ጊዜ በአዎንታዊ ጎኑ ብቻ ላይሰበክ ይችላልና፡፡ መጽሐፍ ፦

“ … አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር እንኳ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብኩታል፤ እነዚህ ወንጌልን መመከቻ ለማድረግ እንደ ተሾምሁ አውቀው በፍቅር ይሰብካሉ ፥ እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ መከራን ሊያመጡብኝ መስሎአቸው ፥ ለወገናቸው የሚጠቅም ፈልገው በቅን አሳብ ሳይሆኑ ስለ ክርስቶስ ያወራሉ። ምን አለ? ቢሆንም በሁሉ ጎዳና፥ በማመካኘት ቢሆን ወይም በቅንነት ቢሆን፥ ክርስቶስ ይሰበካል ስለዚህም ደስ ብሎኛል።” (ፊልጵ.1፥15-18)

      ለሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መታሠር ዋናው ምክንያት የማያመቻምቸው የወንጌል ጠንካራ አቋሙና ለዚያም የጨከነ ብርቱ መሆኑ እንጂ ወንጀል ሠርቶ እንዳልሆነ  እርሱን በሚያውቁትና ወንጌልን እንደእርሱ አምነው ጨክነው የሚመሰክሩቱ ሰዎች ሁሉ ዘንድ ግልጽ ነበር፡፡ ይህ እንዲህ ቢሆንም ሌሎች ግን ወንጌልን ይሰብኩ የነበረው በሁለት መልኩ ነበር፡፡ አንደኛው ወገኖች፦ በጎ ተነሣሥቶት ባይኖራቸውም  ከእርሱ ጋር በመፎካከር ወንጌልን ይሰብካሉ ፤ ሌሎቹ ደግሞ የጳውሎስን ለእውነት ወንጌል ምስክርነት መታሠር የሚያውቁና በዚሁም እርሱ ላይ እስር እንዲጸናበት ፤ ከእስር እንዳያመልጥ ለማድረግ፡፡

     ከዚህ የተነሳን እንደሆን፥ ወንጌል በሁለት መልኩ እንደሚሰበክ እናምናለን ፤ በአሉታዊና በአዎንታዊ መልኩ፡፡ ምናልባት የ“መለከት ድራማ ፈጣሪዎች” የፈጣሪ እግዚአብሔርን ቃል ለሌሎች እንዲደርስ ከሐሰተኝነት ልብ ጸድተው ፥ ከቅንነት ልብ የተነሣ እንዲህ አድርገውት ከሆነ ፥ እጅጉን የተወደደ መልካም ነገር ነው፡፡ በእርግጥም ቃሉን አዎንታዊ ባልሆነ መንገድ ማስተማርም አንዱ “የስብከት ዘዴ መገለጫ” ነውና፡፡ ቅዱስ ጳውሎስን ስለወንጌል የታሰረውን እስራቱን ለማጽናት ወይም ለማሳሰር ሐሰትን ያይደለ ያንኑ የእውነት ወንጌል የሚሰብኩ ሰዎችም ነበሩና፡፡ እንዲህ  በቅንነት ልብ አስባችሁ ካደረጋችሁት እጅግ ደስ ይለናል!!! ግና በማስተዋል ላየው ነገረ ሥራችሁ እንዲህ አይመስልም!?
      ሁለተኛውና አደገኛው ነገር ግን ፥ ሰዎች ለወንጌሉ ቃል ካለመታዘዝ አልፈው በቃሉ ወደማሾፍ ክፉ ልምምድ ውስጥ እንዲገቡ ለማድረግ የማሰናከያን ድንጋይ ከማኖር አንጻር ከተደረገ ፥ አብዝተን በጌታ ጉልበት እንቃወማለን፡፡ እንዳለመታደል በእግዚአብሔርና በቃሉ ፤ በስሙም የሚያሾፉ “ክርስቲያን አርቲስቶችን” ማየት ከጀመርን ውለን አድረናል፡፡ በአንድ ወቅት “ማይ ክርስቶስ (በትክክል ካልጠራሁ ይቅርታ) ፤ የተጨቆኑ ቀልዶች” በሚሉ ርዕሶች ድራማና አጫጭር ስታንድ አፕ ኮመዲዮች ላይ በግልጥ ይደረጉ የነበሩ የድፍረት ሹፈቶችን አስተውለናል፡፡ እንዲሁ ጌታ የተናገራቸውንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተቀመጡትን ግልጽ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችን በድራማ ንግግር ውስጥ አስገብቶ የድራማው ክፍል (ያውም የሹፈትና የፌዝ ንግግሮች አካል) ማድረግ ሊወገዝና እንዳይደገም በብርቱ መሠራት ያለበት ነገር ነው የሚል እምነት አለን፡፡ምሳ.10፥23
      ትላንት የነበረው አልቦ እግዚአብሔር ባይ ትውልድ ራሱን “እውነት ሁኔታዊ ናት” ወደሚል አመክንዮ አሸጋግሯል፡፡ ለዚህም እንደዋናነት መገለጫ መጽሐፍ ቅዱስንና ንግግሮቹን ከሌሎች መጻሕፍትና ንግግሮች ጋር በግድ ለማመሳሰልና ክብሩን ዝቅ ለማድረግ (አይቻልም እንጂ ቢሆንላቸው) የሚደረገው ጥረት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ብዙዎች ለቀልዳቸው ማጣፈጫ የእግዚአብሔር ቃል ሲጠቀሙበት እንደማየት የሚያም ነገር የለም፡፡ “ለልጆችህም አስተምረው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም ተጫወተው።” (ዘዳግ.6፥7) እንዲል ቃሉን ለመጨዋወት መንፈሳዊ ልብና ፍርሃት ከእኛ ጋር ሊሆን ግድ ነው፡፡
      በመለኮት እስትንፋስ የተነገረውን ቃል በፌዝና በስላቅ መካከል ማንሣት የቃሉን ተናጋሪ ባለሥልጣንነት መናቅና መዳፈር ነው፡፡ አንዳንዶች የእግዚአብሔርን ቃል ለኃጢአታቸው ድጋፍ እስከመጥቀስ የደረሱበት አንዱ የክፋት “ጥበብ” ይህ ነው፡፡ ዘፋኞች ፣ ጉበኞች ፣ አጭበርባሪ ነጋዴዎች ፣ የቲያትርና የፊልም አብዛኛዎቹ ደራሲና ዳይሬክተሮች ፣ በዝሙት ፊልም የተካኑ አርቲስቶችና ሌሎችም ለኃጢአታቸው መሸፈኛነት በዋናነት የእግዚአብሔርን ቃል በመጥቀስና በማውራት የታወቁ ናቸው፡፡ መቼም ኃጢአት ፥ ኃጢአት እንጂ ሌላ የዳቦ ስም የለውም፡፡ እግዚአብሔር ድምጽን እንጂ የዘፈንን መንፈስ ፣ ሥልጣን እንጂ በስግብግብነት ገንዘብን መሰብሰብ ፣ ንግድን እንጂ ማጭበርበርናን ሚዛን መስለብን ፣ የቲያትርና የፊልም ጥበብን እንጂ ለዝሙትና ለክፋት መንገድ … ማዋያነት ፈጽሞ አልሰጠንም፡፡ “መለከት ድራማ አስተማሪ ነኝ” ካለ አስተማሪነቱን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግሮችን ለማሾፊያነት ከመጠቀምን ተቆጥቦ ፤ ብዙ የጥበብ መንገድን በመከተልና በማሳየት መሆን እንዳለበት እናምናለን፡፡  
  ጌታ ሆይ! ማስተዋልን ለባርያዎችህ አብዛልን፡፡ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment