Thursday, 9 July 2015

ሐዲስ ሕይወት



                                                 Please read in PDF



ምንጭ ፦ ቴዎፍሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ዘኢትዮጲያ መልእክት ፤ ፩ኛ አመት የፓትርያርክነት በዓለ ሢመት መጽሔት ፤ ግንቦት ፩ ቀን ፲፱፻፷፬ ዓ.ም ፤ ገጽ ፯- ፱፡፡

     ሰላም ለክሙ ወጸጋ እግዚአብሔር አቡነ ወእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘአፍቀረነ ወሐደሰ ለነ ፍኖተ ሕይወት በመንጦላዕተ ሥጋሁ ከመ ናንሶሱ ውስተ ሐዲስ ሕይወት ወወሀበነ ፍሥሐ ዘለዓለም ዘሎቱ ክብር ወስብሐት ለዓለም ዓለም፡፡
     የሰው ልጅ ዳግም ልደት ያገኘበት መንፈሱ ፤ ሕሊናው ፤ ሁለንተናው የታደሰበት ሁል ጊዜ በየቀኑ የሚታደስበት የዘለዓለም ፍሥሐ መገኛ የሚሆን የእግዚአብሔር ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፡፡

      ይህን የሐዋርያውን መልእክት መሠረት በማድረግ የእግዚአብሔር ረቂቅ ጥበብ በየጊዜው ያስነሣቸው አበው ሊቃውንት እየተመራመሩ ያደራጁትን የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በዘመናችን የቃልና የጽሁፍ ማሰራጫ ዘዴዎች አማካይነት በአዲስ መልክና አቀራረብ ተርጉመን ለማቅረብ ግዴታችንም ምኞታችንም ስለሆነ በልዑል እግዚአብሔር ፈቃድ ግንቦት  ፩ ቀን ፲፱፻፷፫ ዓ.ም የኢትዮጲያ ፓትርያርክ በኢትዮጲያ ምድር ከተሾመበት ጀምሮ በየጊዜው የሚታተም አንድ መጽሔት መሥርተናል፡፡ ስሙንም “ሐዲስ ሕይወት” ብለነዋል፡፡ ይህም ከላይ የጠቀስነውን የሐዋርያውን ቃል መሠረት በማድረግ ነው፡፡

    
     አዲስ አሮጌ ዘመናዊ ጥንታዊ የሚል የተለያየ ሐሳብ በየዘመኑ የነበረ ያለም ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረው የሕይወት አዲስነት ከዚህ ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ የማያረጅ የማይለወጥ ሁል ጊዜ ዘላቂ ጠባዩን እንደያዘ የሚኖር ፤ መታደስን ለሚመኙና ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ትክክለኛውን አቅጣጫ የሚያዩበት መለኮታዊ መርሕ ያለበት ሕይወት ነው፡፡ ማንኛውንም ነገር አዲስ አሮጌ የሚያሰኘው ጊዜ የሚባለው መለኪያ ነው፡፡ ግን የጊዜው መለኪያነት የሚጸናው ዓለማዊና ግዙፍ በሆነው ነገር ላይ ብቻ ነው፡፡ መለኮት ስንል ከጊዜ ከዘመን በላይና ውጭ የሆነ ለሌላው በመከታተልና በመፈራረቅ ለሚገኘው ጊዜ ፤ ዘመን መሥራች ፤ መገኛ ማለታችን ነው፡፡
    የአብ የባሕርይ ልጁ የሚሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ደኅንነት ይሆን ዘንድ የሰጠን ትምህርት ብልየት እርጅና የማያውቀውና ዘለዓለማዊ ሐዲስነት ገንዘቡ ስለሆነ ከተነገረበት ጊዜ ጀምሮ ዓለምን ከሁለት ከፍሎ አስቀድሞ የነበረውን ጊዜ ዘመን ብሉይ አሰኝቶታል፡፡
    ሐዲስነት ፤ ያለማቋረጥ ሁልጊዜ በክርስቶስ መታደስ (ወእንተ ውስጥነሰ ይትሐደስ ኩሎ አሚረ ፤ (፪ቆሮ.፬፥፲፮) መሆኑን ለማስገንዘብ ሐዋርያው ጳውሎስ በዘመናት መካከል ያለማቋረኝ የሚያስተጋባ ብርቱ ድምጽ ደጋግሞ አሰምቶአል፡፡
       ወይእዜሰ በክርስቶስ ጠሐደሰ ኩሉ ዘኮነ ወኀለፈ ዘትካት (፪ቆሮ.፭፥፲፯)፤
       ሐደሰ ለነ ፍኖተ ጽድቅ ወሕይወት ግብተ በመንጦላዕተ ሥጋሁ (ዕብ.፲፥፳)፤
       እስመ ኀለፈ ዘቀዳሚ ሥርዓት ወናሁ ተሐደሱ ኩሎሙ (ራዕ.፳፩፥፭) ፤
       ንሕነኒ ናንሶሱ ውስተ ሐዲስ ሕይወት (ሮሜ.፮፥፬) ፤
       ሐድሱ መንፈሰ ልብክሙ ወልበስዎ ለሐዲስ ብእሲ ዘሐደሶ እግዚአብሔር በጽድቅ ወበርትዕ ወበንጽሕ (ኤፌ.፬፥፳፬)
       በዚህ ትምህርተ ተሐድሶ ፤ ጽድቅ ፤ ርትዕ ፤ ንጽሕ ፤ ለሰው ሁሉ የመንፈሳዊ ሕይወት ጉዞው (አቅጣጫ) መሪዎች ናቸው፡፡ በነዚህ ላይ የተመሰረተ የግልም ሆነ የማኅበራዊ ኑሮ ሥነ ሥርዓት ሁል ጊዜ አዲስ ነው፡፡ አያረጅም ፤ የመንግሥት አቅዋም ፤ የኅብረተሰብ ሥርዓት ፤ የልማት ድርጅት ፤ በጽድቅ በርትዕ ፤ በንጽሕ ፤ ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት፡፡ ጽድቅ ፤ ርትዕ ፤ ንጽሕ ፤ የተለዩት ሕይወት ጊዜያዊ በመሆኑ ማርጀቱ አይቀርም፡፡ ወዘሰ በልየ ቅሩብ ውእቱ ለሙስና ፡፡ ያረጀ ለድቀት ለጥፋት የቀረበ ነው፡፡ ይህ እንዳይደርስ የቤተ ክርስቲያን ጥረት ነው፡፡ የመታደስ የዳግም ልደት ባለቤት ናትና፡፡
    ጌታ ተከታዮቹን በብርሃን መስሎ መናገሩ እዚህ ላይ የሚታወስ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንም የመለኮት ብርሃን መፍለቂያ መቅረዝ ማለት ናት፡፡ ብርሃን አንድ ጠባይ አለው አያረጅም፡፡ የብርሃን አዲስ አሮጌ የለም፡፡ ለሚያየው ሰው ሁልጊዜ ያው ነው፡፡ ይህ ብርሃን የዘመኑ ምርምር ባስገኛቸው አዳዲስ ዘዴዎችና መሣሪያዎች አማካይነት ለብዙዎች ጎልቶ ይታይ ዘንድ ለማድረግ የታሰበ በመሆኑ ይህም የእኛም ጥረትና ዓላማ ስለሆነ በማናቸውም መንገድ ቀዳሚ እንጂ ተከታይ ልንሆን አንፈልግም፡፡
        ስለዚህ ይህን የመሰለውን አዲስ የሥራ ዘዴ የሚያጠና ድርጅት በመንበረ ፓትርያርኩ ሥር እንዲቋቋም ለማድረግ አስበናል፡፡ ዓላማውም ከዘመኑ የአስተዳደርና የልማት የትምህርትና የኅብረተሰብ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ያለውን የሥራ አያያዝ በክርስትና ብርሃን መሪነት ማጥናትና ከሌሎቹም አብያተ ክርስቲያናት አሠራር ጋር አመዛዝኖ በውጤቱ መሠረት አስፈላጊውን ምክር ለቅዱስ ሲኖዶስ ማቅረብ ይሆናል፡፡ በዚህ መሠረት የሚወሰነው የቤተ ክርስቲያን መምሪያ በልዩ ልዩ የዘመኑ የሐሳብ ዘዴ ማሠራጫ ዘዴዎችና እንዲሁም የመጀመርያው ቁጥር በእጃችሁ ላይ በሚገኘው በዚህ መጽሔት “ሐዲስ ሕይወት” አማካይነት ለብዙዎች እንዲደርስ እናደርጋለን፡፡ … ወደፊትም ማንኛውም ሥራችንን የተቀደሰና የተቃና እንዲሆን ቅን ሐሳብን አስጀምሮ የሚያስጨርስ የደግ ሥራ ሁሉ ደጋፊ እርሱ ልዑል እግዚአብሔር ስለሆነ ጸጋውን ረድኤቱን በብዙ ያክልልን ዘንድ እየጸለይን የሁላችሁን ትብብር እንጠይቃለን፡፡
                                       
                                       ቴዎፍሎስ ቀዳማዊ  ፓትርያርክ ዘኢትዮጲያ፡፡


     አቤቱ ጌታችን ሆይ!  እንዲህ ያሉ፤ ስለሕዝብ መዳንና መለወጥ የሚጨነቁ  አባቶችና መምህራንን አብዛልን፡፡ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment