Monday, 20 July 2015

እኛ የክርስቶስን እንጂ የፖፑን (ጳጳሱን) ቃል አንከተልም!!!


                                     

                                                                             Please read in PDF                                                

የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና። (1ጴጥ.2፥21)

    የዘመን ፍጻሜ ደጅ ላይ ነንና ከሐሰተኛው ጠላት ዲያብሎስ (ዮሐ.8፥44) ብቻ ሳይሆን “የክርስትናን ካባና ላንቃ ከደረቡትም አንደበት ቀጥተኛውን የጠላትን ሐሳብ በአደባባይ እየሰማን ነው፡፡ የሮማው ፖፕ “ጌታ እግዚአብሔር አስሩን ሕግጋትና ሌሎችንም ለማሻሻል ሥልጣን እንደሰጣቸውና እንዳሻሻሉም ሰምተናል” ያውም “ግብረ ሰዶምን እንደቅዱስ ተግባር ከመቀበልና ሌሎችም እንዲቀበሉት ከሚያዝ ስብከት ጋር” ፡፡

     የዕብራውያን መልዕክት ጸሐፊ “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤” (ዕብ.1፥1-2) እንዳለው እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ሃሳቡን “በእርሱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተርኮልናልና” (ዮሐ.1፥18) “ስለዚህ ከሰማነው ነገር ምናልባት እንዳንወሰድ፥ ለእርሱ አብልጠን ልንጠነቀቅ ያስፈልገናል።” (ዕብ.2፥1)
     አንድያ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ከአባቱ ዘንድ ያየውንና “ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምነንም በስሙ ሕይወት ይሆንልን ዘንድ” (ዮሐ.20፥30) ለእኛ የሚጠቅመንን ሁሉ አንዳች ሳያስቀር ነግሮናል፡፡ ያልነገረንም ምንም ነገር የለምና ሁሉን አስቀድሞ ነግሮናል፡፡ (ማቴ.24፥25) ስለዚህም ማንም እንደእርሱ ያለ የነገረን የሚነግረንም ስለሌለ ነው ጌታችን “በዚያን ጊዜ ማንም፦ እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ።” (ማቴ.24፥23-24) በማለት በብርቱ ያስጠነቀቀው፡፡
     ነቢያትና አባቶች “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” የሚሉበት  ያ ፥ አሮጌው ብሉይ ዘመን አልፎ አሁን አንድያ ልጁ “እውነት እውነት እላችኋለሁ” በማለት ሊሆን ያለውን ግልጥ አድርጎ ነገረን፡፡ ደቀ መዛሙርቱና ሌሎችም ቅዱሳን ደግሞ ጌታ ያስተማራቸውን “እንዳይዘልፍህ፥ ሐሰተኛም እንዳትሆን በቃሉ አንዳች አትጨምር።” (ምሳ.30፥6) የሚለውን ቃል በማክበርና በመፍራት አንዳች ነገር ሳይጨምሩ “በእግዚአብሔር ተልከው  በመንፈስ ቅዱስ  … ተነድተው ተናገሩ ፤ ጻፉትም” (2ጴጥ.1፥21)
     የተገለጠውና የተነገረው የእግዚአብሔር ቃልና ትእዛዛቱ እውነትና ፈጽሞ ከሐሰት ጋር የማይስማማ ነው፡፡ (2ሳሙ.7፥28 ፤ መዝ.118(119)፥86 ፤ 142 ፤ 160 ፤ ዮሐ.17፥17) ስለዚህም     የእግዚአብሔርን ቅዱስና እውነት የሆነውን ቃል ከሰው ሃሳብና አመክንዮ ፣ ግምትና አመለካከት ጋር በመሸቃቀጥ ልናቀርብና ልንናገረው አይገባንም፡፡ የክርስቶስ ቃል ብቻውን የየትኛውንም የሰው አሳብና አመለካከት እርዳታ ሳያስፈልገው የሰውን ሕይወት መለወጥና መቀደስ ይቻለዋል፡፡ በዚህ በእርሱ ቃል ላይ አንዳች ቃል ብቻ ሳይሆን “ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ።” (ማቴ.5፥18) ተብሏልና ሥርዓተ ነጥቡ እንኳ የሚሻር አይደለም፡፡
      ስለዚህም “የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥” (2ጴጥ.1፥3) የሰዎች ፍልስፍና ፣ አለማዊ እውቀት ፣ በቃሉ ያልተቀኘ አመክንዮና ተመሳሳይ ነገሮች ፈጽሞ አያስፈልጉንም፡፡ እንዲሁም ከጥንት የተነገረን በክርስቶስ ሆነን (2ቆሮ.12፥19) በቃሉ መውጣትና በቃሉ መግባትን እንጂ “በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾ” (2ቆሮ.5፥8) ከቅንነት ጎድሎ በቃሉ ላይ ስለመጨመርና  በሐሰት ስለመሸቃቀጥ አይደለም፡፡ (ዘኊ.27፥21 ፤ 2ቆሮ.2፥17 ፤ 4፥2)
      ለዚህ ነው የራሳችንን ቃል ልክ እንደእግዚአብሔር አስመስለን ብናቀርብ፥ ሊገጥመን የሚችለውን ፤ ቃሉ ፦ “ማንም በዚህ ላይ አንዳች ቢጨምር እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን መቅሠፍቶች ይጨምርበታል ፤ ማንምም በዚህ በትንቢት መጽሐፍ ከተጻፉት ቃሎች አንዳች ቢያጎድል፥ በዚህ መጽሐፍ ከተጻፉት ከሕይወት ዛፍና ከቅድስቲቱ ከተማ እግዚአብሔር ዕድሉን ያጎድልበታል።” (ራዕ.22፥18-19) በማለት ቃሉን በግድ የለሽነት መተላለፍም ሆነ አልፎ መጨመርን ከሚያስከትለው መቅሰፍት ጋር ያስቀመጠው፡፡
      “ክቡር” የሮማው ፖፕ “ሆይ”! በክርስትናና በእግዚአብሔር ላይ በመዘበት በእግዚአብሔር ትዕዛዛት ላይ ስለምትጨምሩት (ስለጨመራችሁት) ትዕዛዛት አናመሰግናችሁም ፤ አንቀበላችሁምም፡፡ ይልቁን ጌታችን የነገረንን ያንኑ የመዳን ፣ የጸጋ ፣ የክብር ወንጌል “ብትነግሩን” በወደድን ነበር፡፡ ዳሩ “የማያምኑ ስለ ሆኑ በቃሉ ይሰናከሉበታልና” (1ጴጥ.2፥8) እንደተባለ ባለማመን ውጤት ስለተሰናከሉ  እግዚአብሔር የንስሐ ልብ እንዲሰጥዎ እንጸልይሎታለን፡፡ ከሁሉ ይልቅ ደግሞ “በእኔም ከሚያምኑ ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ፥ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር መስጠም ይሻለው ነበር። ወዮ ለዓለም ስለ ማሰናከያ፤ ማሰናከያ ሳይመጣ አይቀርምና፥ ነገር ግን በእርሱ ጠንቅ ማሰናከያ ለሚመጣበት ለዚያ ሰው ወዮለት።” (ማቴ.18፥6-7) የተባለው ቃል ለእርስዎም ነውና ትዝ እንዲልዎ እንማልድልዎታለን፡፡
      ውድ ክርስቲያኖች ሆይ! ቃሉን በመሸቃቀጥ ከፊት ይልቅ የሚሰብኩ ምድርን እያካለሉ ስለመሆናቸው ብዙ ነገሮችን እያየን ነው፡፡ ስለዚህም ከፊት ይልቅ ዛሬ የሚሆነውን ፣ የሆነውን ፣ የሚነገረውን ፣ የተነገረውን ሁሉ ማንም ይናገረው ማን ተናጋሪው ሳያስጨንቀን ፥ ልበ ሠፊ በመሆን በእግዚአብሔር ቃል ሚዛንነት በመመዘን (ሐዋ.17፥11) ከቃሉ ጋር ብቻ የተስማማውን በመቀበልና ለቃሉ በመታዘዝ ፥ በቃሉ ላይ ጸንተን ልንኖር ይገባናል፡፡  

    አቤቱ ይህንን እውነት በሕዝብህ ልብ አብራ፡፡ አሜን፡፡

1 comment: