Monday 3 August 2015

ክርስቶስን በሚያባብል ቃል ለምን? (የመጨረሻ ክፍል)



ኃጢአትን በማለዘብ አንቃወምም!

       እንኪያስ! ኃጢአትንና ኃጢአተኝነትን በማለዘብ ወይም በማድበስበስ አንቃወምም፡፡ መቃወም ያለብን ፊት ለፊትና በድፍረት ነው፡፡ ወንጌልን ለመስበክ የምንደፍርበትን ድፍረት ኃጢአትን ለመቃውም ካልደፈርንበት ምስክርነታችን በጌታ ፊት የተናቀና የተጣለ ነው፡፡   በተለይም ተመክረው ፣ ተዘክረው ፣ ተወቅሰው ፣ ተገስጸው ፣ ተለምነው ፣ በቁጣም ቃል ብዙ ተብለው አልሰማ ፤ አልመለስ ያሉትን ሐሰተኛ የአዞ እንባ አንቢ አባባዮችን እንደአረመኔና እንደቀራጭ ቆጥሮ (ማቴ.18፥17) ያለፍርሃት መቃወም አገባብ ነው፡፡

      የእነዚህን ሰዎች ሥራ መቃወም ዲያብሎስን መቃወም ነው ፤ በእነዚህ ሰዎች ሥራ በዝምታም ይሁን በሌላ መንገድ ማማማትም ከዲያብሎሰ ጋር መስማማት ነው፡፡ “ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት፤ ሰላም የሚለው ሰው በክፉ ሥራው ይካፈላልና።” (2ዮሐ.10-11) በሌላ ሥፍራም “ወንድሞች ሆይ፥ ከእኛ እንደ ተቀበለው ወግ ሳይሆን ያለ ሥርዓት ከሚሄድ ወንድም ሁሉ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን።” (2ተሰ.3፥6) በማለት ቀድሞ በዚያ ዘመን ለነበሩ አማኞች ከመጀመርያዎቹ መናፍቃን ግኖሲሳውያን ፤ በኋላ ዘመን ደግሞ ለእኛም ከሐሰት መምህራን ጋር መደራደር እንደሌለብን የሚነግረን፡፡
      የአደባባይ ስህተት ብዙ ጊዜ ክርስቶስንና የክርስቶስን ሁሉ እንደሚበድል ታላቁ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ (1ቆሮ.5፥4 ፤ 8፥11) ይህን ደግሞ በግልጥ ንስሐ እንዲገባ ከመምከር ይልቅ ማባባል ክርስቶሳዊ የስብከት ዘዴ አይደለም፡፡ ጌታችን ወጣቱን ሃብታም “ፍጹም ልትሆን ብትወድ ፥ ሂድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፥ መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ፥ መጥተህም ተከተለኝ” አለው እንጂ ስለንብረቱ አዝኖ እኔን ከመከተል ይተወኛል ብሎ በመንግሥቱ ሥጋት አልገባውም፡፡ (ማቴ.19፥21)  
      ራሳቸው ደቀ መዛሙርቱንም “እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላችሁን?” (ዮሐ.6፥67) አላቸው እንጂ አላባበላቸውም፡፡ ገና ሲሾማቸውም እውነቱን “እኔ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ … ” (ማቴ.10፥16) ፤ “ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና” (ሐዋ.9፥16)  እያለ ነገራቸው እንጂ፥ እውነትን እየሠዋና እያለዘበ በማባበል ቃል እየተናገረ አማኞችን አልጠራም፡፡ በብሉይም ቢሆን ቢመርም እውነቱ እየተነገረ እንጂ የእግዚአብሔር ባርያዎች በማባበል ቃል አልተጠሩም፡፡ (ዘፍ.12፥1 ፤ ዘጸ.3፥10 ፤ ኤር.1፥7)
       ስለዚህም፦
       ወንጌልን የምንሰማ ቃሉን በእግዚአብሔር ህሊና ሆነው ቆርጠው ከማይናገሩ ፤ ዳሩ እያባበሉ ቃሉን ከሚሰብኩት ልንርቅ ሲገባን ፤
       ቃሉን የምንሰብክ ደግሞ ለእግዚአብሔርና ለቃሉ ህሊናችንን በማስገዛት (ሐዋ.23፥1) በሚያባብል ቃል ከመናገርና ከመስበክ ልንጠበቅና ልንጠነቀቅ ይገባናል፡፡
      አዎን! “እንደምታውቁ ፥ እያቈላመጥን ከቶ አልተናገርንም፥ እግዚአብሔርም እንደሚመሰክር እያመካኘን በመጐምጀት አልሠራንም” (1ተሰ.2፥5) እንዲል ቃሉ በእግዚአብሔር ቃል እውነት ላይ ባለመጨመር ፥ ያንኑ ቃል ብቻ በመናገር በቃል ንግግራችንም ፤ በሕይወታችንም ታማኞች ልንሆን ይገባናል፡፡

  ጌታ ለእውነት ቃል የሚታዘዝና ፤ የእውነትን ቃል በመስማት የምንኖርበት ልብና መንፈስን ያብዛልን፡፡ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment