Sunday 5 July 2015

ክርስቶስን “በሚያባብል ቃል” … ለምን?! (ክፍል ሁለት)



                                       Please read in PDF

እኒህም፦
       ክርስቶስን እንደሌሎች በሚያባብል ቃል አንሰብክም፡፡
       ሐሰተኝነትንም በማለዘብ አንቃወምም፡፡

ክርስቶስን በሚያባብል ቃል ስላለመስበክ

“እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፥ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፥ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም።” (!ቆሮ.2፥4-5)

   ወንጌል ስንሰብክ የሰዎችን ነጻነት (የአመለካከትና የማሰብ) አንጋፋም፡፡ ይህንን ላለመጋፋት ዕውቀትን በጥበብ የመግለጥ መንፈስ ቅዱሳዊ ጸጋን እንጂ (ሐዋ.17፥16-17 ፤ 1ቆሮ.12፥8) የማባበልና የመሸቃቀጥን መንገድ አንከተልም፡፡ የተቆረጠን እውነት ለመናገር በእርግጥም የቆረጠ ልብና መንፈሳዊ ጭካኔ ያስፈልጋል፡፡

    አንድ ወንጌላዊ ከምንም በላይ ትልቅ ትኩረቱ ሊሆን የሚገባው “ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳያውቅ መቁረጥ” ነው፡፡ ይህ የአዲስ ኪዳን የመጀመርያውም የመጨረሻውም መርሕ ነበር፡፡  ይህም ማለት የእግዚአብሔር ኃይል የተባለውን ክርስቶስ በመስቀል ላይ የከፈለውን የማዳን ሥራ (1ቆሮ.1፥18 ፤ 24) በመናገር እንጂ ሰዎችን ስለጽድቅና ስለኃጢአት መውቀስም ሆነ መምከር ፣ አንድ አማኝ ኃጢአትን በመጥላት ከክርስቶስ ጋር ብቻ ህብረት እንዲያደርጉ “በንግግር ችሎታ ወይም በማባበያ ቃል” እንድናደርገው አልታዘዘንም፡፡ በማራኪና በሚስብ የንግግር ችሎታ ወይም የሚያባብል ስብከትን ለሰዎች በማቅረብ ሰዎችን ወደመንፈስ ቅዱስ ሐሴትና ወደክርስቶስ የዘላለም ሕይወት ማምጣት ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በግል የንግግር ችሎታው ወንጌልን ፈጽሞ አልመሰከረም ፤ አላሰበውምም፡፡
    ትምህርታችንና ስብከታችን የእግዚአብሔርን ኃይል የክርስቶስን የመስቀል ሥራ መስበክ ከሆነ፥ ይህን ማድረግ ያለብን በፍጹም መንፈሳዊ ጭካኔ ሊሆን ይገባዋል፡፡  እግዚአብሔር ይህንን እንድንሰብክና በክፋት ላይ እንድንጨክን በጎ ፈቃዱ ነው፡፡ እውነት የሆነውን የክርስቶስን ወንጌል ለመናገር  የሕሊና ጉዳይ እንጂ መሠረቱ ዕውቀትና ችሎታ አይደለም ፤  (በደፈናው ዕውቀት አያስፈልግም የሚል ሃሳብም ፤ አቋምም የለኝም) ሰው በሕሊናው ፊት መልካምነት ከሌለው (ሐዋ.23፥1) ምላሱ ሁለት ነው፡፡ ብዙዎች አገርን የሚጠቅም ዕውቀትና ችሎታ እያላቸው “ሕሊና ቢስ” ስለሆኑ ዕውቀትና ችሎታቸው ለክፋት ፤ ለመሸቀጥ ፤ ለሐሰት ፤ ለኃጢአት ብቻ ሲጠቀሙበት እናያለን፡፡ ቢጨክኑ ግን ብዙ ነገሮችን በመልካም ተጽዕኖነት ለውጠው ፤ ለውጡንም ባየን ነበር፡፡
    እንዲሁ ብዙ የእግዚአብሔር ቤት አገልጋዮች ሕዝቡን ወደክርስቶስ መንግሥት የሚያመጣውን የመዳንና የጸጋ ወንጌል አውቀው ወይም ተረድተውት ሳለ ነገር ግን በሕሊናቸው ፊት ያለውን እውነት ቀብረው ፣ ሸቅጠው ፣ ቀላቅለው ፣ የማባበያና የድለላ ቃል አብዝተውበት ፤ “ሕሊናን ጥለው፥ መርከብ አለ መሪ እንደሚጠፋ፥ በእምነት ነገር ጠፍተው፥” (1ጢሞ.1፥19) ብዙዎችን የሚያጠፉ ሆነው ከመንፈሳዊነት ጭካኔ ርቀው ሲሰብኩ እናያለን፡፡ ለምን?
1.     ብዙ ተከታዮችን ለማግኘት ፤
2.    የሐሰት ትምህርታቸውን ለማስረጽ እንዲመቻቸው ፤
3.    ለኃጢአት ዕውቅናን ለማሰጠትና ለመስጠት፡፡
    እኒህን እያንዳንዳቸውን ለማየት እንሞክራለን፡፡

1.    ብዙ ተከታዮችን ለማግኘት፤
    
     የሐሰት መምህራን ብዙ ተከታዮችን የማፍራትና ፣ “አምነዋል” የተባሉትንም ሃሳባቸውንና እምነታቸውን መገልበጥ ልዩ ልማዳቸው ነው፡፡ እግረ መንገዴን አንድ አሳዛኝ ነገር ላንሳ፦ አሁን በቅርብ የሠማሁት አንድ አሳዛኝ ታሪክ አለ ፤ አንድ “ወንድማችን” ከቤተ ክርስቲያን የነገረ መለኮትን ትምህርት ተከታትሎ ከወጣ በኋላ ራሱን “የጽድቅ አገልጋይ መስሎ ከሚመላለስ የሐሰት መምህር” ጋር እርሱና ብዙዎች እንደሚመላለሱ አውቅ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ “ወንድም” ከዚህ “ክርስቶስን ለመሆን ከሚያጣጥር” ከሚመኝ የሐሰት ትምህርት የተነሳ ራሱን ማጥፋቱን ስሰማ ክው ብዬ ነበር የቀረሁት፡፡ ሌሎቹ ተከታዮች ከዚህ ምን እንደተማሩ ባላውቅም፡፡
  የማባበያን ቃላት በመጠቀም የሚያስተምሩ የሐሰት መምህራን ለአውሬ ነፍሳትን ሊማግዱ ብዙ ተከታዮችን ስለማግኘት ይሠራሉ፡፡ (ማቴ.24፥5 ፤ 11 ፤ ሐዋ.5፥36 ፤ 20፥29-30 ፤ ገላ.1፥7) በዘመን ፍጻሜ ቤተ ክርስቲያን ከሚገጥማት ተግዳሮቶች አንዱ የሐሰት መምህራንን የሚከተሉ ብዙ “አማኞች” የመብዛታቸው ነገር ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ ዘመን እያለ የሚጠራው ከጌታ ሞትና ትንሳኤ ፤ ማረግ በኋላ ያለውን ዘመን በመላ ነው፡፡ ይኸውም የቀደመው ምጽአት በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ሲዘጋ የመጨረሻው ደግሞ በዳግም ምጽአቱ ሊዘጋ በሞቱና በትንሳኤው ተከፍቷል፡፡ ሐዋርያትም የጌታን ምጽአት ቶሎ እንደሚሆን ያወሱትም ለዚህ ነው፡፡ (1ተሰ.4፥16-17 ፤ ራዕ.1፥1 ፤ 4 ፤ 22፥7 ፤ 12 ፤ 20)
   በዚህን ጊዜ የሐሰት መምህራን ትልቁ ሥራቸው የሚከተሏቸውንና ሌሎችን በሰይጣናዊ የሽንገላ ቃል ማሳታቸው ነው፡፡ ሰይጣን ሥራው ዘማሪ ነበር ፤ ከቅዱሳን መላዕክቱ ጋር የሚዘምር፡፡ በስህተቱ ምክንያት ሲወድቅ ደግሞ ሥራውን የጀመረው በእግዚአብሔር ላይ ሐሰትን በሚያባብል ቃል በመናገሩ ነው፡፡ (ዘፍ.3፥4 ፤ ዮሐ.8፥44) ስለዚህም የእግዚአብሔር በሆኑት ላይ ለሁል ጊዜ እያገሳ በመዞር ያደባል (1ጴጥ.5፥8) ፤ ዘማሪ የነበረው ሰይጣን አቅሙ ዘፈንና ሽንገላ ነውና፥ ደቀመዛሙርቱም እንደእርሱ “እርስ በርሳቸው ከንቱ ነገርን ይናገራሉ ፤ በሽንገላ ከንፈር ሁለት ልብ ሆነው ይናገራሉ።” (መዝ.12፥2) ፤ “እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል ሰዎችን በማታለል በአዕምሮ ሕጻናት ያደርጋሉ” (ኤፌ.4፥14) ፡፡ ለዚህ ነው በብዙ አባባይ “መምህራንን” የሚከተሉ ብዙዎች “የሚከተሏቸው መምህራን” በታወቀ ነውርና ርኩሰት ወድቀው እያዩ እንኳ አባባይ ስብከቶቻቸውንና ትምህቶቻቸውን ሰምተው  ለእግዚአብሔር ከማድላት ይልቅ ፈዘው የሚቀሩት፡፡
     እንግዲያስ ፥ የዲያብሎስን ሽንገላና የደቀ መዛሙርቱን የሚያባብል የሐሰት ትምህርት በመስማት ልባችን እንዳይናወጥና እንዳይታለል፥ “የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ።” (ኤፌ.6፥11) የሚለውን አምላካዊ ቃል በፍቅርና በእውነት አምነን ልንታዘዝ ይገባናል፡፡
    አቤቱ ሆይ! ለባርያዎችህ በቅንነት መታዘዝን አብዛልን፡፡ አሜን፡፡

ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment