Saturday, 7 December 2013

ጸሎት- ከራስ መልካምነት ታደገኝ!

 Please read in PDF

     አቤቱ የጽድቄ አምላክ ሆይ በጠራሁህ ጊዜ መልስልኝ ፣ወዴት ነህ? ባልኩህ ጊዜም ተገኝልኝ፡፡ የተጠጋሁብህ አምባዬ የተጠለልኩብህ ታዛዬ ጌታዬ ኢየሱስ ሆይ ለባርያህ መንገድህን እከተልህ፣ አብሬህም አድር ዘንድ አሳየኝ፡፡
          ጌታዬ ሆይ ዛሬም በመቅበዝበዝ ተይዣለሁ፡፡ እንደሰካራም አንተን እንኳ ቀምሼ መሄድ ያምረኛልና እባክህን ወደልቤ መልሰኝ፡፡ አንተን መከተል ማለት ህይወትን መከተል ማለት እንደሆነ ይህን አንድ እውነት ለልቤ ግለጥልኝ፡፡ አውቀዋለሁ፣ ባትነግሩኝም ባላነበውም ይገባኛል ከሚል አይቶ ማንበብን ሰምቶ ማስተዋልን ከሚጠላ ጋኔን ባርያህን ጠብቀኝ፡፡ አንተን አምኜ በተረዳሁበት እምነት አጽናኝ፡፡


         በቅዱስ መንፈስህ ሳልቀኝ ከማገልገል ከልክለኝ፡፡ ፈቃድህን ሳልባርክ ዉሎ ከማደር ባርያህን አንቃኝ፡፡ ከአለም ጫጫታ፣ሁካታና ግርግር ተለይቼ አንተን አጥርቶ ማድመጥ የሚችል ልብና መንፈስን ስጠኝ፡፡ ጌታዬ ሆይ ! እያነከሰ ከሚኖር ማንነት ፣እየበደለህም ራሱን ከሚሸነግል ግብዝነት ባርያህን አድነኝ፡፡አምባዬ ሆይ! ዘመኔን ሙሉ ያንተ ጠላት ሆኜ በዝሙት የምትከብርበት መቅደስ ሰውነቴን፣ በመባረኪያህ ከንፈሬ ዘፈንና ነውርን፣በቃልህ ማሰላሰያ ልቤ አመጽንና ትዕቢትን በማሰብ አሳዝኜሐለሁና ንስሐዬን ተቀበለኝ፡፡

        ጌታዬ ሆይ ረሐብና ጥሜ፣ናፍቆትና ህልሜ ካንተ ጋር መኖር ነውና ጌታዬ ዕድሜዬን በኃጢአት ሳልጨርሰው ባርያህን ወደእቅፍህ ሰብስበኝ፡፡ ሁለንተናዬን ለቅዱስ ፈቃድህ ለየው፡፡ ጉንዳን የምትመግብ ብርታትህ ሙት ማንሳት ትችላለችና በኃጢአት ሙት የሆንኩ ባርያህን ይህች ብርታትህ ታግኘኝ፡፡ በአይኖቼ ፊት መልካም መስሎ ከሚታየኝ ኃጢአትና በደል አድነኝ፡፡ለራሴ መልካም ካልኩትም ነውር አንተ ታደገኝ፡፡
     የብልቶቼ አውራጃዎች ፣የአካሌ ግዛቶች ፣ የሰውነቴም ከተሞች አንተ ብቻ የምትነግስባቸው ይሁኑ፡፡ መድሐኒቴ ህልውናህን በመንፈሴ አይቼ ድርቡን ምስጋና ቅኔውን ላዝንምልህ ፡፡አባ አባቴ ሆይ! ዜማና ግጥም ከመሸምደድ እባክህን በመዝሙር መንፈስ እንድዘምርልህ የመዝሙርን ልብ ስጠኝ፡፡እያየሁህ ልስበክህ ፣እያመንኩህ ልመስክርህ፣እየኖርኩብህ ልሙትልህ ፣እየወደድኩህ ላምልክህ፣እየሰማሁህ ልጥራህ፣እየተመገብሁህ ልራብህ፣ እየጠጣሁህ ልጠማህ ፣ ትኩር ብዬ እያየሁህ ልናፍቅህ፤ እርካታዬ ሆይ ! ለዘለዓለም ልፈልግህ አንተም ተገኝልኝ፡፡ኃጢአቴን ከከሳሽ ፊት ሰውረህ በልጅህ ደም እጠብልኝ፣ በመንፈስህም ኃይል አድሰኝ፡፡
        ወልድ ሆይ! ስለእኔ ዛሬም ከሁለት ሺህ አመት በፊት እንደተሰዋውና ትኩስ ሆኖ ኃጢአቴን በሚያጥበው ደምህ ራራልኝ፣ይቅርም በለኝ፡፡ደምህ ዛሬ ስለእኔ መልካምን እንዲያወራ አምናለሁ፤አምኜም በደምህ ጥላ ሥር ተጠልዬ ነፍሴን ላንተ አደራ እሰጣለሁ፡፡አንተ ሰው አይደለህምና አትጣለኝ፡፡ የምታጽናናኝ መንፈስ ቅዱስ ሆይ! አቤቱ ከፍቅርህ መዓዛ የተነሳ ነፍሴ ትረካብሐለች፡፡መጽናናትህ ልቤን ይመላዋል ስለዚህም እባርክሐለሁ፡፡ ዕለት ዕለት ኢየሱስንና መስቀሉን በልቤ የምትስለው ወዳጄ ሆይ! ላንተ ገና የማያልቅ የዝማሬ ነዶ ከእልልታ ጋር አቀርብልሐለሁ፡፡ጸሎቴን እንደፈቃድህ ስለምትሰማ ተባረክ፡፡የሚያስጨንቀኝ ጠላቴንም ከእግሬ በታች ታስገዛልኛለህና ከፍ ከፍ በል፡፡
 ሞትን በዋጠው፣ ክብርን ባለበሰኝ ኢየሱስ ህያው ስምህ፡፡ አሜን፡፡

2 comments:

  1. Waw,Amen,be blessed *♡*

    ReplyDelete
  2. Amen, Cheru Medhanealem befekru Yanuren! Kalehiwot yasemalegn!

    ReplyDelete