Wednesday, 9 October 2013

ስውር አገልጋዮች


Please read in PDF

 ርዕሰ መምህራን ኢየሱስ ክርስቶስ ህዝብ ወደተሰበሰበበት ቦታ በመሔድ ያስተምር እንደነበር አራቱ ወንጌላውያን በህብረት ዘግበውታል፡፡ በለቅሶ ቤት ፣በገበያ ቦታ ፣በምኩራብና በመቅደስ ፣በባህር ዳርቻ፣በሠርግ ቤትና በሌሎች ስፍራዎች  ከሳሾች እስኪገረሙና እስኪደነቁ ፣ኃጥአን እስኪጽናኑና  እስኪመለሱ፣ ጻድቃን በልባቸው የመንፈስ ቅዱስ ሐሴትና ደስታ እስኪመላና እስኪበዛ ፣ትዕቢተኞች እስኪገሰጹና በሥራቸው እስኪያፍሩ … ያለከልካይ በግልጥ ያስተምር ነበር፡፡ዛሬ በሚያሳዝን መልኩ ለአብዛኛዎቹ አገልጋዮች እንደክስ ምክንያት የሚሆነው ከቤተ መቅደስ ውጪ የሚሰጡት አገልግሎት ነው፡፡በየቤቱ ተሰባስቦ ለሚደረገው የሥጋ ግብዣና ተራ ወሬ ከልካይ ሳይኖርበት ቃለ ወንጌል ለመነጋገርና ለመወያየት ሲሆን ግን ከሌላ ነገር ጋር በግድ ማያያዝ ጠማማነት እንጂ ሌላ ምንም ትርጉም አይሰጠውም፡፡ በእርግጥ አንዳንዶች ይህን አገልግሎት ለኃጢአት አውለውታል፤ ነገር ግን ከኀጢአተኞች ተነስቶ ጻድቁንም መንቀፍ በእግዚአብሔር ዘንድ አጸያፊ ነው፡፡
        የአደባባይ አገልግሎት በነፍስ መወራረድን  የሚጠይቅ ፣የተገለጠ የምስክርነት ህይወትን ያዘለና ጥንቃቄና ማስተዋልን የሚሻ የአገልግሎት አንዱ ክፍል ነው፡፡ የአደባባይ አገልጋዮች የተራቆተ ገላ ናቸው፡፡ ሁለንተናቸው መሰወር የማይችል፡፡ የሰገነት መብራቶች ናቸው በሁሉም ዘንድ የሚታዩ፡፡ ጌታ ለዚህ አገልግሎት  አስራ ሁለት ደቀ መዛሙርት ሲመርጥ ሌሎች ሰባ ሁለት ረዳት ወንድሞችና ሰላሳ ስድስት ምርጥ እህቶችም አብረው ነበሩ፡፡


       የአደባባዩ አገልጋይ ቁጥሩ ትንሽ ነው፡፡ ከጀርባ በስውር ያሉት ግን ቁጥራቸው ከሦስት ጊዜ እጥፍ በላይ ነው፡፡ የአደባባይ አገልግሎት ጠላቱ ብዙ ነው፡፡ ስለዚህ ድብቅና ስውር አገልጋዮች ያስፈልጉታል፡፡ ወጥና እንጀራ ብቻ በማቅረብ አይደለም ጠላት የህዝቡን ልብ እያባከነ ዘሩን ፍሬ አልባ እንዳያደርግና ሲዘራ ዘሩ ፍሬ እንዲኖረውና በቅሎ አብቦ እንዲያፈራ በቦይ የሚያደርጉ፣ አፈር የሚያለብሱ ሌሎች ያስፈልጋሉ፡፡"በታላላቅ" ጉባኤያት ላይ የምናየው ትልቅ ድካም ወጥ አቅራቢና እንጀራ አሳላፊዎቹ ወንጌሉ ላይ የሉም ወይም አይጋበዙም፡፡
      አንድ ንጉስ በሞገስ በህዝብ ፊት የሚራመደው መንገድ ጠራጊዎቹና የደህንነት ሰራዊቶቹ ቀድመው ወጥተው መንገድ ሲደለድሉ፣ ነጻ መሆኑን ሲያረጋግጡለትና እርሱም ዝግጅቱን ሲጨርስ ነው፡፡በወንጌል አገልግሎትም መንገድ ጠራጊና ደልዳይ ስውር አገልጋይ ያስፈልጉናል፡፡ የአደባባዩ አገልጋይ በሞገስ ወጥቶ በሞገስ እንዲመለስ ፣መከራው እንኳ እንደጌታ ሐሳብ እንዲሆንለትና አሳዳጆቹንም ምርኮ አድርጎ ጌታ እንዲሰጠው የተወደዱ ረዳቶች ሊኖሩት ይገባል፡፡
       የብቻ ሩጫ አያጠረቃም፡፡ ለመድረስ አብሮ ሩጫውን መሮጥ ያስፈልጋል፡፡ ቤት የሚሰራው በብዙ ባለሙያዎች ነው፡፡ ቤቱን ሠሪም መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ጸጋን ሠጪና አደላዳዩም እርሱ ነው፡፡አንዳችን ያለአንዳችን አንደምቅም ፡፡ ጳውሎስ ያለሉቃስና ሲላስ ደካማ ነው፡፡ እርሱ ሲሮጥ እነርሱ በብዙ ነገር አብረውት አሉ፡፡ ሁላችንም በድርሻችን በመታመን ልናገለግል ይገባናል፡፡
     ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ የታደለ ነበር፡፡በብዙ መልዕክታቱ ላይ ወንጌሉ እንዳይታሰር "ጸልዩልኝ" እያለ ይለምናል፡፡እርሱም "ጸልዩልኝ" ላላቸው ወገኖች ጌታ የጸሎት ልብና መንፈስ እንዲሰጣቸው ደግሞ ሳይታክት ይጸልያል፡፡ለዚህም ነው እኮ የሚገርምና የሚያስደንቅ ቸርነት እየተደረገለት ፣የሚጠሉትና የሚተቹት ሳይቀሩ በደስታ እየተቀበሉት ወንጌሉን በድንቅ  ምስክርነት የመሰከረው፡፡ስለዚህም በሄደበት ሁሉ ለወንጌሉ መፋጠን የሚማልሉና ደጅ የሚጠኑ ድብቅ የጸሎት ሠራዊትን ያበዛ ነበር፡፡
     ወንጌሉን ስንሰብክና ለህዝብ ስንዘምረው ከኋላ በጸሎት የሚራዱን ያስፈልጉናል፡፡ስላጠናን አናስጠናም፣ስለሸመደድን እውቀት አናስጨብጥም … አገልግሎትን ለፍሬ የምናበቃበት ትልቁ መንገድ ጸሎት ነው፡፡ ከትልልቅ የህይወት ፣የአገልግሎትና የፈውስ ሥራዎች ጀርባ ልብ የሚገዙ የጸሎት ሰዎች አሉ፡፡  ብዙ አገልግሎች ተውበው ተጀምረው ፍጻሜያቸው ምናምንና ፍሬ አልባ የሆነው የኋላ ደጀን ሰራዊት ስላላሰማራን ነው፡፡
      እናንተ የዛሬ አገልጋዮዎች ይህን አስተውላችሁ ይሆንን? አዎ ጥቃቅን የሚመስሉ እነዚህ ሠራተኞች የአገልግሎቱን መልክ ያስውቡታል፡፡ ላለፈው በእንባ ንስሐ ገብተን እንዲህ ወደአገልግሎት ብንወጣ ብዙ ምርኮ፣ብዙ ፍሬ፣ብዙ ባለሠላሳ፣ባለስድሳ፣ባለመቶ … ወደመንግስቱ እናፈልሳለን፡፡ ጌታ ሆይ እንዲህ ያሉ አስተዋይ አገልጋዮችን አስነሳልን፡፡አሜን፡፡

12 comments:

  1. Truly truly It is inspiring me,interesting
    thanks bra,blessing.

    ReplyDelete
  2. Truly truly it is inspiring me,interesting
    Blessing.thanks.

    ReplyDelete
  3. Thank you my brother.

    ReplyDelete
  4. it is really good

    ReplyDelete
  5. እግዚአብሔር አምላክ ፀጋውን ያብዛልህ

    ReplyDelete
  6. Amen Amen Amen God bless u bro

    ReplyDelete
  7. Amen Amen Amen it's correct God bless u bro

    ReplyDelete
  8. አሜን አሜን ቃለህይወትን ያሰማልን !!!

    ReplyDelete
  9. AMEN AMEN AMEN KALEHYWETN YASEMALN !!!

    ReplyDelete
  10. AMEN AMEN AMEN KALE HYWETN YASEMALN !!!

    ReplyDelete
  11. AMEN KALE HYWETN YASEMALN !!!

    ReplyDelete
  12. Thank you for sharing such a wisdom, yes we need more humble servants, who can give freely what they have received freely, we are about making God famous not making flesh and blood famous, on the other hand I see why some people are concerned taking the Gospel everywhere, it may be misused but I still feel the Holy Ghost works better than our enemy, May God help us to be fruit full! Kalehiowt Yasemalen, Tsegawen yabzaleh!

    ReplyDelete