Friday 25 October 2013

ጸሎት - "አቤቱ! ዋጋዬን ለባርያህ ግለጥልኝ "

                           ሺህ ……   1,000?
እልፍ ……   10,000?
አዕላፍ ……   100,000?
አዕላፋት ….    1,000,000?
ትዕልፊት ……    10,000,000?
ምዕልፊት  ….     100,000,000?
አዕላፈ አዕላፋት .…     100,000,000,000?
አዕላፈ ትዕልፊት ……      1,000,000,000,000?
ትዕልፊት አዕላፋት ……     10,000,000,000,000?
ምዕልፊት አዕላፋት ……      100,000,000,000,000?
.?
.?
.?

.?





ጌታዬ ሆይ! ከሚቆጠረው ቁጥር ይልቅ ከመስፈሪያውም እጅግ በዝቶ ምህረትህ ደግፎኛልና አመሰግንሐለሁ፡፡መድኃኒቴ አዕላፍ ጊዜ ካመነዘርኩበት ከዝሙት መንደር እንባ እየረጨሁ ስመጣ ስንት ጊዜ ተቀበልከኝ ? በዘፈን ታጥቦ ጭቃ ከሚሆንና ከማይጠራው ማንነቴ ስንት ጊዜ አጠራኸኝ ? እያመነህ ከሚጠራጠር መናፍቅ ማንነቴን ስንት ጊዜ አለማመኔን ረድተህ መለስከኝ? ጌታ ሆይ አትችልም፣ ረስተኸኛል፣ ዘንግተኸኛል፣አላደመጥከኝም፣ በኃጢአቴ ታዝበኸኛልእያልኩህ ስንቴ አማሁህ? ቤዛዬ ኢየሱስ አንተ ግን ሳትጠየፍ ዛሬም እጅህን ዘርግተህ ተቀበልከኝ፡፡

 ምህረትህ ብዙ ኤልሻዳይ ሆይ! የምህረትህ መጠን ስንት ነው? ሺህ ነውን? አዕላፍ ነውን? ምዕልፊት ነውን? በውኑ የአንተ ምህረት ከእኔ ኃጢአት ከምዕልፊት አዕላፋት ጊዜ አይበልጥምን? የምህረትህን ባዕለጠግነት ማን ሊቆጥረው ይችላል? በበደሌና በኃጢአቴ ሙትና የማልጠቅም ፣በፍጥረቴም የቁጣ ልጅ የምሆነውን፣ እንዲሁ ጠላትና ደካማ ሳለሁ የወደድከኝ በዚህ ፍቅርና ምህረት አይደለምን? ጌታዬ ሆይ! እንኪያስ እኔ ለዚህ ታላቅ ምህረትህ ምን አለኝና ምኔን ልስጥህ? …
     ጌታዬ እኔን ታናሽ ሰው ምኔን አይተህ ወደድከኝ? በውኑ በምድር መካከል የተጣለን ታናሽ ሰው እንዴት አየኸኝ? አፈርና ትቢያ የሆነውን ይህንን ሰውነቴን እንደምን ተዛመድከው? ከቤቴስ ጣርያ በታች እንደምን ገባህ? ጌታዬ ሽቱ ሳላዘጋጅ፣ታርፍበት ዘንድ ምንጣፌን እንኳ ሳላጥበው፣ለእግርህ ውኃን ሳላቀርብልህ ፣ማበሻ ጨርቅ እንኳ ሳላኖርልህራሴን በማጽደቅ የሌላውን ኃጢአት ስቆጣጠር ስንት ዘመን አሳለፍኩ? …
    ጠባቂዬ ሆይ! ታላቅ ምህረትህን እንደእኔ ያበዛህለት ማን ነው? በውኑ እንደእኔ የወደድከው ሰው ማን ነው? ከሁሉ ይልቅ ኃጢአተኛና በደለኛ የሆንኩትን ለፍርዴም ገሐነም የማይተካከለኝና የሚያንሰኝን የእጅህን ሸክላ እንዳከበርከኝ ማንን አከበርክ?


እረኛዬ ሆይ!!! እንዲህ ምህረትህን ያገነንክልኝ ለካስ ዋጋዬ ከምንም ይልቅ ውድ መሆኑን ልትነግረኝ ነውን? ይህ ሁሉ ምህረትና ይቅርታ የበዛልኝ ባርያህ ዋጋዬ ስንት ነው? በውኑ ከፍጡር ወገን ይህንን ማን ያውቅ ዘንድ ይችላል?! ጌታዬ መድሐኒቴ ኢየስስ ሆይ !!! ይህን ሁሉ ያደረክልኝ ፣ውድ ነፍስህንም የሰጠኸኝ በውኑ ዋጋዬ በሰማይና በምድር ካሉት ቢበልጥ አይደለምን? ጌታዬ ሆይ! ይህችን አንዲት ልመናዬን አትንሳኝ፡፡ ባርያህ ዋጋዬ ስንት እንደሆነ አንተ ብቻ ለመንፈሴ ግለጥልኝ፡፡ዋጋዬ ባንተ ዘንድ ብቻ መሆኑንም ይህንን አብራልኝ፡፡
        አብ ሆይ አንድያ ቅዱስ ልጅህን የሰጠኸኝ የእኔ ዋጋ ውድ ቢሆን አይደለምን? እጅጉን ብትሳሳልኝ አይደለምን? መንፈስ ቅዱስ ቅዱሱ እግዚአብሔር ሆይ ይህንን እውነት በልቤ የምትስለው ፣የማትተወኝ፣ ላትረሳኝ በእጅህ መዳፍ ቀርጸህ፣ በዙሪያዬ እንደቅጥር ሆነህ ከምዕልፊት ጊዜ በላይ የምትታደገኝ ይህ ሁሉ ለእኔ አይደለምን? ዋጋዬንስ ከአንተ በቀር ማን ሊያውቀውስ ይችላል?
         በብዙ ምህረት የያዝከኝ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ሆይ! ዛሬም እጅህ ተዘርግታ በብዙ በተትረፈረፈ ምህረትና ይቅርታ ትቀበለኛለችና ምስጋናዬን በእንባ እሰዋለሁ፡፡በደስታም እዘምራለሁ፡፡ እንዲህ ያለ አባት አለኝና ጠላቴ ሆይ ደስ አይበልህ፡፡ በደምህ ባነጻኸኝ መድሐኒቴ ክርስቶስ ኢየሱስ፣ ዛሬም እጅህ ሊቀበለኝ በተዘረጋው አማኑኤል ህያው ስምህ፡፡አሜን፡፡


9 comments:

  1. በጣም ደስ ይላል ።። እውነት ነው እገዚኣብሄር ስራው አፁብ ድንቅ ነዉ።።

    ReplyDelete
  2. Thank you Lord for D Abenezer Teklu.

    God bless you my brother.

    ReplyDelete
  3. AMEN AMEN AMEN KALE HYWETN YASEMALN !!!

    ReplyDelete
  4. AMEN AMEN AMEN AMEN MIHRETU TEKOTRO SILEMAYLKEW GETA MISGAN YIHUN

    ReplyDelete
  5. Amen God bless you more and more brother!

    ReplyDelete
  6. በብዙ ምህረት የያዝከኝ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ሆይ! ዛሬም እጅህ ተዘርግታ በብዙ በተትረፈረፈ ምህረትና ይቅርታ ትቀበለኛለችና ምስጋናዬን በእንባ እሰዋለሁ፡፡በደስታም እዘምራለሁ፡፡ እንዲህ ያለ አባት አለኝና ጠላቴ ሆይ ደስ አይበልህ፡፡ በደምህ ባነጻኸኝ መድሐኒቴ ክርስቶስ ኢየሱስ፣ ዛሬም እጅህ ሊቀበለኝ በተዘረጋው አማኑኤል ህያው ስምህ፡፡አሜን፡፡

    ReplyDelete
  7. Amen eskey Fetare edewedede yadrgew ke su buzu entebkalen des endalew yadrg Geta ulun yawkal








    ReplyDelete