Friday, 4 October 2013

ዮሴፋዊው ጻድቅነት ሲወገዝ



የማቴዎስ ወንጌል ምዕ.1÷19 ስናነብ አንድ ጻድቅ ሰው ሲጨነቅና ለሚበልጠው ለእግዚአብሔር ሐሳብ ሲሸነፍ ፣ሲገዛም እናያለን፡፡እንደኦሪት ህግ አንዲት ሴት ከሌላ ሰው ባል(ወንድ) ወይም ከባልንጀራዋ ባል ጋር ብታመነዝር ሁለቱም በአንድነት እንዲገደሉ (ዘሌ.20÷10) ህጉ ይፈቅዳል፡፡ ህጉ በራሱ ከሳሽ ነውና ከሳሾች አስፈልገውታል፡፡ ህጉ አንዳች ኃይል ሳይሰጠን እንድንፈጽመው ያስገድደናል፡፡ በዚህም "በደልም እንዲበዛ ህግ ጭምር ገባ" (ሮሜ.5÷20) ይለናል ቃሉ፡፡
      በህጉ መሰረት የተከሰሰን መክሰስ ኦሪታዊነት ነው፡፡ ምክንያቱም ህጉም ይህንኑ ይላልና፡፡ የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ቅንና በጎ ብትሆንም ሰዎች ግን ሊፈጽሟት ባለመቻላቸው ኃጢአት የምትጨምርና ሁላችንን ኃጢአተኞች ብላ ልካችንን የምትነግረን ሆናለች፡፡በአንዱ አዳም ህግ መተላለፍ ምክንያት ሁላችን በእርሱ ክስ ተከሰን ኃጢአተኞች ተብለናል፡፡
     ዮሴፍ በህጉ መሰረት በቂ ምክንያት አለው፡፡እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያለወንድ ዘር ጌታ ኢየሱስን ጸንሳ ተገኝታለች፡፡በህጉ መሰረት ያለወንድ ዘር የጸነሰች ሴት ፈጽማ ልትገደል ይገባታል፡፡ይህንን ዮሴፍ ቢያሳውቅ አይሁድ ስራቸው ከቃየል እንደተማሩት ድንጋይ  ጨብጦ መንጋጋት መሆኑን ዮሴፍ ያውቀዋል፡፡ስለዚህ "ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ። "፡፡የክርስቶስ ደም ሳይፈስና ኦሪት ሳትሻር ከህጉ በላይ ጻድቅ የሆነ ብርቱ ሰው ዮሴፍ ተገኘ፤ የቅድስቲቱን "እንደህጉ" አለመጽነስ በመግለጥና በመክሰስ ሳይሆን ሊገልጥ ሳይወድ በስውር በመተው፡፡የሐዲስ ኪዳን ታላቅና ልዩ መገለጥ!!!




       ጌታችን በዚህ ምድር በሥጋ በነበረበት ወራት አይሁድ ስታመነዝር አገኘን ብለው አንዲት ድኃ ሴት አንጠልጥለው ይዘው መጡ(አብሯት ያመነዘረው ወንድ ግን የለም፡፡ምናልባት ባለሥልጣን ዘመድ፣ጉልበት ፣ጉቦ የሚሰጠው ብር ኖሮት ይሆን?)፡፡እንደህጉ ትክክል ናቸው፡፡ህጉ ግን ተሰጥቶ የነበረው ወደእግዚአብሔር እንድንቀርብበት እንጂ ነውር እየገለጥን እንድንነካከስበትና እንድንበላላበት አልነበረም፡፡እነርሱ ግን እርሷን አንጠልጥለው ይዘው መጡ፡፡ዛሬም እንደምናየው ህጉ ብዙ ጊዜ የሚያጠቃው የሌላቸውን ነው፡፡ያላቸውማ የዳኛውን እጅ የቤተክርስቲያንን ህሊና ጠምዝዘው ሲያስፈርዱ፣ሲያስወግዙ፣ሲያሳድዱ በአይኖቻችን እያየን ነው፡፡
     ጌታ በአይኖቻቸው ምሰሶ ተሸክመው የሰው ጉድፍ የሚያጠሩትን አይሁድ  " …ቀና ብሎ ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት አላቸው።"(ዮሐ.8÷7)፡፡የሰውን ኃጢአት ገልጠን የምናወራው የራሳችንን ኃጢአት ልናወራርድበት ነው፡፡የሰዎችን ገመና ስናጠና የምንውለው የእኛን ገመና ለማስተባበል ነው፡፡እግዚአብሔር ግን ጨለማ እንኳ በፊቱ የተገለጠ ብርሐንም የሆነለት አምላክ ነው፡፡ሁሉም  "… ይህን ሲሰሙ ሕሊናቸው ወቀሳቸውና ከሽማግሌዎች ጀምረው እስከ ኋለኞች አንድ አንድ እያሉ ወጡ፡፡"
     ጌታ የኃጢአት ዜና ዘጋቢዎችን ለራሳቸው ተዋቸው፡፡ህሊና ሲበይን ደግሞ እንደፍርድ ቤት ቀጠሮ አያሻውም፡፡ፍርድ ቤት ነጻ ተብለው ህሊና ከግዞት ቤት ያልፈታቸው ስንት እስረኞችን ይሆን ምድራችንና ቤተክርስቲያናችን አዝላ የተቀመጠችው? ሴቲቱ ማመንዘሯ እውነት ነው ቢሆንም እንኳ ጌታ የፍርዳቸውን ጠማማነት በዝምታው ነቀፈ፡፡በሚፈርዱበት በዚያው ኃጢአት መያዝ እንደምን ያለ ምስኪንነትና ባዶነት ነው? አውደ ምህረት ላይ ቆመው አታመንዝሩ የሚሉና የሚጮሁ በህይወታቸው ግን ከአህዛብና ህሊና ከሌላቸው የማይተናነሱ፣ሌላውን የሚናጠቁ ተኩላዎች ብለው ሲዘልፉ ለራሳቸው "በውጭ ለሰው እንደ ጻድቃን እየታዩ፥ በውስጣችው ግን ግብዝነትና ዓመፀኝነት የሞላባቸው"(ማቴ.23፣28)፣ህጉን ለሰው ኃጢአት ሲሆን ሸምድደው የሚያጠኑ ለራሳቸው ሲሆን ግን እኛ "ምዕመናን" አይደለንም የሚሉ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ፈሪሳውያን ዛሬም በዙፋኑ ተቀምጠዋል፡፡
       ዮሴፍ የሐዲስ ኪዳኑን ታላቅ ጻድቅነት አሳየ፡፡ጌታም በህይወት ይህንን ብርቱ ትምህርት አስተማረን፡፡ የሰውን ኃጢአት በማነብነብ ሳይሆን ሁሉን ለእግዚአብሔር በመተው፡፡ዛሬ በአብያተ ክርስቲያናት የምናየው አሳዛኝ ነገር ቢኖር ዮሴፋዊው ጻድቅነት ተወግዞ አይሁዳዊው የከሳሽነትና የሰውን ኃጢአት መተንተን ተንሰራፍቶ ነው፡፡የሚገርመው ነገር ከሳሾቹ በሚታይ ነውርና ኃጢአት እንደተያዙ እየታወቀ እንኳ፤ተከሳሾቹ እንኳን ሊደመጡ እስከወዲያኛው ሊወገዙና ስማቸው ሊጠፋ ይችላል፡፡
       ዲያብሎስ ዘዋሪ ነው፡፡"በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።"(1ጴጥ.5÷8-10)እንደተባለ የሚዞረው የሚውጠውን ፈልጎ እንደአንበሳ  እያገሳ ነው፡፡በጥንት ከእሳት የተጠነቀውን ትንታግ ኢያሱን እድፋም ልብስ ለበሰ ብሎ ከሰሰ(ዘካ.3÷1-6)፣በኋላም ምድርን አካሎ መጥቶ በእግዚአብሔር ልጆች መካከል ቆሞ ኢዮብን ከሰሰ(ኢዮ›2÷2)ዛሬም ዘዋሪ ነውና እነሆ በወንድሞች አንደበት የሚከስ ነው፡፡(ራዕ.12÷10)እንደጌታ ኢየሱስ የሰዎችን ክስ አይከድንም ፣እንደዮሴፍም አለመግለጥን አይመርጥም፡፡የራሱን ጻድቅነት የሚገልጠው አንተን ጥላሸት ቀብቶ ነው፡፡ዘዋሪ ነውና አገልጋዮቹም አንተን ለመክሰስ የማይቆፍሩት ጉድጓድ፣የማይገለብጡት ድንጋይ፣የማይምሱት ምስ የላቸውም፡፡እንዳትገረም ባይገኝብህ እንኳ ከተቀናበረ የሐሰት ክስ እንደጌታ ኢየሱስና እንደቅዱሳኑ አታመልጥም፡፡
       ግና ወዳጄ ክፉን በክፉ ለመበቀል እንዳትነሳ፡፡ሰዎች ያንተን ኃጢአትና ነውር ቢገልጡም አንተ ግን እንኳን ኃጢአቱን ለጊዜው ያልገባህን መልካምነት እንኳ እንደዮሴፍ ልትገልጠው እንዳትወድ፡፡እግዚአብሔር አምላክ የአረጋዊ ዮሴፍን ልብ ያላቸውን መሪዎችና አማንያንን ያብዛልን፡፡ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment