Monday 14 October 2013

የቱ ይበልጥብናል?


                  Please read in PDF
    
     ስለመብለጥ ሚዛናችንን ከቅዱስ ቃሉ አንጻር ካላየንና ብልጫነትን ከሌላ ነገር ተነስተን የምንመዝን ከሆነ በቅጽበት እድሜ ቃሉ ያልፈቀደውንና ፈጽሞ የማይወደውን ሚዛን እናበጃለን፡፡በዓለም ላይ ከሚገመተው ቁጥር በላይ የሆነው ሰው የሚዋደቅለትና አብዝቶ የሚመኘው ነገር ቢኖር ብልጫነትን ወይም መብለጥን ነው፡፡መቼም ለመልካምና እግዚአብሔር በሚወደው ነገር በቅዱስ ቅንአት ማደግና መጎልመስን ከዚህ እንደማናያይዘው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ምክንያቱም በክርስትና ትምህርት ባደግን፣በቤቱ በኖርን ቁጥር መብለጣችንን ሳይሆን በተወደደ ትህትና አለልክ ዝቅ ብለን ሁሉን ማገልገል እንዲገባን እንቆጥራለን እንጂ በአንዳች እንኳ የምንበልጥበት እንዳለን በልባችን ሐሳብ አይገባንም፡፡
      በእርግጥ ዛሬ ለምጽፋት "ትንስዬ" ጭብጤ ይህን ብዬ ተንደረደርኩ እንጂ ዋና ሐሳቤ ሌላ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የመስዋዕትን ህግ ለሙሴ ሲሰጠው የተናገረውን ብዙ ጊዜ እንዲህ ሲገለጥ እወደዋለሁ "ለእንሰሳ ቀንዱ ካልከረከረ፣ጠጉሩ ካላረረ፣ጥፍሩ ካልዘረዘረ ከንጹህና ከተወደደው መካከል መርጦ" ፣ለእህል ቁርባኑ ደግሞ "ነቀዝ ካልበላው ፣ወፍ ካልጠረጠረው፣ እንክርዳድ ከሌለው ከሰባውና "ከመልካም ዱቄቱ" መባሉን አብዝቼ እወደዋለሁ፡፡በእርግጥ ቃሉም ይህን በሚገባ ይገልጠዋል፡፡
      እግዚአብሔር የብሉይ ኪዳኑን የሞትና የኩነኔ አገልግሎቱን እንኳ እንዴት ባለ ክብር እንደወደደ እዩ!! እንኪያስ በደሙ የከበረውና የመንፈስና የጽድቅ አገልግሎት የሆነው የምህረቱ ዘመን አገልግሎት እንዴት ባለክብር ይበልጥ ይሆን?እንደከበረው ምርጡና ውድ መስዋዕት ሆኖ የቀረበውን ትልቁና ዋናውን ነገር ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ይገልጥልናል

      " እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፥ …"(ሮሜ.12÷1)
      ቅዱስ ጳውሎስ ከልመና በሚበልጥ ልመና "በእግዚአብሔር ርህራሄ" አብ ልጁን በመስቀል ላይ በሰጠበት ፍቅርና ጽድቅ ይለምነናል፡፡ለሐዲሱና ለዋናው መስዋዕት ክቡር የገዛ ሰውነታችንን ጌታ ለሚከብርበትና ደስ የሚሰኝበት ነገር ብቻ ህያውና ቅዱስ መስዋዕት አድርገን እናቀርብ ዘንድ፡፡ ይህ ብርቱ ተማህጽኖና ልመና የቀረበው በስሙ አምነን ለተጠመቅን ሁላችን ነው፡፡
      ጌታ እንዳስተማረንና እንደጸለየው ደግሞ "ከጥፋት ልጅ በቀር ማንም ከእነርሱ(ከእኛም) እንዳይጠፋ" በጎ ፈቃዱ ናት፡፡(ዮሐ.17÷12)፡፡በትልቅ ልመና ተለምነን የተጋበዝንለት ግብዣ ከህሊና መረዳት የሚዘል ነው፡፡አዎ! መላ ብልቶቻችን መስዋዕት ሆነው እንዲቀርቡ ብቻ ሳይሆን ሁላችንም አንድም ሰው እንኳ ሳይጎድል ለጌታ የተወደደ መስዋዕት ሆኖ በሰውነቱ እንዲቀርብ በፍቅር ተለምነናል፡፡
      እግዚአብሔር አንድያ ልጁን የሰጠው ለዓለሙ ሁሉ ነው፡፡አንድም እንዳይጠፋ ሁሉም እንዲድኑ፡፡እኔ እንደዳንኩ እርግጠኛ የምሆነው የሌላው አለመዳን በጣም ሲያሳዝነኝና መጥፋቱም መንፈሴን ሲያቃጥለው ነው፡፡ እግዚአብሔር የአመጸኛውና የከሐዲው አዳም ውድቀትና ሞት አላስደሰተውም፡፡ስለዚህ በራሱ መሐላን ምሎ ሊያድነው ተካካይ የሌለውን ኪዳን ገባለት፡፡የእግዚአብሔር ልጁ ነኝ የምንል ተከታዮቹ በምንም ዓይነት መስፈርት የሰው ውድቀትና ሥህተት ሊያስደስተን ሊያስፈነድቀን አይገባም፡፡የሰው ቁስል ሲታየኝ የጌታዬ ቁስል ካልታወሰኝና ማዘን ካልጀመርኩ መንፈሳዊነቴና የክርስቶስ መሆኔ አጠራጣሪ ነው፡፡ስህተታችንን እያገዘፈ የደሙን፣ የበዛ ምህረቱንና ንስሐን እያረከሰ በጌታ ፊት ሊያሳጣን የሚሞክር ብርቱ ጠላት አለብን፡፡የወንድሞች ከሳሽ ዲያብሎስ፡፡ይህ ጠላት ግን እንደእኛ ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ በተፈተነው አባትና ወንድም ኢየሱስ የወደቀና የተጣለ ነው፡፡(ዕብ.4÷15፤ራዕ.12÷10)
         ይህ የተጣለው ጠላት ግን ነገር ለዋውጦብን ለሚበልጠው እውነት እንዳንታዘዝ ልባችንን በብዙ ነገር ገዝቶታል፡፡የአንድ ገዳም ጫካ መቃጠል ፣በሰው እጅ የተሰራ የአንድ ቤተ ክርስቲያን መፍረስ ፣የአንድ ንዋየ ቅድሳት መሰረቅና መጥፋት ፣የአንድ መታሰቢያ ቅጥርና ሐውልት መነቀል … (ይቃጠል፣ይፍረስ፣ ይሰረቅ፣ ይነቀልብሏል ተብሎ እጅ ጠምዝዞ እንደማይተረጎም አምናለሁ) የሚያስቆጣንን፣ የሚያናድደንን ፣የሚቆጨንን፣የሚያስለቅሰንን፣የሚያንገበግበንን፣የሚያስጮኸንንያህል ለምንድር ነው ትልቁ ጌታ የሞተለት አማኝ ክርስቲያን ሲክድ የማያስጮኸን? ለምንድር ነው የአንድ አማኝ በዝሙትና በስካር በዘፈንና ጥንቆላ መፍረስና መርከስ የማያንገበግበን?ሰው በአግባቡ ሳይዳኝ ሲጋዝ፣ሲወገዝ ፣ሲጠላ፣ከቤቱና ከቅጥሩ ደም እያዘነበ፣አካሉ እየጎደለ ሲባረር ለምን ነው የማያስለቅሰን? የቱ ነው የእኛ ጠላትን እንኳ በፍቅርና በእውነት የማሸነፍ ጥበብ?
     በሰውነቱና በመንፈሱ ጌታውን እንዲያከብርና መስዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ የተጠራው ህዝብ ለዘፋኝ ጨርቁን ጥሎ ሲያብድና የጠንቋይ እግር እጣቢ ሲጠጣ ምነው ያላንገበገበን? እውነት የአንዱ ክርስቲያን ወንድም ወይም እህት በኃጢአት መሰናከልና አምላኩን መካድ ከአንድ ቤተ ክርስቲያን መቃጠል የሚያንስ ሆኖ ነው ያላስቆጨን?በርኩሰትና በዘረኝነት መያዙ ከአንድ ገዳም ጫካ መቃጠል ይልቅ ሳያንገበግብ ቀርቶ ነው በመንፈስ ያላቃጠለን? የቱስ ነው የበለጠብን? ለምን ነው አማኝ ነኝ እያለ ለሚዘፍነው፣ ለሚሰክረው፣ ጫት ለሚቅመው፣ ለሚሴስነው፣ ጭፈራ ቤት አድሮ "ኪዳን ለማይቀረው፣ ስብከት ለሚሰብከው ፣ቅዳሴ ለማያስታጉለው ፣መዝሙር ለሚዘምረው ፣ቃሉን ለሚመገበው ምዕመን፣ዲያቆን ቄስ ፣ጳጳስ፣መጋቢ፣ ወንጌላዊ፣ መናኝ መነኩሴዝምታን ከልክ ያለፈ ጸጥታን መርጠን ለገዳም ጫካ፣ለፈረሰ ቤተ ክርስቲያን ፣ለተሰረቀ ንዋይ  … መጮህ ፣እሪታእንዴት ያለመገለጥ፣ እንደምንስ ያለማስተዋል ነው? እውነት ክርስቶስ የሞተለትና ሊፈልገው ከሰማያት ዝቅ ያለለት አንድ ነብስ ከዚህ ሁሉ ሳይበልጥ ቀርቶ ነውን? በውኑ የመላዕክቱና የእግዚአብሔር ደስታ በአንድ ኃጢአተኛ አለመሞትና መመለስ አይደለምን? ደስታው ይህ ከሆነ የሚበልጠው ሐዘኑስ ይህ ሳይሆን ሲቀር መሆን አልነበረበትምን? … ? አዎ ጌታ የሚወደው ይህንን መስዋዕት ነው፡፡ኃጢአተኛ ተመልሶ የምስጋናን መስዋዕት በመንፈስ ሲሰዋለት ማየት፡፡ በውኑ ይህ ምስጋና የሚቀርብበትና አቅራቢ ህያው ቤተ መቅደስ የሰው ሰውነት ሲረክስ ከሁሉ ይልቅ አያንገበግብምን? ቅንአት አያስቀናምን? አያስቆጣምን? ደም እንባ አያስነባምን? የቱ ይሆን የበለጠብን?
     ጌታ ሆይ የሚበልጠውን የምናይበት የልቡናን ብርሐን ስጠን፡፡አሜን፡፡





No comments:

Post a Comment