ሄኖክ ኃይሌ፣ ስለ ተአምረ ማርያም በጻፈው ኹለተኛ ክፍል ላይ እስካኹን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ
ቤተ ክርስቲያን፣ አዋልድ መጻሕፍትን (ማለትም ትርጓሜያትን፣ ገድላትን፣ ድርሳናትን፣ መልክዐ መልክዕን፣ ተአምራትን፣ ነገራትን፣
ፍካሬያትን) ለማስተካከልና ለማደስ የተቸገረችበትን ምክንያት ሲጠቅስ እንዲህ ይላል፤
“ … ላለፉት ሠላሳ ዓመታት ያሳተሟቸውና በነጻ ያደሏቸው መጻሕፍት … ክርስቶስን ‘ጨርሶ አታውቂም’
የሚሏትን ከሳሾችዋን በማስታገሥ ሥራ ላይ ተጠምዳ እንድትቆይ ግድ ኾኖባት ቆይቶአል።”
በገድላት ላይ እንዲህ ያለ ችግር የመጣበትንም ምክንያት ሲናገር፣
1.
ከቋንቋ ወደ ቋንቋ ሲገለበጡ የዐሳብ መጥፋት፣
2.
ጸሐፊያኑ በራሳቸው የሥነ ጽሑፍ ስልት ታሪኮቹን ሲተርኩ
የሚጨምሯቸው አንዳንድ አንቀጾች፣
3.
የመንደር ማተሚያ ቤቶች መኖር፣
4.
የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር ማቃለል የሚፈልጉ ወገኖች
በሚሠሩት የተንኮል ሤራ እንደ ኾነ ይናገራል።
ሄኖክ ላለፉት 30 ዓመታት ብቻ ሳይኾን፣ ተአምረ ማርያምን ፊት ለፊት ከተቃወሙት ከእስጢፋኖሳውያን
ዘመን ጀምሮ፣ አዋልድ መጻሕፍት እንዲስተካከሉ አያሌ ዋጋዎች ተከፍለዋል። ከዚህም ባለፈ በተለያየ መንገድ እጅግ አስተማሪ የኾኑ
ጥናቶች ሲቀርቡ ኖረዋል፣ (ለምሳሌ፦ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፉ የጌታቸው ኃይሌን (1968 ዓ.እ.)፣ የታደሰ ታምራትን
(1970 ዓ.እ.)፣ የሰላማዊት መካን (2006 ዓ.እ.) መጥቀስ ሲቻል፣ በአማርኛ ደግሞ የሰባሄ ካሳውን 1981 ዓ.ም)፣
የሰርፀ ገብረ መድኅንን (1982 ዓ.ም)፣ የኤልያስ መንግሥቱንና
(1997 ዓ.ም) እንዲሁም እነ ዲያቆን አግዛቸው ተፈራ፣ ሊቀ ጉባኤ አበራ በቀለ፣ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ አቡነ መርሐ ክርስቶስ፣ አባ
ገሪማ የሠሩአቸውን ሥራዎች) መጥቀስ ይቻላል።
አራጌ ይመር በወለተ ጴጥሮስና በፍቅርተ ክርስቶስ ላይ
በተሠራ አንድ የገድላት ጥናት ላይ እንዲህ ቀርቦአል፤
“ … ተራኪዎቹ የሴቶቹን ታሪክ ሲያቀርቡ ግራ የመጋባት፣
የማወላወልና የመጠራጠር ነገር ይታይባቸዋል። “የሚስተካከላት የለም” ባሉበት አንደበታቸው፣ መልሰው ‘ተከለከለች’ ይሉናል። ‘የምድር
ነገሥታት ለእርስዋ ይሰግዳሉ’ ባሉበት አንደበት፣ እንደገና ‘ሸሸች፣ ተደበቀች፣ አለቀሰች’ ይሉናል። … ይህን የሚያደርገው የገድሎቹ
ተራኪዎች አድሎአዊ ስለኾኑ ወይም የገድሉ ባሕርይ ኾኖ ሳይኾን የሃይማኖቱ አባዊ ተፈጥሮ ነው። …”[1]
ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት በተጨማሪ እንዲህ ይላሉ፣
“ብዙዎቹ ገድሎች የሚጻፉት ተጋዳልያኑ ከሞቱ ከብዙ ዘመን በኋላ በመኾኑ፣ የገድሎቹ ጸሐፊዎች ስለ ግለሰቦቹ የሚነገሩ አባባሎችን፣ ተረኮችን፣ ታሪኮችን፣ ትውፊቶችን
መሰብሰብና በጽሑፍ መልክ ማዘጋጀት ግድ ይላቸዋል። ጥቂቶቹ ገድሎች ደግሞ ቅዱሳኑ እንደ ሞቱ ወዲያው ስለሚጻፉ ጸሐፊዎቹ
(ምናባዊ ፈጠራ በብዛት ሳይጨምሩ) በገሃድ የሚያውቁትንና የሚያስታውሱትን ይጽፋሉ። በዚህ ዓይነት መንገድ በሚጻፉ ገድሎች ውስጥ
የሚቀርቡ ተጋድሎዎች ‘ተራ’ እና ‘የዘወትር’ መምሰላቸው አይቀርም።”[2]
እንግዲህ የገድላት ተሐድሶ ጥያቄ የረጅም ዓመታት ጥያቄና ውትወታ መኾኑንና ጥያቄውም ዳጎስ ያለና ሊስተባበል
የማይችል ነበር መላት እንችላለን።
በሌላ በኩል ሄኖክ፣ ስለ አዋልድ መጻሕፍት፣ አንድ አስደናቂ ንግግር ተናግሮአል፤
“ገድላት፣ ድርሳናትና ተአምራት ሲነሡ ‘ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ሌላ መጽሐፍ አንፈልግም’ ብለው የሚተቹ
አካላት መጽሐፍ መሸጫ መደብሮቻቸው ጎራ ብትሉ ‘ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ አይሸጥም’ አይሏችሁም። መጽሐፍ ቅዱስን የሚያብራሩ
የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች፣ የሚሲዮናውያን ታሪኮች፣ ‘ሲኦል ደርሶ የመጣው ሰው ምስክርነት’፣ የወንጌላዊው እገሌ የአገልግሎት
ግለ ታሪክ ወዘተ የሚሉ መጻሕፍት መጽሐፍ ቅዱስ ናቸው? አዋልድ መጻሕፍት ማለት ይሄ ነው።”
ይህ እጅግ አስደናቂ ምስክርነት ነው፤ እንዲያውም፣ ሄኖክ፣ “አሜሪካ የተስፋ ምድር ናት” የሚሉ አዋልድ
መጻሕፍት ጭምር አሉ እስከ ማለት ከደፈረ፣ “ለመታደስ” የሚደረገው ጉዞ ይበል የሚያሰኝ ነው ማለት እንችላለን። ከዚህ በፊት
አዋልድ መጻሕፍትን በተመለከተ ያለው ምስክርነት ግን በተቃራኒው ነበር፤ ዳንኤል ክብረት(ዲያቆን) እንዲህ ብሎ ነበር፤
“የሰው ዘር አባትና እናት አዳምና ሔዋን ናቸው፤ ልጆቻቸው ግን
በዝተዋል፤ ሞልተዋል፤ ይበዛሉም፤ ይሞላሉም፤ አዋልድ መጻሕፍትም አባት እናታቸው አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ቢኾንም ልጆቻቸው ግን
በዝተዋል፤ ሞልተዋል፤ ይበዛሉም፤ ይሞላሉም”[3]
ሄኖክ ግን፣ አዋልድ መጻሕፍትን በዚህ ልክ እንዲታዩ መጻፉ ይበል የሚያሰኝ ነው። በነገራችን ላይ ሄኖክ
ወደ ወንጌላውያን የመጻሕፍት መደብር ጎራ ብሎ ያስተዋለውን ትዝብት እኔም እጋራዋለሁ፤ የምጋራው ግን ክርስቶስ ሰምራ ወደ ሲዖል
ወርዳ የመመለሷን ነገር፣ የወንጌላውያን መንደር አለ የተባለውን ‘ሲኦል ደርሶ የመጣው ሰው
ምስክርነት’ በማመሳሰል ነው!
ሌላው፣ የተአምረ ማርያም መጽሐፍ የተጻፈበትን ጊዜም ማስቀመጡ አስደናቂ ምስክርነት ነው፤ የተጻፈበትን
ዘመን 13ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ብሎታል፤ ይህም ጊዜ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ የነገሠበት ጊዜ መኾኑን አንስተውም። ዘርዓ ያዕቆብ
ደግሞ፣ ደቂቀ እስጢፋኖስን በመግደልና በእነርሱ ላይ አሰቃቂ መከራ በማድረስ የታወቀ ሰው እንደ ነበር በታሪክ ሊዘነጋ የማይቻል
እውነት ነው፤ ሄኖክ ግን ‘በዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ብቻ አልተጻፈም’ ለማለት መልሶ ይክድና፣ ሌሎቹም (ማለትም ዐፄ በካፋ፣ ዳዊትና
ቴዎድሮስ) ግን የየራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንና በዘመናቸው የነበረውን ተአምር ማስፈራቸውንም ይናገራል።
በክፍል ኹለት ጽሑፉ ሄኖክ ኃይሌ፣ ሌላ (በርግጥ የተለመደ ነው) አደገኛ ስህተት ይስታል፤ እንዲህ
በማለት፣
“ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንኳንስ አዋልድ መጻሕፍትን ቀርቶ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተካተቱትንም
መጻሕፍት ከብዙ መጻሕፍት መካከል መርጣ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ነው ብላ ወስናለች… ‘ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ሠጠችን እንጂ
መጽሐፍ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን አልሰጠንም’ እንደሚባለው ቤተ ክርስቲን መጽሐፍ ቅዱስን እንኳን በዕድሜ ትቀድመዋለች።”
በዚህ ጽሑፉ ሄኖክ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችበትን ሕያው ቃል በግልጥ ይክዳል። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር
እስትንፋስ ነው ብሎ የሚያምን ሰው፣ ከእስትንፋሰ እግዚአብሔር በፊት ቤተ ክርስቲያን አለች ብሎ ደፍሮ አይናገርም። “በዚችም ዓለት
ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥” (ማቴ. 16፥18) እንዲል፣ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው
በክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅነት ላይ በማመን በጸኑ ቅዱሳን ነው። ይህን ዐሳብ በተመለከተ፣ “የመድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ የመጽሐፍ
ቅዱስን ሥልጣን በመጋፋት ለጻፈው ክፍል የመለስኩትን በስፋት መመልከት ይቻላል።
በመጨረሻም፣ ሄኖክ ከዚህ ጋር አያይዞ፣ የአትናቴዎስን ቀኖና መቀበሉን ካመነ ከ27ቱ የአዲስ ኪዳን
መጻሕፍት ውጭ ሌሎቹን (ግጽው ሲኖዶስ፣ አብጥሊስ፣ ሥርዓተ ጽዮንንና ሌሎችንም) ከወዴት አምጥተው ይኾን የተቀበሉት? ማለት እንወዳለን።
“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ
ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።
[1] አራጌ ይመር፤ የሴትነት ጽንሰ ዐሳብ
በድለ ፍቅርተ ክርስቶስና በገድለ ወለተ ጴጥሮስ፤ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር የሥነ ጽሑፍ መጽሔት (ብሌን) ቅጽ 8፤ ቍ.
1(ታኅሳስ 2007፤ ገጽ 65
[2] Taddesse Tamrat.
“Hagiographies and the Reconstraction of Medieval Ethiopian History.” Confrence
on Current Research Trends in Ethiopian History. Addis Abeba: A.A,U., I.E.S.,
1970
[3] ዲያቆን ዳንኤል
ክብረት፤ ሐመረ ተዋሕዶ(የሐመር መጽሔት ልዩ መጽሔት)፤ ሚያዝያ 1999 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ አሳታሚ ማኅበረ ቅዱሳን።
ከዚህ በላይ ንግግር የለም ለሚገባው የሁሉንም ባይሆን የኔን ጥያቄ ጠይቀህልኛል ድምጽ ሆነህኛል አመሰግናለው ኑርልኝ
ReplyDelete