Saturday, 3 December 2022

የመንፈስ ቅዱስ ጸጋዎች ቀርተዋል ለማለት አንሻፍፈው የሚተረጕሟቸው ጥቅሶች

Please read in PDF

   “በአሁኑ ዘመንም የመንፈስ ቅዱስ እንቅስቃሴ በሚታይበት ቦታ ኹሉ አንዳንዶች ያፌዛሉ፤ ሌሎች ደግሞ እውነተኛ ምልክት እያዩ “ዐይኔን ግንባር ያድርገው” በማለት ለአኹኑ ዘመን አይደለም የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች በሐዋርያት ዘመን አክትሟል ሲሉ ሌሎች ደግሞ “ተጠንቀቁ” በማለት በድፍኑ መሸሽን ይመርጣሉ።”[1]

ኹሉም የስሕተት አስተማሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ክፍሎች ለትምህርታቸው ዋቢነት ከዐውዱ ውጭ ቦጭቀው በማውጣትና በመጥቀስ ዘወትር ይታወቃሉ። የቅዱሳት መጻሕፍትን ሐሳብ ለገዛ ትምህርታቸው በማጣመም ይታወቃሉ፤ ግልጡን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በማጣመም ወይም አወሳስቦ በመተርጐም የሚያኽላቸው የለም፤ ቅዱስ ጴጥሮስ “በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፥ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ” እንዲል (2ጴጥ. 3፥16)።

የእውነት ቃል አገልግሎት አማኞች ወይም እቃአዎች፣ የመንፈስ ቅዱስ የተወሰኑት ጸጋዎች ቀርተዋል፤ ወይም ከሐዋርያት ዘመን ወዲህ አልተሻገሩም ለማለት እንደ ድጋፍ የሚጠቅሷቸው ጥቅሶች የሚከተሉት ናቸው፤

ሐ.ሥ. 2፥1-22፦ ከላይ እንደ ተመለከትነው የእቃአ አማኞች ይህን ክፍል በዋናነት እንደ ተፈጸመ አያምኑም። በአንደኛው መጽሐፋቸው እንዲህ ይላሉ፦

“በመጨረሻም ተጨባጭና የማያሳስት የቤተ ክርስቲያን የምድር ላይ የታሪክ ወሰኖች በዓለ ኀምሳ (ሐ.ሥ. ም. 2) እና የቅዱሳን መነጠቅ ወይም ወደ ላይ መወሰድ ናቸው (1ተሰ. 4፥15-17)።”[2]

በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የነቢዩ ኢዩኤል ትንቢት ጊዜው ደርሶ መፈጸሙን ቅዱስ ጴጥሮስ ከትንቢቱ ክፍል በመጥቀስ ተናግሮታል። እግዚአብሔር አምላክም በነቢዩ ኢዩኤል እንደ ተናገረው፣ በእውነት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቹ ላይ ከመንፈሱ በማፍሰስ ትንቢቱን በቅዱሳን ደቀ መዛሙርት ላይ በትክክል ፈጽሞታል። ይህንም በመጨረሻው ዘመን አደረገው።

በቅዱሳን ደቀ መዛሙርት ላይ መንፈስ ቅዱስ በምልአት ፈጽሞ መፍሰሱ እሙንና ሊካድ የማይችል ነው። ለዚህ የሐዋርያት ሥራን ደጋግሞ ማንበብ አያሌ ምስክሮችን ያስቀምጥልናል፤ እንዲያው በጥቂቱ እንኳ ብንጠቅስ፦

ü  ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክ የሰጠው የተስፋ ቃል በቀጥታ ተፈጽሟል (ሐ.ሥ. 1፥4-5፤ ሉቃ. 24፥49፤ ዮሐ. 14፥16-18፤ 15፥26-27)።

ü  መንፈስ ቅዱስ መውረዱ ለቅዱሳን ደቀ መዛሙርት በትክክል ታይቷል፤ “እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው” እንዲል (2፥3)።

ü  ያው ያዩትና በእያንዳንዳቸው ላይ የተቀመጠው መንፈስ ቅዱስ ደግሞ “ … ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር” እንዲል (2፥4)።

ü  ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተሞልተው በተለያዩ ልሳኖች ሲናገሩ የሰሟቸው በተለያዩ አገራት የሚኖሩ አይሁድ፣ የሰጡት ምስክርነትም እጅግ አስደናቂ ነው፤ “ … የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በልሳኖቻችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን” (2፥11)።

ü  እንግዲህ ቅዱስ ጴጥሮስ ከዚህ በኋላ በነቀፋና በፌዝ ቃል፣ “ጕሽ የወይን ጠጅ ጠግበዋል” ብለው ለተናገሩት አንዳንድ አይሁድ የመንፈስ ቅዱስ መውረድ እንጂ፣ የጕሽ ወይን ጠጅ ጥጋብ እንዳይደለ አበክሮ በመናገር የነቢዩ ኢዩኤልን ትንቢት በዋቢነት ጠቅሶ አጽንቶ ሲያረጋግጥ እንመለከታለን።

ü  በሌላም ስፍራ ለ“ቅዱሳን ደቀ መዛሙርት መንፈስ ቅዱስ እንደ ወረደ፣ የሐዋርያት ሥራ በሚገባ ይመሰክርልናል፤ ‘ … መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ደግሞ በመጀመሪያ እንደ ወረደ ለእነርሱ ወረደላቸው’ ” (ሐ.ሥ. 11፥15)።

እንግዲህ እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መንፈስ ቅዱስ በቅዱሳን ደቀ መዛሙርት ላይ በትክክል መውረዱን ይናገራሉ እንጂ፣ ገና ወደ ፊት በዳግም ምጽአቱ እንደሚወርድ ፈጽመው አይነግሩንም። መንፈስ ቅዱስ በደቀ መዛሙርት ላይ ወርዷል፤ ፈስሷልም። እውነት ለመናገር የእቃአ አማኞች “መንፈስ ቅዱስ በዳግም ምጽአት እንጂ በደቀ መዛሙርት ላይ አልወረደም” ካሉ፣ በዓለ ኀምሳን እንዴት “የቤተ ክርስቲያን የምድር ወሰን መጀመሪያ” ሊሉ ቻሉ? አንድ ነገር እጅግ ወሳኝ ካልኾነ እንዴት “የቤተ ክርስቲያን ወሰን” ሊኾን ይችላል? … ይህ ትምህርቶቻቸው ምን ያኽል እርስ በእርሳቸው የማይታረቁ መኾናቸውን የምናስተውልበት አንዱ ማስረጃ ነው።

በርግጥ አንድ እውነት ፈጽሞ መካድ አይቻልም፤ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ በመውረድ ሥራውን ጀመረ እንጂ የፈጸመ አይደለም። መውረዱ እውን ነው ስንል፣ መንፈስ ቅዱስ የመጨረሻውን መጀመሪያ በማብሠር ጀምሮ፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ደግሞ በተለያየ ጊዜና ኹኔታ ለቅዱሳን ሰዎች መውረዱን ሳያቋርጥ ሥራዎችን በዘመናት ኹሉ ይሠራል ማለታችን ነው።

“ያለ እውነት የእውነት ቃል አገልግሎት!?” ከሚለው መጽሐፌ ገጽ 192-195 ተቀንጭቦ የተወሰደ)



[1] ገብሩ ወልዱ፤ የመንፈስ ቅዱ ስጦታዎችና አጠቃቀማቸው፣ 3ኛ እትም፤ 1992 ዓ.ም.፤ ገጽ 48

[2] ሲ. ኤች. ማኪንቶሽ፤ የጌታ መምጣት 1 እትም፤ ዓ.ም. ያልተጠቀሰ፤ገጽ 34።

No comments:

Post a Comment