ኢየሱስ
ከይሁዲነት ይልቃል!
ኢየሱስ
ከኦሮሞነትና ከአማራነት ከሌሎችም ይልቃል!
ኹሉም የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የተጻፉበት የየራሳቸው ዓላማ አላቸው፤ የመጻሕፍቱ ዋነኛ ዓላማ ማጠንጠኛው ደግሞ፣ የእግዚአብሔር መንግሥትን ማዕከል ያደረጉ ናቸው፤ ከዚህም የተነሣ ዓላማቸው የሚበልጠውንና የሚልቀውን የእግዚአብሔርን ዐሳብና ፈቃድ ማሳየት ነው። ከዚህ አንጻር የዕብራውያን መልእክትን ስንመለከት፣ ኹለት ዋና ዋና ዓላማዎችን ማውጣትና መናገር እንችላለን።
ከመጽሐፉ ስያሜ እንደምናስተውለው ዕብራውያን የአይሁድ ወገን ናቸው፤ አይሁድ
ደግሞ የሚመኩባቸውና አልቀው የሚያዩዋቸው፤ አተልቀው የሚያስቧቸው የተለያዩ ነገሮች አሉአቸው። የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ
በፊተኛ ዓላማው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ አይሁድ ታላቅ ነው ብለው ከሚያስቡት ነገር ሁሉ እጅግ እንደሚልቅ፤ እንደሚበልጥና የሚበልጥበትንና
የሚልቅበትን ምክንያት በትክክል ማሳየት ነው።
አይሁድ በብሉይ ኪዳን ከእግዚአብሔር ጋር በነበራቸው ልዩ ቃል ኪዳን ምክንያት፣
ከሌሎች ሕዝቦች ይልቅ ከፍተኛ የትምክህተኝነት ስሜት ይሰማቸው ነበር። ጌታ እግዚአብሔር ይህን ታላቅ ትምክህታቸውን እንዲተዉ በተደጋጋሚ
ተናግሮአቸዋል፤ በተለይም ደግሞ እነርሱን ማለትም አባታቸውን አብርሃምን እንዴት ካለ አስቀያሚ ስፍራ እንደ ጠራው በማስታወስ፤ (ሕዝ.
16፥1-5፤ ሐ.ሥ. 7፥1-3፤ ዘፍ. 11፥31)።
በርግጥም አይሁድ፣ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ያረፈበት ቃልና ኪዳናት፣
በመላእክት በተደጋጋሚ የተጎበኙ፥ ከሙሴ ሕግን የተቀበሉና እግዚአብሔር ባዘዛቸው መንገድ አምልኮአቸውን የሚያካሂዱ ሕዝቦች
ወዘተ... በመኾናቸው ይኵራሩ ነበር። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር በመጣበት ወራት፣ “የአብርሃም ዘር ነን ለአንድም ስንኳ ከቶ ባሪያዎች
አልሆንም፤” በማለት
በታላቅ የትምክህትና የትዕቢት ንግግር ተናግረዋል፤ (ዮሐ. 8፥33)። ምንም እንኳ አይሁድ ጌታችን ኢየሱስን እንዲህ ቢናገሩትም፣
በግብጽ ለ430 ዓመታት፣ በባቢሎን 70 ዓመታት፣ ለግሪክና ይህን በሚናገሩበት ጊዜ እንኳ በሮም ቅኝ ግዛት ሥር ነበሩ።
የእግዚአብሔር ምሕረት ታላቅ ስለኾነ፣ የመዳን ወንጌል አስቀድሞ ለአይሁድ ተሰብኮ
በዚህ መንገድ ዕብራውያንም ክርስቲያኖች ኾኑ። ክርስቲያን ከኾኑ ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ በአይሁድ ክርስቲያኖች ላይ ከወገኖቻቸው
ስደት ተነሣባቸው። ስለዚህም ዕብራውያን ክርስቲያኖች በመከራው ከመጽናት ይልቅ በመፍገምገም ወደ ቀድሞ ትምክህታቸው በመመለስ ፈተና
ተፈተኑ። እናም የዕብራውያን ጸሐፊ ለዚህ ሁኔታ ምላሽ ለመስጠት አይሁዶች ወደ ብሉይ ኪዳን የአምልኮ መንገድና ወደ ቀደመ ትምክህታቸው
ቢመለሱ፥ በክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት ማመናቸውን እንደ ካዱ ያስረዳል።
ክርስቶስ ታላቅ ሰው ነው ብሎ ቢያስቡም እንኳን፥ ወደ ብሉይ ኪዳን መመለሱ
የክህደት ተግባር ነበር። ለኃጢአታቸው መሞቱን ጭራሽ እንዳልተፈጸመ ታሪክ ከንቱ ማድረጋቸው ነበር። የእግዚአብሔርን የድኅነት
መንገድ ባለመቀበላቸው ሌላ የመዳን መንገድ አያገኙም ነበር። እግዚአብሔር የእንስሳት መሥዋዕቶችን የድኅነት እና የይቅርታ
መንገድ አድርጎ የሚቀበልበት ጊዜ አልፎ ነበር።
ጸሐፊው የክርስቶስን ታላቅነትና እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ዘመን ያቀደው ነገር
ኹሉ ፍጻሜው መኾኑን ያስረዳል። ብሉይ ኪዳን እንደ ጥላ ሲኾን፥ እውነታው ክርስቶስ ነበር። ክርስቶስ የሚገልጣቸውን ነገሮች
በተምሳሌትነት አሳይቷል። ጸሐፊው ለምን አይሁዳውያን ክርስቶስ ላይ ዓይኖቻቸውን መትከል እንዳለባቸውን ወደ ይሁዲነት መመለስ
እንደሌለባቸው ሲገልጽ፥ የሚከተሉትን ነጥቦች አብራርቷል። ክርስቶስ ከሚከተሉት ሁሉ እንደሚበልጥ፥ በዕብራውያን መልእክት ውስጥ
እንመለከታለን፡
1.
ክርስቶስ
እግዚአብሔር ከገለጣቸው ቀደምት መገለጦች፥ እንደ ኢሳይያስ ካሉት ነቢያትም የሚበልጥ ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር በአዲስ
ኪዳን ዘመን አምላክ በኾነው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ልዩ መገለጥን ሰጥቶአልና (ዕብ. 1፥1-4)፣
2.
ክርስቶስ፣
አይሁድ ከሚያከብሩአቸው ቅዱሳን መላእክት በላይ ነው። መላእክት እግዚአብሔር ሕዝቡን እንዲያገለግሉ የሚልካቸው መናፍስት ሲኾኑ፣
ክርስቶስ ግን አምላክና ሰዎች እንዲሁም መላእክት የሚሰግዱለት ነው፤ (ዕብ. 1፥3-2፡18)፣
3.
ክርስቶስ
በብሉይ ኪዳን ታላቅ ሕግ ሰጪ ከነበረው ከሊቀ ነቢያት ሙሴ በላይ ነው (ዕብ. 3፥1-6)። ሙሴ ምንም ያህል ታላቅ ቢኾንም፥
የቤቱ አካል ወይም የእግዚአብሔር ሕዝብ አካል ሲኾን፣ ክርስቶስ ግን አምላክና ከእግዚአብሔር ሕዝብ በላይ ነው።
4.
ክርስቶስ
ከሊቀ ካህናቱ ከአሮን ይበልጣል (ዕብ. 5፥1-10)። አሮንና ከእርሱ በኋላ የነበሩት ሊቀ ካህናት በሙሉ ኃጢአተኞች በመኾናቸው፥
ለራሳቸው ኃጢአቶች መሥዋዕቶችን ማቅረብ ያስፈልጋቸው ነበር። ክርስቶስ ካህንም ንጉሥም በመኾኑ፣ ኃጢአት የሌለበት እና ፍጹም
በመኾኑ፣ ሰውም አምላክም በመኾኑና ከዚህም የተነሣ ሰውንና እግዚአብሔርን ለመወከል በመቻሉና በሌሎችም አያሌ ምክንያቶች ከአሮን
ይበልጣል።
5.
ክርስቶስ
ከብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶች የበለጠ መሥዋዕት ነው (ዕብ 9፥11-14)። እንስሳት ጊዜያዊ የኃጢአት ይቅርታ ከማስገኘት ያለፈ
ፋይዳ የላቸውም። ክርስቶስ ግን ሰውም አምላክም በመኾኑ፥ የበለጠ ታላቅ መሥዋዕት ኾኖአል። እንዲያውም በሚልቅ ክብር ክርስቶስ በመሥዋዕቱ
ከአዳም ጀምሮ እስከ መጨረሻው ግለሰብ ያሉትን ሰዎች ኃጢአት ለማንጻት ችሏል።
6.
ክርስቶስ
በላቀ ድንኳን ወይም ቤተ መቅደስ ውስጥ ያገለግላል (ዕብ. 9፥1-10)። ሰብአዊ ካህናት የሰማያዊቱ ቤተ መቅደስ ነጸብራቅ በኾነ
እና ፍጹምነት በጎደለው የመገናኛ ድንኳን ወይም ቤተ መቅደስ ውስጥ አገልግለዋል። ክርስቶስ እውነተኛ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ
በኾነችው መንግሥተ ሰማያት ውስጥ ያገለግላል።
ክርስቶስ የብሉይ ኪዳንና የአይሁድ የአምልኮ ሥርዓት ማዕከላት ከኾኑት ነገሮች
ኹሉ ስለሚበልጥ፥ ከክርስቶስ ርቆ ፍጹም ወዳልኾነ፥ የአምልኮ ሥርዓት መመለሱ ሞኝነት ነበር።
ኹለተኛ ዓላማ፡ አማኞች ከስደት ለማምለጥ ብለው በክርስቶስ ላይ ያላቸውን
እምነት እንዳይክዱ በጽኑ ለማስጠንቀቅ። ክርስቲያኖች እምነታቸውን እንዳይክዱ የሚያሳስቡ እጅግ ጠንካራ ማስጠንቀቂያዎች
በዕብራውያን መልእክት ውስጥ ይገኛሉ። አይሁድ ክርስቲያኖች በክርስቶስ በማመናቸው ምክንያት ከአይሁድ ወገኖቻቸው የሚመጣውን
ስደት ፈርተው ነበር። ብዙዎቹ እምነታቸውን ለመደበቅ፥ ወይም እምነታቸውን ክደው ወደ ይሁዲነት ለመመለስ እያሰቡ ነበር። የዕብራውያን
መልእክት ጸሐፊ፣ የይሁዲነትን ብልጫ ይንቃል፤ እናም እምነታቸውን ከመካድ ይልቅ በድፍረት ስደትን እንዲቀበሉ ይመክራቸዋል።
የአይሁድ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ ብዙ ካወቁ በኋላ፣ እምነታቸውን ሲክዱ፣ ዘላለማዊ ቅጣቶች ይከተሉአቸዋል።
ሌላ የመዳን መንገድ አያገኙም፤ ስለኾነም ወደ ኋላ ከመመለስ ይልቅ በብሉይ
ኪዳን እንደ ነበሩት ከጊዜያዊውን ችግርና መከራ ይልቅ የመሲሑን ተስፋና ክብር አሻግረው እንደ ተመለከቱ የእምነት አባቶችና
እናቶች መጽናትና ጀግኖች መኾን ያስፈልጋቸዋል። በዚህ ኹሉ ደግሞ ክርስቶስ ሊቀ ካህናት ደግሞ በፈተናዎቻችንና በመከራዎቻችን
ላይ ኹሉ እንድናሸንፍ ጸጋ ይሰጠናል።
እናም በዘመናችን ብዙዎች ከክርስቶስ ይልቅ አተልቀው ወይም አግዝፈው የሚያዩዋቸው
ነገሮች አሉአቸው። ልክ ለአይሁድ ቀናተኞችና አይሁዳዊነት ትልቅ እንደ ነበረው፣ ለአንዳንዶች አማራነትና ፋኖነት ትልቅ ነው፣ ለሌሎች
ደግሞ ኦሮሞነትና ቄሮነት ትልቅ ነው፤ ለሌሎችም ትልቅ ነገራችን ብለው የያዙት ነገር አላቸው፣ ብሔር፣ ነገድ፣ ቋንቋ፣ ጐሳ፣ ሕዝባዊ
ወይም መንግሥታዊ ፖለቲካ፣ ዘረኝነት … ሌሎችም ትልቅ ላሉት ነገር ከክርስቶስ ወደኋላ የተመለሱ አሉ። ለእነዚህና ለሌሎች እንዲህ
እንላለን፤ ኢየሱስ ከኹሉ የላቀና ከፍ ያለ፤ ትልቅ እንላለን! ኢየሱስ ይልቃል! አሜን።
No comments:
Post a Comment