Monday 12 December 2022

ተሐድሶ እንዴት ይታያል? የመጨረሻ ክፍል

 Please read in PDF

ካለፈው የቀጠለ …

የቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓታት የዶግማ ማስፈጸሚያ ሥልቶች ናቸው። ለምሳሌ መጠመቅ የግድ ነው፦ ዶግማ ነው፤ የአጠማመቅ ኹኔታ ግን ሥርዓት ነው። ቁርባን ዶግማ ነው፤ ‹እንዴት መቁረብ ይኖርብናል?› በሥርዓት መልስ ያገኛል። በዚህ ዓይነት ከሐዋሪያት ጀምሮ ያሉ አባቶች ከኅብረተ ሰቡ የአኗኗር ሁኔታ ጋር የሚስማሙና ለጽድቅ ሥራ የሚያበቁ የእምነት መተግበሪያ ስልቶችን ነድፈዋል፤ እንደ ኹኔታውና እንደ ኅብረተ ሰቡ እያዩም ሊያስተካክሉት ይችላሉ።

ለዚህም ልክ እንደ ሕገ መንግሥት ማሻሻያ ቤተ ክርስቲያኒቱ የምታሻሻልበት የራሷ ሥርዓት አላት። የተሐድሶም እንቅስቃሴ በዚህ ዙሪያ ከኾነ በሥርዓቱ መሠረት ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል። ባይኾን ‹የትኛውን ሥርዓት ነው እንዲሻሻል የተፈለገው? እንዲሻሻል የተፈለገበት ምክንያትስ ምንድን ነው?  እስከ ዛሬ ትክክል በመኾን ሲሠራበት ኖሮ አኹን ስህተት መኾኑ በምን ታወቀ? ይሻሻል የተባለው የቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓት የተሻለና ትክክለኛው ቢኾንስ?…› የሚሉ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ። እንዲሁም ‹የሚሻሻለው የቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓት የዶግማዎቹን አይነኬነት ያረጋገጠ ነው ወይ?› የሚለው ጥያቄም መሠረታዊና ሊታለፍ የማይችል መልስ ፈላጊ ነው። እነዚህ ጥያቄዎች ተነስተው አግባባዊ መልስ ካገኙ ሥርዓትን ማሻሻሉ ስህተት አይኾንም። “እውን የተሐድሶ እንቅስቃሴ በዚህ መልክ ነው ወይ?” የሚለውን ጥያቄ ወደ ኋላ እናየዋለን።

በሌላ በኩል በሦስተኛው አማራጭ መሠረት ቤተ ክርስቲያኒቱን ማደስ ያስፈለገው፣ በታሪክ ስህተት የኾኑ አስተምህሮዎች ቀይራ ወይም ጨምሯ በመገኘቷ ነው የሚል መከራከሪያ በተሐድሶዎች ሊነሣ ይነሳል። በዚህ ረገድ አያሌ ጥናቶች ቀርበው ታይተዋል፤ ለማስተካከል በቤተ ክርስቲያኒቱ በኩል ዝግጁነት ባይኖርም። ኹለተኛም በታሪክ የተፈጠረ ስህተትን ማሻሻልና ማስተካከል የሚቻለው ስምምነት ላይ ሲደረስበት እንደ ኾነ ቢታመንም፣ ነገር ግን አንዳንድ ጳጳሳት ይህን በጥቂቱ ደፍረው በአደባባይ ቢናገሩም በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ወይም በሲኖዶሱ በኩል ለትግበራ ሲነሣሱ አልታየም። ለዚህም ይመስላል አንዳንዶች በአቋራጭና በቅሰጣ እስትራቴጂ እስከ መሄድ ያበቃቸው።

ለምሳሌ፦ ‹በቤተ ክርስቲያኒቱ የተፈጠረው ትውፊታዊና ታሪካዊ ስህተት ምንድን ነው? ከመቼ ጀምሮ? ይህ ሊኾን የቻለበት ምክንያት ምንድን ነው? ትውፊታዊና ታሪካዊ ስህተት ስለ መፈጠሩ ማረጋገጫችን ምንድን ነው? እስከ ዛሬ ተደብቆ ኖሮ ዛሬ እንዴት ሊታወቅ ቻለ? ምናልባት ስህተቱ የአኹኑ ቢኾንስ?…› እነዚህና መሰል ጥያቄዎች ተነሥተው መልስ ማግኘት አለባቸው። እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች የአስተምህሮ የዘር ሐረግ አላቸው። እና ቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርቷ በጊዜ ሒደት መሣሣቱን የሚያሣውቀውን ማስረጃ ተሐድሶ በነማን የዘር ሐረግ አገኘው? እነሱ እንደ ትክክለኛ ወስደው እናድስበት የሚሉት ትምህርት በክህደታቸው አውግዛ ከቤቷ የለየቻቸው መናፍቃን አስተምህሮ ቢኾንስ? እነዚህ ኹሉ ጥያቄዎች ተነስተው መልስ የሚፈልጉትም የተሐድሶ እንቅስቃሴ በቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ተነሳሽነት የውስጥ አስተምህሮትዋን መሠረት አድርገው የተነሱ ከኾነ ነው። የተሐድሶ እንቅስቃሴ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ውጪ ባሉ አካላት ቀስቃሽነት የራስዋን አስተምህሮ መሠረት ሳያደርግ የተነሳ ከኾነ ክርክሩ በሌላ መንገድ ይሆናል።

‹የተሐድሶ እንቅስቃሴ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ውጭ ባሉ ኃይሎች አነሣሽነት ተመሥርቶ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመለወጥ የሚንቀሳቀስ ወይም ከውስጥና ከውጭ ባሉ አካላት ስምምነት የተፈጠረ እንቅስቃሴ ቢኾንስ ምን ዓይነት የክርክር አቋም ይኖራል? አኹን የሚካሔደው የተሐድሶ እንቅስቃሴስ ምንጩ ከየትኛው እንደኾነ እንዴት እናውቃለን?› የሚሉ መከራከሪያዎችን እንመርምራቸው። ከኹሉም በፊት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ውጭ ባሉ የእምነት ተቋማት የተመሠረተ ድርጅት ነው ካልን በየትኛው ተቋም አነሣሽነት እንደ ተመሠረተ በዶግማ አስተምህሮውና በእንቅስቃሴ ግንኙነቱ ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል።

ምክንያቱም ከኦ/ተ/ቤ/ክ ውጭ ያሉት ኹሉም የእምነት ተቋማት በኅብረት ተስማምተው ተሐድሶን አቋቁመው በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ አስርፀው አስገቡት ብሎ ለማመን ይከብዳል። በተለይም እርስ በራሳቸው የማይስማሙ የእምነት ተቋማት የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ለማደስ ኅብረት ፈጠሩ ማለት የማያስከድ ዕይታ ይሆናል። ደግሞስ የኢ/ኦ/ቤ/ክን ሃይማኖት ለማደስ የሚስማሙበት ምክንያት ምንድን ነው? ቢኾንስ ለምን በስውርና ምዕመናንና አገልጋይ ካህናት ሳይውቁት ይህንን ያደርጋሉ? መንፈሳዊና ክርስቲያናዊ አካሔድ ነው? የሕግ አግባብስ ይኖረዋል?  ነው ወይስ ከቤተ ክስርስቲያኒቱ አባቶች ጋር ተስማምተው ነው ይህን የሚያከናውኑት? ምክንያቱም ‹ተሐድሶ ከላይ ካሉ ‹አባቶች› ጀምሮ የተቀናጀ እንቅስቃሴ ለማካሔድ እየጣረ ነው› የሚባል ሐሜት ስላለ ስምምነት ያደረጉ ‹አባቶች› ካሉ ብዬ ነው።

ይህ ከኾነም ‹ምን ማለት ነው?› ከመንፈሳዊነት አንጻር ስናየው የሃይማኖት ልዩነት የለም ለማለት ነው? አዎ ከተባለም ኢየሱስ ክርስቶስን ፍጡር ማለትም ኾነ ፈጣሪ ማለት ትክክል ነው ማለት ነው? አኹንም አዎ ከተባለ፣ እንደዚህ ከኾነ ለምን በሃይማኖት ማመን ያስፈልጋል? የሁሉም እምነት ትክክል ከኾነ  አለማመንም ትክክል የማይኾንበት ምክንያት ምንድን ነው? በሃይማኖትም አለመመራት ትክክል ነው ከተባለ ነገሩ ከመንፈሳዊነት ወጥቷል። ሃይማኖት አልባነት ትክክል ከኾነም ተሐድሶ ስሑት ሊሆን ይችላል? አይችልም፦ ሃይማኖትን የማጥፋት ወይም የማርገብ ዓላማ አካል ነውና።

ከዚህ በላይ የቀረበውን መከራከሪያ በማጥበብ ‹የተመረጡና ተቀራራቢ አስተምህሮ ያላቸው የሃይማኖት ተቋማት በጋራ የመሠረቱት ነው፤ ለምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚመሩ የእምነት ተቋማት ልዩነታቸው የተረጓጐም ነው፤ ስለዚህ ተቀራርበው በመነጋገር ወጥ የኾነ የሚያግባባ አስተምህሮ ለመቅረፅ የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው።› የሚል የመከራከሪያ ግምት ሊቀርብ ይችላል። ይኹንና ይህም ቢኾን አያስኬድም።

ምክንያቱም፦

አንደኛ የተሐድሶ እንቅስቃሴ የሚካሔደው በኦርቶዶክስ ቤ/ክን እንጂ በሌሎቹም ጭምር እየተካሔደ መኾኑን የሚጠቁም ማስረጃም ሆነ መረጃ የለም። ‹ተሐድሶ ነኝ› የሚለው ቡድንም እንቅስቃሴውን የሚያደረገው በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ውስጥ መኾኑን ነው በጽሑፎቹ ያረጋገጠው።

ኹለተኛም አንድምታው እስከ ዛሬ የተካሔዱ የአባቶች ጉባኤያትን ኹሉ ይቃወማል። ለምሳሌ፦ የኦርቶዶክስ፣ የካቶሊክ፣ የፕሮቴስታንት (መካነ ኢየሱስ፣ የወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያን ኅብረት…) ኹሉም የእምነት ተቋማት ተስማምተው አንድ አስተምህሮ ሊኖራቸው ከቻለ ከኒቂያ (ሠለስቱ ምዕት) ጀምሮ የተደረገ ጉባኤያትና በጉባኤያቱ የተደረጉት ውግዘቶች የተሣሣቱ ለመኾን ይገደዳሉ። ይህ ደግሞ አጠቃላይ የክርስትና ታሪክን ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል። በሌላ አቅጣጫ ካየነውም በመጀመሪያ እስከ 4ኛው መ/ክ/ዘ ያሉ ጉባኤትን ኹሉም አብያተ ክርስቲያናት በትክክልነት የሚቀበሉ ከኾነም የኦርቶዶክስን አስተምህሮ (ዶግማ) መቀበል ይኖርባቸዋል። ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትመራበት ዶግማ እስከዚያ ጊዜ ድረስ የተወሰኑ ውሳኔዎችን መሠረት ያደረገ ነውና። ለዚህም የአባቶችን አስተምህሮ ሰብስቦ የያዘውን ሃይማኖተ አበው የሚለውን መጽሐፍና የቤተ ክርስቲያኒቱን ቅዳሴያት ማየት ጥሩ ምስክር ይኾናል።

ሦስተኛም ‹ኹሉም ልክ ነው› ወይም ‹ሁሉም ስህተት ነው› የሚል መርህን የተከተለ ይመስላል። ይህ ከኾነም መሠረት አልባነት ነው፤ ምክንያቱም ኹሉም ትክክል ከኾነ ስህተት የሚባል የለም ማለት ነው፤ ኹሉም የተሳሳተ ከኾነም ትክክል የሚባል መሠረት አይኖርም። ይህ ደግሞ ከሃይማኖት ያለፈም አደጋ አለው። ሃይማኖትን የተወሰኑ ግለሰቦች የጉባኤ ስምምነትና ፍላጎት ማንፀባረቂያ በማድረግ ግቡን የሳተ ያደርጉታል። ይህ ምዕመናንን ለኢ-አማንያን አሳልፎ መስጠት ነው።

እነዚህ የእምነት ተቋማት በስምምነት ተሐድሶን ማቋቋማቸው የማያስኬድ ከኾነም ይህን ቡድን በስውርና በምሥጢር የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን ለማፍረስ የሚፈልግ ድርጅት ወይም የሃይማኖት ተቋም ያቋቋመው ነው የሚል ጥርጣሬ መያዝ የግድ ይሆናል። ነገር ግን መሳት የሌለብን እውነት የተሐድሶ ጥያቄን አንግበው የተነሡት የራስዋ ልጆችና የራስዋ ልጆች የነበሩት አገልጋይና አማኞች ናቸው።

እንዲሁም ጥቂት የማይባሉ የቤተ ክርስቲያኒቱም አባቶች ተስማምተውበታል ሊባል ይችላል። ይህም ቢኾን የበለጠ ችግርን ጎልጉሎ የሚያወጣ ይሆናል እንጂ በራሱ የመፍትሔ መልስ የሚሰጥ አይደለም። ነገር ግን ከውስጥም ከውጭ የሚደረገው የተሐድሶ እንቅስቃሴ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ወደ ጥንተ እውነት እንመለስ የሚል ታላቅ ምልክት ይዞ የተነሣ ነው። ይህ ግን እውን የሚኾነውና ከግብ የሚደርሰው በወንጌል ካልሸቀጥን፣ ብርሃን የኾነውን ክርስቶስን በትምህርታችንና በሕይወታችን ከገለጥን፣ ለእንጀራ ስንል ክርስቶስንና ወንጌልን ካልገፋንና ካላፈርንበት ብቻ ነው።

መጽሐፍ ቅዱሳዊው ተሐድሶ ማየሉና ማሸነፉ አይቀርም!

No comments:

Post a Comment