በግልጽ ቃል የዮናታን ዓላማ ቅዱስ ወንጌልን መስበክ አይደለም፤ ዓላማው ቅዱስ ወንጌልን መስበክ ቢኾን
ኖሮ፣ “የቃል እምነት እንቅስቃሴ” ከሚባል ነሁላላ ትምህርት አስቀድሞ ራሱን ባረቀና በጠበቀ ነበር። ነገር ግን ይህ የኑፋቄ
ትምህርቱ እንዳይታወቅበት፣ የኦርቶዶክስን ድርሳንና ገድላት በመንቀፍና በመተቸት “ራሱን ወንጌላዊ አድርጎ ለማቅረብ” ብዙዎችን
ያሞኛል፤ ያጃጅላል።
የኦርቶዶክስ ገድላትና ድርሳናት አብዛኛዎቹ የወንጌል ተቃራኒና አምልኮተ ፍጡራንን የሚያገንኑ
ለመኾናቸው፣ ራሳቸው “ሊቃውንት” በሚሉአቸው ሰዎች አንደበት፣ መነቀፍ ከጀመረ ውሎ አድርአል፤ ስለዚህ ተአምረ ማርያምም ይኹን
ገድለ ተክለ ሃይማኖት፣ አልያም ድርሳነ ዑራዔል አሳችና ክፉ መልእክትን በውስጣቸው ለመያዛቸው ምንም አያጠራጥርም። ይህን ግን
ለመተቸት አቅም አለኝ የሚል ሰው፣ ራሱ ከስህተት ትምህርትና አሠራር ማጽዳት እጅግ ይገባዋል። የክርስትና መርህ “ዕውር ዕውርን
ሊመራው አይችልም ይላልና!
እናም በቀበሮ ጠባይ ወንጌልን ማገልገል ተገቢ አይደለም፤ ቀበሮ ተንኮለኛና ብልጣብልጥ የዱር እንሰሳ
ነው፤ ጌታችን ኢየሱስን ስለ ሄሮድስ፣ “ሄዳችሁ ለዚያች ቀበሮ፦ እነሆ፥ ዛሬና ነገ አጋንንትን አወጣለሁ በሽተኞችንም
እፈውሳለሁ፥ በሦስተኛውም ቀን እፈጸማለሁ በሉአት።” ብሎ ተናገረ። ሄሮድስ በብልጣብልጥነቱ መጥምቁ ዮሐንስን እንደ ገደለው፣
ኢየሱስን ገድሎ የኢየሱስን ሥራ የሚያስቀር መስሎታል፤ ነገር ግን የጌታ ሥራ ከቶ አይቋረጥም! ብልጣብልጥ የኾኑ ሰዎች፣ ሞኞች
አምላክ የሌላቸው ይመስላቸዋል!
የሌሎችን
ስህተት፤ ስህተት በማለት የራስን ስህተት እውነተኛ ማድረግ አይቻልም፤ እኔ በግሌ፣ ከኦርቶዶክስ የስህተት መንገድ ይልቅ
የዮናታን የስህተት መንገድ “ለወንጌላውያን አማኞች” አደገኛ ጠንቅ ነው፤ በሌላ ንግግር ከእባብ ሸሽቶ ዘንዶ ሥር የመሸሸግ
ያህል ነው። “የቃል እምነት እንቅስቃሴ” የንስሐ ዕድልን እንኳ የሚያጠፋና መለኮትን ከወደቀው ዓለም ጋር “የሚያዋስብ” ርካሽ
ትምህርትና “አምልኮአዊ ልምምድ” ነውና!
ከዚኹ
ጋር በተያያዘ፣ ከዮናታን መንገድ መንገድ ብዙም ባልተለየ፣ ከስሁታን ጋር ዝምድና የሚፈጥሩ “አገልጋዮች” እየፈሉ የመጡ
ይመስለኛል፤ ማገልግል መልካም ነው፤ የምናገለግለው ግን ወንጌል ከማይገፉና ከማያራክሱ ጋር እንጂ በእኩያ ፍቅር አብረን ከምንከንፋቸውና
ከስህተት ትምህርትና ሕይወት ካልጠራ ማንነት ካላቸው ኹሉ ጋር አይደለም። እንደ ነቢዩ ኢሳይያስና ኤርምያስ ብሎም እንደ ጌታችን
ኢየሱስ ጥቂት ሰዎች ብቻ እስኪቀሩ ድረስ ለእውነት ጨክናችሁ አገልግሉ እንጂ፣ የብዙ ሰዎችን ድጋፍ ለማግኘትና ተሰሚ ለኾን በቀበሮ
ጠባይ አታገልግሉ! ብልጦች የኾናችሁ አይምሰላችሁ፣ ስቁሉን ኢየሱስ በስብከት ሞኝነት የሚያገለግሉ ሞኝ አገልጋዮችም አምላክ አላቸውና!
“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ
ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።
No comments:
Post a Comment