Saturday 31 December 2022

“የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው መጻሕፍት ሁሉ - ኒዎኔወስቶስ” (2ጢሞ. 3፥16)

Please read in PDF

ቅዱስ ጳውሎስ ኹለተኛ ጢሞቴዎስን ሲጽፍ፣ የኑዛዜ ያህል በሞቱ ዋዜማ ነው (4፥6)፤ የሚጽፍለት ደግሞ “በመንፈስ ለወለደው ልጁ” (1፥2) ቅዱስ ጢሞቴዎስ ነው፤ ለዚህ ተወዳጅ ባላደራ አገልጋይ፣ የቅዱሳት መጻሕፍትን እስትንፋሰ እግዚአብሔርነት በግልጥ ይጽፍለታል። ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ክፍል፣ መጽሐፍ ቅዱስን፣ “ቅዱሳት መጻሕፍት” እና የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው መጻሕፍት” በማለት ይጠራቸዋል። “ኒዎኔወስቶስ” የሚለውም የግሪክ ቃል፣ የቅዱሳት መጻሕፍትን የእግዚአብሔር እስትንፋስነት የሚገልጥ ቃል ነው።

በዚህ ንግግሩም፣

·        መልእክቱን ሲጽፍ፣ ቅዱሳት መጻሕፍት ብሎ የሚጠራቸው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ኹሉ ሲኾን፣ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ተጠናቅቀው የተጻፉ አልነበሩም፣ ስለዚህ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትም እንደ ብሉይ ኪዳን መጻሕፍት፣ “ቅዱሳት” ናቸው፣ (1ጢሞ.5፥15፤ 2ጴጥ. 3፥15)

·        ቅዱሳት መጻሕፍት ኹሉ ደግሞ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ስለኾኑ፣ እንከን አልባ፣ ስህተት የለሽ ትክክለኛ የእግዚአብሔር ቃል ናቸው፣

·        እንከን አልባ ለመኾናቸው ደግሞ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱሳት መጻሕፍትን በቅዱሳን ሰዎች ሲያጽፍ፣ ትልቁን ድርሻ የወሰደና የመራቸው፣ ያነቃቃቸው፣ የነዳቸው፣ ኃያል መንፈስ ነበር (2ጴጥ. 1፥20) ብሎ ያስተምረናል።

ስለዚህ በቅዱሳት መጻሕፍት ያሉትን የጌታን ቃል ብንታመናቸውና በእነርሱም ብንጸናባቸው (2ጢሞ. 1፥5)፣

·        በኢየሱስ ክርስቶስ በሚገኘው እምነት ወደ ድኅነት[መዳን] ሊያደርስ የሚችል ጥበብ አላቸው፣ (ቍ. 15)፣

·        ያለ ቅዱሳት መጻሕፍት የመዳንን መንገድ ሊነግሩን የሚቻላቸው ሌሎች መጻሕፍትም ኾኑ የመዳን መልእክቶች በፍጹም የሉም፣

·        ከመጽሐፍ ቅዱስ በቀርም፣ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ያለበት ሌላ መጽሐፍ በምድር ላይ የለም! ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ያለአንዳች መጠርጠር ልንተማመንባቸውና ልንመካባቸው እንችላለን!

እናም መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ፈቃድና ዐሳብ፣ የሰውን ኹለንተናዊ ኹኔታ፣ የመዳንን መንገድ፣ የኃጢአተኞችን ፍርድና የአማኞችን የዘላለም ደስታን በውስጡ ይዞአል። ትምህርቱም የቅድስና መሠረት፣ ታሪኩም እውነት ነው፤ ደግሞም የቤተ ክርስቲያን መሪ፣ የእውነት ኹሉ ምንጭ፣ ፍርዱም የማይናወጥ ሕያው ነው!

ሊቀ ጉባኤ አበራ በቀለ እንዲህ ይላሉ፣

“… ቅዱሳት መጻሕፍት የሃይማኖታችን መሠረት የኾነውን የክርስቶስን ሕይወት፣ ሞትና ትንሣኤ የሚመሰክሩ ኾኖ ሳለ፣ አንባቢያን ግን ይኸን የተጻፈውን አንብበው ለመረዳትና ለማመን የሚያዳግታቸው መኾኑን ነው። … የቅዱሳት መጻሕፍት ባለቤት የኾነው ጌታ ራሱ ካልገለጸልን በስተቀር እንደ ዓለማውያን መጻሕፍት በየግላችን ካለመንፈስ ቅዱስ ረድኤት ብቻችንን በማንበብ ትክክለኛውን ትርጓሜ አውቀን ለመጠቀም አንችልም። … ስለዚህ ነው ቤተ ክርስቲያናችን መጽሐፍ ቅዱስን ከሌሎች ለይታ “መጻሕፍተ አምላካውያት” በማለት የምትጠራቸው። ይህም ማለት አምላካዊ የኾኑ የአምላክ መጻሕፍት ማለት ነው።”[1]

እኛም ለዚህ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስን የሰጠን ልዑለ ባሕርይ አምላክ መንፈስ ቅዱስ እንጂ ቤተ ክርስቲያን አይደለችም፤ የመጽሐፍ ቅዱስም ባለቤት ጌታ ራሱ እንጂ ሌላ ማንም አይደለም የምንለው፤ እናም ቅዱሳት መጻሕፍትን በጸሎትና በማስተዋል በማንበብ ሕይወት ወደ ኾነው ወደ ጌታችን ኢየሱስ እንምጣ!

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።



[1] አበራ በቀለ (ሊቀ ጉባኤ)፤ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት፤ 1996 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ አሳታሚ ማኅበረ ቅዱሳን፤ ገጽ 157

2 comments:

  1. The right person at the right place!

    ReplyDelete
  2. The right person at the right place!

    ReplyDelete