Sunday 11 December 2022

ተሐድሶ እንዴት ይታያል? ክፍል ፩

 Please read in PDF

ከረጅም ጊዜያት ጀምሮ የተሐድሶ ጉዳይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አነታራኪ ኾኖአል። ንትርኩም “ባፍ በመጣፍ” እንደሚባለው ኾኖአል ማለት ይቻላል። ንትርኩና ፍትጊያው አኹንም ድረስ ያለና እንዲያውም፣ በአኹን ወቅት ደግሞ በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ “ጸረ ተሐድሶ የተባሉ ኮሚቴዎች” የተቋቋሙበትና ከፊት ይልቅ በጽኑ ለመቃወም ቅስቀሳ እንዳለ ጸሐፊው ያስተውላል። ንትርኩና ጭቅጭቁ ደግሞ፣ ቀለል ከሚለውና ለመመለስ ግን ከሚቸግረው፣ “ተሐድሶ የሚባለው እንቅስቃሴ አለ ወይስ የለም?” ከማለት ይጀምራል። እኔም ከዚሁ፣ “እውን የተባለው የተሐድሶ እንቅስቃሴ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ እየተካሔደ ነው ወይስ የለም?” ብዬ በመጠየቅ ልነሳ ፈለግኹ።



የዚህ ጥያቄ መልስ “የለም” የሚል ቢኾን ኖሮ፣ የተባለው ሁሉ ስህተት ስለኾነ በዚህ ጉዳይ ላይ መነታረክ አያስፈልግም ነበር። በ“ሌለ” ጉዳይ ላይ መነታረኩ ምን ጥቅም ይኖረዋል? በሌለ ነገር ያለው፣ “የለም” የሚለው ስም ብቻ ነው። ባይኾን አንድ ነገር በአግባቡ መታየት ይኖርበታል፤ “እና በእንቅስቃሴው ዙሪያ የተዘጋጁ መጽሐፎች፣ መጽሔቶች፣ የተለያዩ መንፈሳዊና ሐዳስያዊ ሥራዎች … ከየት መጥተው ነው መነጋገሪያ የኾኑት?›

እኔ በግሌ፦

1)  ይህን እንቅስቃሴ ከሚያካሒዱ ሰዎች ጋር በአካል ተገናኝቼ ፊት ለፊት ዐሳባቸውን በሚገባ ለመረዳት ሞክሬአለሁ፤

2) ቤተክርስቲያን ለማደስ በሚል የተዘጋጁ ከ76 ያላነሱ መጻሕፍትንና የተወሰኑ መጽሔቶችን አግኝቼ ተመልክቻቸዋለሁ፤ በግብረ መልስ የተጻፉ ጽሑፎችንም እንደዚሁ፣

3)  የተሐድሶን እንቅስቃሴ ለማጋለጥ በሚል ወይም እንቅስቃሴውን በመደገፍ የተለቀቁ ማስረጃዎችን በተለያዩ ድራተ ገጻትን አይቻለሁ፤ (የተዘጉትንም ጨምሮ)፤

4) ሐዳስያን የእምነት አቋማቸውንና አስትምህሮአቸውን የገለጡባቸውን ጽሑፎች ተመልክቼና አዘጋጆቹንም አነጋግሬ ለመኖሩ እጅጉን እርግጠኛ ኾኛለሁ። ስለዚህ ተሐድሶ የሚባለው እንቅስቃሴ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ “የለም ወይም አስወጥተናቸው ጨርሰናል” ብሎ የሚከራከረኝን በጥርጣሬ ለማየት እገደዳለሁ። በዚህ የተነሣ የሚከራከረኝ ሰው ከሚከተሉት ሦስት ቡድኖች በአንደኛው ውስጥ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ።

1)  ምናልባት በቤተ ክርስቲያኒቱ ያለውን ነበራዊ እንቅስቃሴ አያውቅም፤ የተሐድሶ እንቅስቃሴንም ባለማወቁ በድፍኑ “የለም” ሲባል ሰምቶ ያንን በመያዝ በጭፍን ያወራል፤

2)  እንቅስቃሴው መኖሩን ቢያውቅም፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ስምና ክብር እንዳይጎድፍ እንቅስቃሴውን ሸፍኖ በመያዝ በምሥጢርነት ማቆየት ፈልጐአል፤ ስለዚህ እስከዚያ ጊዜ ድረስ “የለም” የሚለውን ዐሳብ ያራምዳል፤

3)  ሌላው ደግሞ “የለም” በሚል ሽፋን እንቅስቃሴው ውስጥ ለውስጥ እንዲከናወን የሚያደርግ ሰው ነው።

ከእነዚህ የቤተ ክርስቲያኒቱ ምዕመናን ክፍሎች መካከልም፣ የመጀመሪያዎቹ ችግራቸው የመረጃ እጥረት ነው ማለት ይቻላል፤ ስለዚህ የተሐድሶ እንቅስቃሴ መኖሩን በትክክል የሚያረጋግጥ ማስረጃ ካገኙ፣ አቋማቸውን በመቀየር “የተሐድሶ እንቅስቃሴ መኖሩን” አምነው ለመቀበል አይቸገሩም። ችግራቸው ባለማወቅ ላይ የተመሠረተ ስለኾነ በማወቅ መፍትሔ ያገኛል።

ሁለተኛው ጎራ የሚገኙት አጉል ቀናነትና የዋህነት አለባቸው። እሳትንም በጭድ በመሸፈን ሊያጠፉ ይሞክራሉ። ስለዚህ የችግሩ ዕድሜ ማራዘሚያ ለመኾን ይገደዳሉ። የተሐድሶ እንቅስቃሴ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር መኾኑን ካመኑ፣ ችግሩን ሳያስወግዱ ማቆየት ውስብስብ ችግርን መጋበዝ እንጂ መፍትሔ አያስገኝም። ሦስተኛው የተሐድሶ እንቅስቃሴ አካል ነው። ስለዚህ የማታለል ሥራ ነው የሚያከናውነው፤ የተሐድሶ እንቅስቃሴም ስውር አካሔድ ማሳያ ነው ማለት ይቻላል። በተለይም የቤተ ክርስቲያኒቱን መድረክ ለማስተማሪያነት የሚጠቀም ሰው፣ የተሐድሶ እንቅስቃሴ መኖሩን አያውቅም ለማለት ያስቸግራል።

እሺ! ተሐድሶ የለም በማለት የሚከራከሩት፣ በዚህ መልክ በሦስት ከፈልናቸው ታዲያ በምን እንለያቸው? ትልቁ ጥያቄ እዚህ ላይ ነው። ይህም ራሱን የቻለ የመፍትሔ አቅጣጫ መቀየስ እንዳለበት ይነግረናል። ይህ ከኾነም መፍትሔውን ለሌሎች አካላት (ለአባቶች) ወይም ለቤተ ክርስቲያን ልጆች ጥረትና መረጃን በአግባቡ የመያዝና የማሳወቅ ሥራ፤ እንዲሁም ትብብርና ቤተ ክርስቲያኒቱን የመጠበቅ  ኃላፊነት እንተወውና ወደ ሌላ ነጥብ እንሸጋገር።

“የተሐድሶ እንቅስቃሴ በቤተ ክርስቲያኒቱ መኖሩ እርግጥ ከኾነ ምንጩ ከየት ነው? ከውስጥ ወይስ ከውጭ? ከውስጥ ነው የሚባል ከኾነ የትኛውን የቤተ ክርስቲያኒቱን መሠረታዊ መርህ ነው አድሳለሁ የሚለው? ለማደስ ያነሳሳው ምክንያትስ ምንድን ነው? ምክንያቱስ አግባብነት ያለውና በቂ ነው? እሺ ይሁን ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማደስም በቂና አግባባዊ ምክንያትም ይኑረው አካሔዱስ ትክክል ነው ወይ?…” እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች አጥጋቢና አዎንታዊ መልስ ሊያገኙ ይገባል።

ነገር ግን በተቃራኒው ተሐድሶ፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ሳይኾን፣ ከውጭ ከኾነም ከየትኛው ቤተ እምነት እንደ ፈለቀና ይህን ሊያደርግ የቻለበት ምክንያትና አካሔዱ ተለይቶ መታወቅ ይኖርበታል። አይ! ኹለቱም (ከውስጥና ከውጭ) በመተባበር የሚያከናውኑት እንቅስቃሴ ነው ከተባለም እንዴት? የሃይማኖት ልዩነት የለም ማለት ነው? ይህ ከኾነስ በጥንት ጊዜ የተደረጉ ጉባኤያት ስህተት ናቸው ማለት ይኾን? ይህንስ ለማድረግ የሚያስችል አሳማኝ ነገር ከምን ተገኘ? …  እነዚህ ጥያቄዎች ዙሪያ ገባቸው ተመርምሮ መታየት አለበት።
ወደ መጀመሪያው ተመልሰን “ይህ የተሐድሶ እንቅስቃሴ የተነሣው ከቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ከውስጥ ሊኾን ይችላል” በሚል ግምት ላይ እንነሣ። እሺ ከኾነ እንቅስቃሴ የሚያደርገው ምኑን ለማደስ ነው? ዶግማዎቿን? የቀኖና ሥርዓታቷን? ወይስ በታሪክ አመጣጧ ችግር ተፈጥሮ? … ነው ከዚህ ከተባሉት አማራጮች ሌላ ምክንያት ይኖራል?› የሚሉ ጥያቄዎችን ለማንሳት እንገደዳለን።

ምክንያቱም እንቅስቃሴ የሚደረገው የሃይማኖት ዶግማዎቿን ለመቀየር ከኾነ ግቡ የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን በሌላ ለመቀየር ነው ማለት ነው። የአንድ የሃይማኖት ዶግማ ለዘላለም አይቀየርም፤ ዶግማው ከተቀየረ ሃይማኖትነቱ ተለወጠ ማለት ነው። የኢ/ኦ/ተ/ቤ የምትመራባቸው አምስት አዕማደ ምሥጢራት (ምሥጢረ-ሥላሴ፣ ምሥጢረ-ሥጋዌ፣ ምሥጢረ-ጥምቀት፣ ምሥጢረ-ቁርባን እና ምሥጢረ-ትንሣኤ ሙታን) አሏት። ከእነዚህ አንዱ ከተቀየረ እሷነቷን ታጣለች።

ስለዚህ የሚካሔደው የተሐድሶ እንቅስቃሴ የቤተ ክርስቲያቱን ዶግማዎች ለመቀየር ከኾነ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማጥፋት ያለመ ነው ማለት ይቻላል። ደግሞስ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማ ለማስቀየር የሚያስችል ሌላ ዶግማ ከየት ተገኘ? ለምንስ መቀየር አስፈለገ? እንቅስቃሴው የቤተ ክርስቲያንቱን ዶግማዎች ለመቀየር ከኾነስ ለምን ተሐድሶ ይባላል?…. በዚህ ዙሪያ ብዙ ጥያቄዎችን በማንሳት መተንተንና አንድምታቸውንም ማሳየት ይቻላል። ይኹንና በጥቅሉ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማዎች (አዕማደ ምሥጢራት፣ መሠረታዊ እምነቶች) መቀየር ቤተ ክርስቲያኒቱን ማጥፋት ነው። የተሐድሶ እንቅስቃሴም ‹ዶግማ ተኮር› ከኾነ ለማደስ ሳይኾን ለመቀየር ያለመ ነው ለማለት እንገደዳለን። ሥርዓትዎቿን ለማሻሻል ያለመ ከኾነስ?

ይቀጥላል …

No comments:

Post a Comment