2. የተሐድሶን ጥያቄዎች መቀበል
የተሐድሶን ጥያቄዎች በደፈናው ከመቃወምና አገልጋዮችን ከማውገዝ ይልቅ፣
በቅንነትና በእግዚአብሔር ቃል መሰረት መዝኖ ጥያቄዎችን መቀበል ተሐድሶን ለማጥፋት የመጀመሪያ ርምጃ ነው። ይህም ርምጃ
ምናልባት በአገልጋዮች እውቀትና ልምድ ማነስ ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን ከተሐድሶ ዓላማ ጋር የማይሄድ ችግር ለማስቀረትና ሙሉ
ለሙሉ በተሻለ አቅም ተሐድሶን ለመምራት ያስችላል።
ተሐድሶን አልፈልገውም ተብሎ አይካድም፤ ምክንያቱም ተሐድሶ በራሱ መንገድ የእግዚአብሔር ቃል በተነገረበት፣ የእግዚአብሔር ስም በተጠራበት እንዲሁም የእግዚአብሔር መንፈስ በሚሠራበት ቦታ ኹሉ የሚከሠት እንቅስቃሴ እንጂ ልናስቀረው የምንችለው ጉዳይ አይደለምና።
ነገር ግን በታሪክም ኾነ በአኹኑ ኹኔታ እየኾነ ያለው ነገር የተገላቢጦሽ ነው።
አብያተ ክርስቲያናት ለራሳቸው ጥንካሬና ትንሣኤ የመጣን የንስሐና የመታደስ ጥሪ ከመቀበል ይልቅ፣ በልዩ ልዩ ምክንያቶችና
መንገዶች መግፋትን መርጠዋል፤ አንዳንዶች በግልጥ ይቃወሙታል፤ የተሐድሶ እንቅስቃሴ አራማጆችን መናፍቃን በማለት ከቤተ ክርስቲያን
ያወግዛሉ፤ ያሳድዳሉ፤ ከሕዝብ ይለያሉ።
አንዳንዶች ደግሞ ተቀብለነዋል በማለት ከእውነተኛ ተሐድሶ ይልቅ መንገድ የሳተ
ለውጥን ያካሂዳሉ፤ የሕዝብን ማንነትና ባህል ከግምት ውስጥ ያላስገባ የምዕራባውያን የባህል ወረራ አካል የኾነ እንቅስቃሴን ኹሉ
ተቀብለው እንደ ወንጌል በመስበክ ቤተ ክርስቲያንን ከማደስ ይልቅ ወደ ልዩ ወንጌል መንገድ መሄድን ተያይዘውታል። በዚህ በኩል
በየመንደሩ ቤተ ክርስቲያን ከፍተው፣ በየቲቪው መስኮቱ ብቅ እያሉ የወንጌልን እውነት ከኢትዮጵያውያን ልብ የሚያጠፋ ተግባር የሚፈጽሙ
ራሳቸውን ነቢያት ብለው የሚጠሩ ሰዎችን ማየቱ በቂ ነው።
ከዚህ አንጻር ሲታይ በግራም ኾነ በቀኝ የተሐድሶ ጥሪ በተገቢ መልኩና በቅንነት
ተቀባይነት አላገኘም። ይህ ካልኾነ ደግሞ ተሐድሶ ኾኖልን የእግዚአብሔር ልብ ስላልረካ የተሐድሶ እሳት እየተቀጣጠለ እንዲቀጥል
እግዚአብሔር ይፈልጋልና ተሐድሶ መጥፋት አይችልም።
ይህ የኹለተኛው አማራጭ ካልኾነ ሌላ አማራጭ አለ።
3. የማያቋርጠውን የመንፈስ ቅዱስን ወቀሳና እንቅስቃሴ መቋቋም መቻል
በእግዚአብሔር ቃልና በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመጣ ተሐድሶን ማስቆም የሚፈልግ
አካል የመንፈስ ቅዱስን እንቅስቃሴን መግታት መቻል አለበት። ተሐድሶ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የሚፈጠር መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ነው።
ማንኛውም ሰው በማንኛውም ጊዜ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ያስነሣል። በምድር ላይ ወንጌል እንዳይጠፋ የሚጠብቅ የእግዚአብሔር
መንፈስ ሰዎች ወንጌልን ሰምተው የሕይወት ተሐድሶ እንዲያገኙና ለሌሎች ሰዎችም ኾነ ለቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ እንዲሠሩ ሰዎችን
ማስነሣቱ አይቀርም። ይህን እንቅስቃሴ ተቋቁሞ (ተቃውሞ) ማስቆም የሚችል ግለሰብም ኾነ ተቋም በምድር ላይ የለም። ስለዚህም ተሐድሶ መቆም የማይችል
የመንፈስ ቅዱስ እንቅስቃሴ እንጂ ሰው የጀመረውና ሰው የሚመራው ስላልኾነ በማንም ወይም በምንም ምክንያት ሊቆም አይችልም።
4. ራስን ከቤተ ክርስቲያንነት (ከክርስቲያንነት) ወደ ሌላ ተቋምነት (እምነት)
መቀየር
ከላይ የተጠቀሱት ሦስት አማራጮች ካልተሳኩ ሌላም የሚከር አማራጭ አለ። ይህም
ቤተ ክርስቲን ኾና ወይም ክርስቲን ኾና ወይም ክርስቲን ኾኖ ተሐድሶን የማትፈልግ/የማይፈልግ ከኾነች/ከኾነ ራስን ወደ ሌለ
ተቋምነት (እምነት) መቀየር ነው። ቤተ ክርስቲያን ኾና ወይም ማንኛውም ግለሰብ ክርስቲያን ኾኖ ተሐድሶን የሚጠላ ከኾነ ቤተ
ክርስቲያንዋ ከቤተ ክርስቲያንነት ከመውጣት ውጭ ተሐድሶን ማምለጥ አይቻልም።
5. ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ካሉ መጻሕፍት ኹሉ የክርስቶስን ስምና ስለ ክርስቶስ ማዳን
የሚናገሩ ዐሳቦችን ማጥፋት መቻል፣
የወንጌል መልእክት ምንጩ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው፤ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ
ውስጥ እንደሚገኘው በተሟላ መንገድ ባይኾንም በተሸቃቀጠ ኹኔታ ቢኾን እንኳ የተጻፈም ኾነ ያልተጻፈ ብዙ ትውፊት በቤተ ክርስቲያን
ውስጥ እየተሠራጨ ኖሯል። አኹንም እየተሠራጨ ነው። በአጠቃላይ አዋልድ ተብለው በሚጠሩና ልዩ ልዩ መጠሪያ ስሞች ባሏቸው
መጻሕፍት ውስጥ የወንጌል መልእክት ይተላለፋል። ገድላት፣ ድርሳናትና ተአምራት እንዲኹም መልክአ መልክኣት ኹሉ በተነበቡ ቁጥር
ስለ ክርስቶስ አዳኝነት የሚናገሩ መልእክቶች አላቸው። በውስጣቸው ከሚያስተላልፉት የስህተት ትምህርት መካከል እንደ ዕንቍ
የሚያበራ የክርስቶስ የማዳን ሥራ አለ። ይህን ዐሳብ ከየመጻሕፍቱና ከትውፊቶች ኹሉ መካከል ለቅሞ ማውጣትና ከክርስቶስ ስምና
የማዳን ሥራ መጻሕፍቶቹን ማጽዳት እስካልተቻለ ድረስ ወንጌል በተነገረበት ቦታ ኹሉ ለውጥ መፍጠሩ አይቀርም።
እነዚህን ከላይ የተጠቀሱ ስልቶች መተግበር የሚችል አካል/ተቋም አይኖርም።
ስለዚህ ተሐድሶን ማስቀረት የሚችል አንድም አካል እንደ ሌለ እንረዳለን። በዚህ ምክንያት ተሐድሶ ከቤተ ክርስቲያን ከውስጧ
መፍለቁን አያቆምም። ቤተ ክርስቲያን ደግሞ እነዚህን ከላይ የጠቀስናቸውን ርምጃዎች መውሰድ አትችልም። ይህን ማድረግ አልቻለችም
ማለት ደግሞ ተሐድሶ ይቀጥላል ማለት ነው። መንፈስ ቅዱስ ትናንትናም፣ ዛሬም፣ ኹልጊዜም በሥራ ላይ ነው! በወንጌል ስብከት
ለቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ ተሐድሶ እንድንሠራ የጠራን ልዑል እግዚአብሔር በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ምስጋና
ይድረሰው፤ ለዘለዓለሙ አሜን።
No comments:
Post a Comment