Friday 6 January 2023

ጌታዬ ኢየሱስ ለእኔ የተወለደባቸው ምክንያቶች

 Please read in PDF

በምድራችን ላይ ሲሰሙ ከሚወደዱ ታላላቅ ምሥራቾች ኹሉ፣ የሚልቀውና አቻ የሌለው ምሥራች፣ የጌታችን ኢየሱስ መወለድን የሚያህል ሌላ ምሥራች የለም! መልአኩ እንዲህ አለ፣ “እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።” (ሉቃ. 2፥10-11)፤ ለሰው ኹሉ የሚበቃና ሰውን ኹሉ በእኩል ደስ ማሰኘት የሚችል ምሥራች ከክርስቶስ በቀር አለመኖሩ እንዴት ይደንቃል!

በርግጥ፣ አይሁድ መሲሕ ብለው ይጠብቁት የነበረው ከሮም የፖለቲካ አገዛዝ ነጻ የሚያወጣቸውን አልያ፣ ከምድራዊ በሽታና የኑሮ ሰቆቃ የሚታደጋቸውን መሲሕ በብርቱ ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን አማናዊው መሲሕ የመጣው ሰዎችን ኹሉ ከኀጢአትና ከዘላለም ሞት ያድን ዘንድ ነው፤ (ማቴ. 1፥21፤ ዮሐ. 4፥42)። እናም ሰዎች ከሚያስቡት በላይ ዕረፍትና ፍስሐ፤ መጽናናትና ክብርን ያመጣ ዘንድ መሲሑ ተገለጠ፤ አሜን!

ከዚህ በተጨማሪ መሲሑ ለእኔ የተወለደበትን እኒህን ምክንያቶች ልዘርዝር፣

1.  እግዚአብሔር ልጁን እንድመስል ስለ ወደደ

እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ ሰውን በራሱ መልክና አምሳያ ፈጠረው፣ ወደደው፤ አከበረው፤ አገነነው (ዘፍ. 1፥26 እና 28)። ሰው ግን ኀጢአትን በመሥራቱ (ዘፍ. 3፥7) በእግዚአብሔር ፊት የነበረውን ሞገስና መወደድ አጣ፤ እናም በራሱ መልክና አምሳል ማለትም ከኀጢአተኛ ተፈጥሮ የተነሣ፣ ኀጢአተኛ ማንነት ያለውን ሰው ወለደ (ዘፍ. 5፥3)፤ እናም ለዘመናት ሰው እግዚአብሔርን መምሰል ሳይቻለው ቀረ።

እንግዲህ ክርስቶስ ኢየሱስ፣ “ … በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ[ተወለደ]።” (ዕብ. 2፥14)። ክርስቶስ የእኛን ሥጋ በመንሣት ከቅድስት ድንግል ባይወለድ፣ እኛ እርሱን እንመስል ዘንድ ፈጽሞ አይቻለንም ነበር፤ እግዚአብሔር፣ “አስቀድሞ ያወቃቸው[ን ልጆቹን] የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ የወሰነው” (ሮሜ 8፥29) ልጁ ኢየሱስ፣ ከእኛ ሥጋን በመንሣት፣ በመካከላችን እንደ “ታላቅ ወንድም” እንዲመላለስ በማድረግ ነው፤ ክብር ይኹንለት፤ አሜን።

2.  በሥጋው መሥዋዕትነት ያድነኝ ዘንድ

ክርስቶስ ሰው ኾኖ ባይወለድልኝ ኖሮ፣ በቅዱስና እንከን አልባ በኾነ ሥጋው መሥዋዕት የሚኾንልኝ ማግኘት አይቻለኝም ነበር። ክርስቶስ፣ ከቅድስት ድንግል በመወለዱና ፍጹም ሰው ኾኖ በመገለጡ እንደ እርሱ ያለ፣ በደል አልባ፣ እንከን የለሽ፣ ነቅ ያልተገኘበት … አብን የሚያረካ መሥዋዕት አልተገኘም።

“ለኃጢአት የሚቀርበው መሥዋዕት ንጹህና ነውር የሌለበት እንደ ኾነ ኹሉ እንዲሁ ክርስቶስም “ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም፤ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥” “ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ”(1ጴጥ. 2፥22፤ ዕብ. 7፥25) “የኃጢአታችን ማስተስረያ ኾነ” (1ዮሐ. 2፥2)”[1] እንዲል፣ ከለበሰው ሥጋ የተነሣ፣ “ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፥” (ዕብ. 10፥4)፤ አዎን፤ ስለ ተወለደልኝ መሥዋዕት ኾነልኝ!

3.  መካከለኛዬ ይኾንልኝ ዘንድ

መጽሐፍ ቅዱስ በአጭር ቃል እንዲህ ይላል፣ “በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤” (1ጢሞ. 2፥5)፤ ኢየሱስ ክርስቶስን በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ብቸኛ መካከለኛና አስታራቂ ያደረገው፣ ከቅድስት ድንግል ሥጋ በመንሣቱና በመወለዱ ነው። ሥጋ ለብሶ ባይወለድ መካከለኛ እስከ ዛሬ ሊገኝ ባልተቻለ ነበር።

4.  ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እኖር ዘንድ

እግዚአብሔር አምላክ ሰው በሠራው ኀጢአት ምክንያት እንዲህ በማለት ተጸጸተ፤ “መንፈሴ በሰው ላይ ለዘላለም አይኖርም፥ እርሱ ሥጋ ነውና፤” (ዘፍ. 6፥3)። ኀጢአት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ብርቱ ግድግዳ በማኖር ሰውን ከእግዚአብሔር ፍጹም አቀያየመው። ነገር ግን ክርስቶስ ሥጋ በመልበሱ ምክንያት፣ እግዚአብሔር ከሰው ጋር ዕርቅን ለመመሥረት ወደደ። ዕርቅን መመሥረት ብቻ ሳይኾን፣ በነቢያት እንዲህ ብሎ ትንቢትን አስነገረ፣ “መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፤” (ኢዩ. 2፥28) ይህንም እውን በማድረግ እንደ ተናገረው፣ ከጌታ ትንሣኤና ማረግ በኋላ መንፈሱን በማፍሰስ እውን አደረገው; (ሐ.ሥ. 2)።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ በክርስቶስ ከኾኑት ኹሉ ጋር ሊኖር ወደደ፤ ፈቀደ። እናም ክርስቶስ ሥጋን በመልበሱ እነሆ መንፈስ ቅዱስ ከእኔ፤ ከእኛ ጋር ሊኖር ወደደ!

5.  ያድነኝና ይቤዠኝ ዘንድ

መልአኩ፣ ስለ መሲሑ እንዲህ ያለ ምሥራች ተናግሮአል፣ “እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።” (ማቴ. 1፥21)። ሰውን ከኀጢአቱ ማዳን የሚቻለው የናዝሬቱ ኢየሱስ፤ የተወለደው ወንድ ልጅ ብቻ ነው። እርሱም እኔን ለማዳን ሥጋ ከመልበስ በቀር ሌላ አንዳችም አማራጭ አልነበረውም፤ ሊያድነኝ እኔን ኾነ፤ እኔን ወደ ራሱ ይስበኝና ያቀርበኝ ዘንድ እኔ ወዳለኹበት ወደ ተሰበረውና ወደ ወደቀው ዓለም መጣ።

ጠላቴና ባላጋራዬ ሰይጣን የተሳለቀበትን ሥጋዬንና ኹለንተና ሰውነቴን ኢየሱስ በፍጹም ሰውነቱ ለብሶት፣ የመቤዣና የመዳኛ መንገድ አደረገው። ሊያድነኝ ሥጋ ለበሰ፤ ተይዞ በመገረፍና በመታሠር ሊቤዠኝና ነጻ ሊያወጣኝ ደካማውን ሥጋ በመልበስ ክብሩን ኹሉ ተወልኝ።

የተወለድክልኝ ኢየሱስ ሆይ፤ እወድሃለሁ፤ አሜን፤ ሃሌሉያ!



[1]ኢየሱስ ማን ነው?” ከሚለውና ካልታተመው መጽሐፌ የተወሰደ፡፡

3 comments:

  1. እግዜር አድሜና ጤና ጨምሮ ይስጥህ

    ReplyDelete
  2. ተባረክ እግዚአብሄር ይጠብቅህ አሜን

    ReplyDelete
  3. God bless you,dear

    ReplyDelete