“ዋቄስትና - ዋቄፈናና ክርስትና ምንና ምን ናቸው?” ከሚለውና በቅርብ
ከሚታተመው መጽሐፌ የተወሰደ!
“… አቴቴ ለምልክትነት ወይም የባህሉ ምልክት ብቻ ከመኾን ያልፋል፤ በኦሮሞ
ማኅበረ ሰብ ዘንድ ከማኅበራዊ እውነታነቱ ባሻገር አምልኮአዊ ምልከታዎች አሉት።[1] አቴቴ የፍሬያማነት፣ የወላድነት፣
የእናትነት ክብር መገለጫ ናት። አቴቴ ሴት ልጅ በመንፈሳዊ ልዕልናና ክብር ውስጥ የመውለድን ሞገስ እንድታገኝ ጸጋ የምትሰጥ
ናት። ሰላማዊ የሴት መለኮት ኃይል[2]
ወይም የሴቶች መንፈስና[3]
በዓመት አንድ ጊዜ የምትከበር ሲኾን፣ የመከበርዋም ምክንያት የማኅፀንና የፅንስ ባርኮትን (goddess of fertility)
ባራኪ አማልክት ናት ተብሎ ነው።[4] ሴቶችም አቴቴን ስለ ጤናና ስለ መውለድ
ይለማመናሉ።
ስለ አቴቴ አመጣጥ የዋቄፈና ትውፊታዊው ተረት እንዲህ
የሚል ነው፤
“በአንድ ወቅት ባልና ሚስት በአንድነት ሲኖሩ ልጅ
ስላልነበራቸው ባልየው ለረጅም ጊዜ በብስጭት ይኖር ነበር። ልጅ እንዲኖረው የነበረው ፍላጎቱ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ
በመሄዱ አብራው ያለችውን ሚስት ሳይፈታ ሌላ ሚስት አገባ። የመጀመሪያ ሚስቱም በዚህ አድራጎቱ እጅግ አዘነች። ከዕለታት አንድ
ቀን ውኃ ለመቅዳት ወደ ወንዝ ወርዳ ሳለች የባሏ አስከፊ አድራጎት ትውስ አላት። ከዚያም እራስዋን በራስዋ ልትቈጣጠረው
ባልቻለችው መንገድ ጎንበስ ብላ በምንጩ ዳር ከሚገኘው ለምለም ረግረግ ሣር ውስጥ አንድ ነገር በእጇ አንስታ ከብብትዋ ውስጥ
ወተፈችና፣ “ፈጣሪዬ ችግሬን ታውቃለህ እንደምትረዳኝም አልጠራጠርም” በማለት ወደ ቤቷ ተጓዘች። ከቤቷ እንደ ደረሰችም ከብብቷ
ውስጥ ያቀፈችውን ነገር አውጥታ ተመለከትችው። የሚያማምሉ የጨሌ ዶቃዎችና ለምለም ቄጠማ ሆኖ አገኘችው። በዚህ አጋጣሚ መንፈስዋ
የተረበሸችው ሴት ኹኔታውን በአከባቢው ለሚኖሩ አንድ ሽማግሌ ገለጸችላቸው። ሽማግሌውም ይህ በችግሯ ልትረዳት የመጣች የአንዲት
መንፈስ ምልክት መኾኑን ካስረዷት በኋላ በምን ዓይነት ኹኔታ ልታስተናግዳት እንደሚገባ መከሩዋት።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የአቴቴ እምነት በዚህ ሰበብ በሰዎች
አስተሳሰብ ሊሰርጽ እንደ ቻለ ይነገራል።”[5]
ይላል።
አቴቴ በሚከበርበት ቀን ሴቶች በጨሌና ጫጩ የተጌጠ ባሕላዊ ልብሳቸውን
ለብሰው፣ የተለየ መጠጥ[6]
በማዘጋጀት በማብላትና በማጠጣት በአሉን ያከብራሉ። ጨሌን መውረስ የምትችለው በበኵር ልጅዋ ሚስት ስትኾን፣ አንዲት ሴት ወንድ
ልጅ ከወለደች አምስት ጊዜ እልል ይባላል፤ ምክንያቱም እናቲቱ ጨሌውን የምታስተላልፍበት ዘር በማግኘቷ ነው።
የአቴቴ በአል በሚከበርበት ቀን የሴቲቱ ባል የተለያዩ አገልግሎቶችን
ያገለግላታል (ያርድላታል፣ ስጦታዎችን ይሰጣታል) እንጂ ፈጽሞ አያዝዛትም፤ እርሷ ትበላለች፣ ትጠጣለች፣ በውበት አጊጣ አምላኳን
እያመሰገነች ስትዝናና ትውላለች እንጂ ፈጽሞ ማንም አያዝዛትም። እስከ አምስት ቀንም ይህ ሥርዓት ይቀጥላል።
ከአቴቴ በዓል ጋር በተያያዘ ሴቶች ጋብቻቸውን እንደ ፈጸሙ ሲንቄያቸውን
በመያዝ የሲንቄ እናት፣ የጨረቃ እናትና የሰላም እናትን መርጠው ይቀባሉ ወይም ይሾማሉ።
አቴቴ ዘርንና ትውልድን የምትባርክ ስለ ኾነች የምትከበር ናት። በተለይም
ደግሞ ምሷን ለሚሰጣት፣ በአግባቡ ለሚያስተናግዳት ፍሬያማ ምርትን፣ ብልጥግናን፣ ጤናን፣ መውለድን ትሰጠዋለች። ምሷን ማቋደስ
ካጎደለ፣ በእርሷ ላይ እምነት ከሌለው እርሷም ተንኮል ትሠራበታለች፤ እርሱና ቤተሰቡ ጤናን ያጣሉ፣ ከብቶቹ በበሽታ ያልቃሉ፤
ልጆቹም ይሞታሉ ተብሎ ይታመናል።
በአሉ የኦሮሞ ሴቶችን
የተለያዩ መብቶቻቸው የምታስከብር እንደ መኾንዋ፣[7]
የተለያዩ ስሞችም ተሰጥቷታል፤ አቴቴ ጊምቢ፣ አቴቴ ሓራና አቴቴ ዱላ ትባላለች። ጊምቢ ማለት ግድግዳና ከለላ ነው፤ የእርስዋን
ከለላነት የሚያምኑባትን ከልላ የምትጠብቅ፣ ሓራ ማለት ደግሞ ሐይቅ ማለት ነው። የሐይቆች፣ የወንዞችና የምንጮች አማልክት ናት።
ዱላ ደግሞ እንደ ስምዋ፣ በጦርነት ወቅት የምትዋጋና የምትከላከል ናት። አቴቴ ሓራ፣ ሩኅሩኅ ናት ሲባል ዱላዋ ግን እጅግ ቁጡ
ናት ይባላል።[8]
እንግዲህ ይህን ነው
ባህል እንጂ አምልኮ አይደለም ብለው የሚሞግቱን?!
“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ.
6፥24)።
[1] Kassam, 1999; Smith, 1989
[2] Religion and social
transformation in Africa: a critical and appreciative perspective, Obaji M
Agbiji & Ignatius Swart, Research Institute for Theology and Religion,
University of South Africa, 2013. በዚህ ጥናት መሠረት ኦሮሞ አቴቴ ብሎ የሚጠራት በአማራ ክልል ደግሞ፣
የዛር መንፈስ መቅረብ ተብሎ እንደሚታመን ያወሳል።
[4] Atete, Goddess of The Oromo People and
her role in Women’s resistance to battering, Max Dashu, 2010.
[5] ኢትዮጵያ ታሪክ ወይስ ተረት፤ ገጽ
112-113
[6] ከታወቁት መጠጦች አንዱ booka(buqqurii) ተብሎ የሚታወቀው ነው።
[7] ድሪባ ገጽ 120፤ Haji Aadaam,
Tamaam. Atete Sirna Addunyaarratti addaa tan mirga Dubartoota Oromoo eegduu fi
eegsiftu. Dirree Dawaa, Khalaf Printing Press. 2011.
[8] ኢትዮጵያ ታሪክ ወይስ ተረት፤ ገጽ
112
No comments:
Post a Comment