Monday 26 September 2022

ከዕጸ መስቀሉ ወደ ተሰቀለው ፊታችሁን አቅኑ!

Please read in PDF

በዚህ ሳምንት ከሚከበሩት በአላት አንዱ፣ ጌታችን ኢየሱስ ተሰቅሎበታል የተባለው፣ የዕጸ መስቀሉ በአል ነው። የሚከበርበት ምክንያት በአጭሩ ሲገለጽም፣ አይሁድ በጥላቻ ኢየሱስ የተሰቀለበትን መስቀል ከቆሻሻ መጣያ ቦታ ወስደውት ስለ ቀበሩት፤ ይህን የተቀበለውን መስቀል ከዓመታት በኋላ በአንድ ሰው መሪነት የቆስጠንጢኖስ እናት የኾነችው ከዓመታት ፍለጋ በኋላ፣ የተቀበረውን የእንጨት መስቀል እንዳወጣችና በአሉም ከዚህ ጊዜ ጀምሮ መከበር እንደ ጀመረ ይተረካል።

የዚህ በአል ትልቁ ትኵረት ዕጸ መስቀሉን ማወዳደስና ማክበር፤ ማንገሥም ነው። በዚህ በአል ቀን በመስቀል ስለ መመካት፣ በመስቀል ስለ መታመን፣ ለመስቀል ስለ መስገድ፣ መስቀልን ስለ መማጸንና ሌሎችም የአምልኮ ዝማሬዎች ይቀርባሉ። በዚህ ከተሰቀለው ክርስቶስ ይልቅ የተሰቀለበት ዕጽ ወይም እንጨት ገንኖና ከብሮ፤ ተመልኮም ይውላል።

ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፤

“ … መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፥ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፥ ለተጠሩት ግን፥ አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎችም ቢሆኑ፥ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው።” (1ቆሮ. 1፥22-24)

የክርስቶስ እውነተኛው መስቀል ማለትም፣ ስለ እኛ በበረት መወለዱ፣ በምድር በጽድቅና በቅድስና ፍጹም መመላለሱ፣ መሞቱና መቀበሩ ከጥንትም ለብዙዎች ሞኝነትና ማሰናከያ ነበር። ምክንያቱም የተሰቀለው ክርስቶስ ለብዙዎች፣ “ነገሩ ቢሰማ የማይታመን፤ ምስክርነቱም ሊቀበሉት የሚቸግር ነው” (ኢሳ. 53፥1፤ ዮሐ. 12፥37-38)፤ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ አባባል ማሰናከያ ወይም ሞኝነት ነው። በተጨማሪም ከዓበይት ነቢያት መካከል አንዱ ኢሳይያስ ይህን ሲናገር፣ መሲሑ “የተናቀ፣ ከሰውም የተጠላ፣ ሰው ፊቱን የሚሰውርበት፣ በመቅሰፍት የተመታ የሚመስል፣ መቃብሩ ከክፉዎች ጋር የተደረገ በመኾኑ” (ኢሳ. 53፥3-4፡ 9) በብዙዎች ዘንድ የተወደደ አይደለም።

ክርስቶስ የሚወዳት፣ ሙታንን እያስነሣ በ“ግርምት” የመላት፣ ለብዙ ሺህ ሕዝቦችዋ እንጀራ አበርክቶ ያበላት ኢየሩሳሌም፣ እንደ ዋዛ የካህናት አለቆችንና የሕዝብ ሽማግሌዎችን ሰብስባ ልትገድለው ጉባኤ ሰየመች (ማቴ. 27፥1)፤ ብዙዎች አፌዙበት፤ ዘበቱበት፣ ተፉበት፤ ልብሱን ገፈው ተሳለቁበት፣ ሲሰቀል ብዙዎች ራሳቸውን እየነቀነቁ አፌዙበት (ማቴ. 27፥29-31)። ማንም ሊረዳው እስከማይችል ድረስ፣ እንደ ተረገመና እንደ ወራዳ ወንበዴ ለክፉዎች ተላልፎ ተሰጠ። ከእርሱ ወንበዴ ይሻላል ብለው፣ ወንበዴውን ነጻ አውጥተው ኢየሱስን ለሞት አሳልፈው ሰጡት።

ብዙዎች ሊያዩት የተጸየፉት ስቁሉ ክርስቶስ፣ እርሱ መድኃኒትና የኀጢአትን ምንጭ በደሙ ቀጥ ያደረገ ብቸኛ ቤዛ ነው። አጣድፈው የገደሉት ጌታ እርሱ የሕይወት መገኛና ራስ ነው (የሐ. ሥ. 3፥15)። ቅዱሳን ሐዋርያት ይህን ታላቅና ዘላለማዊ እውነት ነው በሚሰማና ከፍ ባለ ድምጽ የመሰከሩት። ዕጹን ሳይኾን የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስ፤ ዕጽ ተሸክመው ሽባ አልፈወሱም፤ ይልቁን “በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ” (የሐ. ሥ. 3፥6) በማለት ስሙን በአደባባይ ጠሩት እንጂ።

ሰይጣን ዋናውን አስጥሎ፣ ዕራፊውን ማስያዙ ያሳዝናል። ልክ እስራኤል በአንድ ወቅት ሙሴ በምድረ በዳ የሰቀለውን እባብ፣ ወደ መቅደሱ አስገብተው ያጥኑትና ያመልኩት እንደ ነበረ፣ በኋላ ግን ሕዝቅያስ ከመቅደሱ አውጥቶ ነሁሽታን(ነሐስ ብቻ) ብሎ እንደ ሰባበረው (2ነገ. 18፥4)፤ ዛሬም የተሰቀለውንና ዋናውን ክርስቶስን አስጥሎ፣ እንጨቱ ላይ ብቻ ተንጠልጥለን እንድንቀር ያደረገንን “መስቀል(እንጨት) ብቻ” ብሎ በድፍረት የሚያስወግድ ብርቱ ትውልድ ያስፈልገናል።

የተሰቀለውንና ለማያምኑ ኹሉ የተናቀ፣ የተጠላ፣ የተረገመ የተባለውን የተሰቀለውን ክርስቶስን ወድደን፣ ዕጽ(እንጨት) ብቻ የኾነውን መስቀል ከማምለክ ልባችን ይመለስ ዘንድ በክርስቶስ ፍቅር እንማልዳለን።

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።

3 comments:

  1. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  2. የሰማነውን በልቦናችን ያሳድርብን

    ReplyDelete
  3. አይ ተሀድሶ እንዲህ ሆነህ ቀረህ? ክህደት አደ አርዮስ ይሉሀል ይህ ነው። መስቀልን እንጨት የሚሉት መናፍቃን ያንተ አይነቶቹ ናቸው። እኛ የክርስቶስ ደም ያረፈበት በደሙ የተቀደሰ የመዳናችን ምልክት ነው የምንለው። አንተ እንደምትለው አናመልከውም ይልቅ መስቀሉን ስናይ የተሰቀለውን ክርስቶስን ነው የምናየው። ለምን ከምታጭበረብር ለይቶልህ ጴንጤነትህን አታውጅም?

    ReplyDelete