Saturday, 10 September 2022

በዘመናት የሸመገለው “የሰው ልጅ”!

 Please read in PDF

ከሰማይ በታች ያለው መላለም(መላው ዓለም) አንድ ቀን ወይም በጌታ ቀን፣ በታላቅ ድምጽ፣ በትኵሳትና በመቅለጥ ሊያልፍ ቀን ተቀጥሮለታል፤ መጽሐፍ፣ “በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፥ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፥ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል።” እንዲል (2ጴጥ. 3፥10)። ሰማይና ምድር የሚያልፍበት ኹኔታ፣ የሰው ልጆች ኹሉ ሥራ በእግዚአብሔር ፊት የሚመረመርበት ወይም የሚታይበት መንገድ እጅግ አዳጋችና ኹኔታውን ለመግለጥ የሚያስቸግር እንደ ኾነ ይታመናል፤ ለጌታ ግን ኹሉ ይቻላል!

ጌታ እግዚአብሔር፤ ግዑዙንና እጅግ ሰፊውን ይህን የምናየውን ዓለም ማሳለፉና ማቅለጡ ባይደንቅም፣ እርሱ ግን ከዘላለም እስከ ዘላለም ጸንቶና በማይለወጥ ማንነት መኖሩ፣ እጅግ የሚደንቅና ለሀያ አራቱ ሽማግሌዎች፣ ለአራቱ ሰማያውያን ፍጡራን፣ ለአእላፍ ጊዜ አእላፍ፤ ሺህ ጊዜ ሺህ ለኾኑ መላእክት የአምልኮና የዝማሬ ምንጭ ነው፤ “ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በዙፋን ላይ በተቀመጠው ፊት ወድቀው፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሕይወት ለሚኖረው እየሰገዱ … ክብርና ውዳሴ ምስጋናም” ሰጡት እንዲል፤ (ራእ. 4፥10-11፡ 9)።

በበብሉይ ኪዳን በዘመናት ስለ ሸመገለው “የሰው ልጅ” በግልጥ የተናገረው፣ ነቢየ እግዚአብሔር ዳንኤል ነው፤ እርሱም በትንቢቱ እንዲህ ሲል ይናገራል፤“በዘመናት የሸመገለውም ተቀመጠ፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ፥ የራሱም ጠጕር እንደ ጥሩ ጥጥ ነበረ፤ ዙፋኑም የእሳት ነበልባል ነበረ፥ መንኰራኵሮቹም የሚነድድ እሳት ነበሩ።” (ዳን. 7፥9 እና 22)። የዳንኤል ምዕ. 7 ዐውዱን ስናጠና፣ ዳንኤል ስለ ተመለከተው ራእይ የሚናገር ነው፤ ራእዩም እርስ በእርሳቸው ስለማይመሳሰሉ አራት አስፈሪ አውሬዎች የተመለከተው ነው፤ አውሬዎቹ በአንበሳ፣ በድብ፣ በነብርና በአስፈሪ ኹኔታ ስለ ተገለጠ ሌላ እንሰሳት ናቸው። እንሰሳቱ የሚወክሉት፣ በምድር ላይ በተከታታይ ዘመን የሚነግሡትን ምድራዊ መንግሥታትና ከእነርሱ ጀርባ የሚሠራውን የክርስቶስን ተቃዋሚ መንፈስን “ጭምር” የሚወክል ነው፤ (7፥15 ጀምሮ)።

ነገር ግን እኒህ ሃያላን መንግሥታትና ድል ነሺ የሚመስሉ ማለትም በብረት፣ በናስ፣ በብርና በወርቅ ተመስለው፣ ነገር ግን በሸክላ መሠረት ላይ ያሉትን የምድር መንግሥታት ኹሉ ድል የሚነሣ አንድ ብርቱ ገዥና አሸናፊ ንጉሥ አለ። እርሱም “የታመነ ምስክር ከሙታንም በኵር የምድርም ነገሥታት ገዥ የኾነ ኢየሱስ ክርስቶስ” ነው፤ (ራእ. 1፥5)። ዳንኤል እንደ ተናገረለት ደግሞ እርሱ፣ በዘመናት የሸመገለ ወይም ጥንታዌ ጥንት ነው፤ ለእርሱ ዘመን አይቆጠርለትም፤ ዘመኑ ጥንት ወይም መጀመሪያ የሌለው አልፋ ነው።

ኹሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጐናጸፊያም በእርሱ ይለወጣሉ፥ ይለወጡማል፤” እንዲል፣ ጻድቁ ብላቴና ክርስቶስ፣ ዓመቶቹ ከቶ ሳያልቁ ዘመናትን አስረጅቶ ብቻውን ከዘላለም እስከ ዘላለም ጸንቶ ይኖራል፤ (መዝ. 102፥26-27፡ 12፤ 9፥7፤ ዕብ. 13፥8፤ ያዕ. 1፥17፤ 1ጢሞ. 6፥15)። በዘመናት የሸመገለው ጌታ ወይም ከጥንት የኖረው ጥንታዌው ጌታ፤ በኋለኛው ዘመን ከቅድስት ድንግል፣ በለበሰው ሥጋ ሰው ኾነ፤ የሰው ልጅም ተባለ፤ ራሱንም የሰው ልጅ ብሎ ጠራ፤ (ማቴ. 11፥19፤ 13፥41፤ 16፥13፤ ማር. 2፥28፤ 8፥38)። እኛን ለማዳን የተዋረደውን የሰውን ልጅ ሥጋ ገንዘብ በማድረጉ፣ ዘመን የማይቆጠርለት ዘመን ተቆጠረለት፤ በዘመናት የሸመገለውና የምድር መንግሥታትን የሚገዛው ጌታ፣ እርሱ ለሕግ የታዘዘ፤ ራሱን ባዶ በማድረግ ፍቅርን ገለጠ። ትሁቱ ጌታ ዳግመኛ ይመጣል፤ ሲመጣ ግን በፍርድና በኃይል በአሸናፊነትና በድል ነሺነት ይመጣል። ማራንአታ!

ዘመን የተጨመረልን፤ ከጊዜና ከዘመን ቍጥር ውጭ ለኾነው ጌታ ክብርን እንድናመጣ ነው፤ በምድራችን ላይ ያለው ነገር፣ እግዚአብሔር የሚያየውና የሚቆጣጠረው አይመስልም፤ ነገር ግን እንዳንዘንጋ! በዙፋኑ የተቀመጠው ጌታ ዛሬም አለ፤ እርሱ ልጆቹን ብቻ ሳይኾን፣ መንግሥታትንም ያያል፤ ይመለከታል፤ በፍርዱም ያጠራቸዋል። በእርሱ የሚታመኑና ለእርሱ በመገዛት የሚኖሩ፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ በረከትና ዕረፍት አላቸው። የሰው ልጅ ከተባለውም ከኢየሱስ ጋር በአንድነት ይገዛሉ፤ ያሸንፋሉ፤ ድል ይነሣሉ፤ ከእርሱ የተነሣም ከዘላለም እስከ ዘላለም በሕይወት ይኖራሉ። በመሲሑና ለዘመናት በሸመገለው ጌታ እንዲህ እናምናለን፤ እንታመናለን። አሜን። 

5 comments:

  1. 🥰🥰🥰በጣም ልብን ጠልቆ የሚገባ ገለፃ ነው

    ReplyDelete
  2. We are blessed by your grace

    ReplyDelete
  3. ዳንኤል 7
    ¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
    ¹³ በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት።
    ¹⁴ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።

    በዘመናት የሸመገለ የሚያመለክተው እግዚአብሔር አብን ሲሆን የሰው ልጅ ደግሞ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ነው:: ከዚህ ጥቅስም የምንረዳው አና አካል (person) እንዳልሆኑ ነው::

    ReplyDelete
    Replies
    1. Wow thankyou... ስላሴ ሚሉት ነገር ድሮም ግራ አጋቢ ነበር

      Delete
  4. ዳንኤል 7
    ¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
    ¹³ በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት።
    ¹⁴ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።

    The ancient of days is God the Father, while the 'son of man' is our Lord Jesus Christ. They are not one person!

    ReplyDelete