Thursday 1 September 2022

መድሎተ ስሑት ወይስ “መድሎተ ጽድቅ”?! (ክፍል ፲፱)

 Please read in PDF

የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን የእግዚአብሔር የራሱ ሥልጣን ነው ስንል፦

1.   ቃሉ የእግዚአብሔር ነው፦ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ስለ ኾነ፣ ለቤተ ክርስቲያና መሠረትና ዓምድዋ ነው። ቃሎቹ የእግዚአብሔር ባሕርይ ገንዘብ አድርገዋልና፣ መጽሐፍ ቅዱስ አይለወጥም (ማቴ. 5፥17)፤ ልብን ኹሉ ይመረምራል (ዕብ. 4፥12)፣ ይቀድሳል (ዮሐ. 17፥17)፤ ይፈውሳል (መዝ. 107፥20)።

የምናነበው የእግዚአብሔር ቃል፣ እግዚአብሔር ሊል የፈለገው ቅዱስ ቃሉን ወይም ፈቃዱን ነው። እግዚአብሔር የልቡን መሻት፣ ፍላጎቱን፣ ዐሳቡን ኹሉ የተናገረው በቅዱስ ቃሉ አማካይነት ነው። ከዚህ ታላቅ ነገር የተነሣ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ሥልጣን ይዞአል።

2.   በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ተጽፎአል፦ “ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።” (2ጴጥ. 1፥21) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ያለ መንፈስ ቅዱስ ከቶውንም ወደ ሰዎች አልመጣም።

በመንፈስ ቅዱስ ለመጻፉ ምን ማስረጃ አለ?

·        የቃሉ ምስክርነት፦ መንፈስ ቅዱስ ሲመጣ የኢየሱስን ቃሎች እንደሚያስታውስ መጻፉ አስደናቂ ነው። “አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።” (ዮሐ. 14፥26) እንዲል።

·        የመጽሐፉ ወጥነት፦

ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ወጥነት ወይም አንድ ዓይነትነት ስናወራ ብዙ ርዕሰ ጉዳዮችን አንስተን ማውራትና ማስረገጥ እንችላለን። ለምሳሌም እኒህን መጥቀስ ይቻላል።

1.   ከተጻፈበት ዘመናት አኳያ፦ መጽሐፍ ቅዱስ አያሌ ርዕሰ ጉዳዮችን በውስጡ አጭቆ ቢይዝም፣ አንደኛው ከሌላኛው ጋር የተሰናሰነና የተያያዘ፤ የተዛመደ፣ የታረቀ እንጂ ከቶውኑ እርስ በእርሱ የሚጋጭ አንዳች ዐሳብ የለውም። ከ40 በላይ ጸሐፍት በ1500 ዓመታት የዘመን ልዩነት ውስጥ ቢጽፉትም መሪውና ነጂው፣ አነቃቂና አጻፊው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ፈጽሞ አልተሳሳተም፤ አልተዘናጋምም።

የዓመታቱ መራራቅና በአንድ ዘመን ውስጥ ሳይኾኑ አንዳች ያልተፋለሰ እውነት ማቅረባቸውና መጻፋቸው እጅጉን የመንፈስ ቅዱስን ነጂነት እንድናደንቅ ያደርገናል።

2.   ከጸሐፊዎቹ ግለ ኹኔታ አኳያ፦ እጅግ የሚደንቀው በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው የሚጽፉት ጸሐፊዎቹ አንዳንዶንቹ እረኞች (ንጉሥ ዳዊት፣ ነቢዩ ሙሴ፣ አሞጽ)፣ አንዳንዶቹ ነገሥታት (ሰሎሞን፣ ዳዊት)፣ ሌሎቹ ዓሳ አጥማጆች (ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ቅዱስ ዮሐንስ)፣ ሌሎቹ ቀራጮች (ቅዱስ ማቴዎስ)፣ አንዳንዶቹ ሐኪሞች (ወንጌላዊው ሉቃስ) እንዲሁም በአስተዳደጋቸውና አኗኗራቸው ለምሳሌ፦ ነቢዩ ሙሴ በግብጽ ሲያድግ፣ ዳዊት በቤተ ልሔም ነው ያደገው። ሰሎሞን ኢየሩሳሌም ሲያድግ ሉቃስ ግን ከኢየሩሳሌም ውጭ ነበር።

ነቢዩ ሕዝቅኤል በባቢሎን ምርኮ በተጋዘበት ሲጽፍ ቅዱስ ጳውሎስና ዮሐንስ የተወሰኑ መልእክቶችን በእስር ቤት ሳሉ ጻፉ (የዮሐንስ ወንጌል፣ ወደ ኤፌሶን፣ ፊልጵስዩስ፣ 2ኛ ጢሞቴዎስ፣ ፊሊሞና)። በተለያየ ኹኔታና በተራራቀ የኑሮ ዘይቤ ውስጥ ቢያልፉም ግን መንፈስ ቅዱስ ኹሉንም ተቈጣጥሮ አስጽፎአቸዋል።

3.   ከጸሐፊዎቹ አኅጉራተ ዓለም አኳያ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ቢያንስ በሦስቱ የተለያዩ አኅጉራት የተጻፈ ነው። በኤሽያ በአውሮፓና በአፍሪካ። ሙሴ በሲን ምድረ በዳ በአፍሪካ ሲጽፍ፣ ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ በሮም በእስር ቤት ጻፈ፣ ዳንኤል ደግሞ በባቢሎን ምርኮ ውስጥ ጻፈ፤ ዕዝራ ደግሞ በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ጻፈ።

4.   ጸሐፊዎቹ መጽሐፉን ሲጽፉ ከነበሩበት ኹኔታ አኳያ፦ ሌላው ቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉት በተለያየ ኹኔታዎች ውስጥ ነው፤ ዳዊት ከጦርነት ጊዜ በፊት ሲጽፍ፣ ኤርምያስ ደግሞ ከእስራኤል መውደቅና መማረክ በፊት ጻፈ። ቅዱስ ጴጥሮስ እስራኤል በሮም ባርነት ሥር ሳሉ ሲጽፍ፣ ኢያሱ ደግሞ በከነዓን ምድር እንደ ጻፈ ማስተዋል እንችላለን።

5.   ከቅዱሳት መጻሕፍት ከተጻፉበት ዓላማ አኳያ፦ ቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉበት አያሌ ዓላማዎች አላቸው። ኢሳይያስ የእስራኤል ቅዱስ በኀጢአት ምክንያት ሊፈርድና ከፍርዱም በኋላ እንዴት ባለ ተሐድሶ ጉብኝት እንደሚያደርግ ሲጽፍ፣ ማቴዎስ ደግሞ አይሁድ፣ የተወለደውን ኢየሱስ “መሲሐዊ ንጉሥ” ብለው እንዲያምኑ ጻፈ።

ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ በአውሮፓና በኤጅያን ደሴቶች ላይ ነበሩትና በተለያየ ችግሮች ውስጥ ለነበሩ፣ ደግሞም ትክክለኛውንም የመዳንን እውነት ወይም የጽድቅን መንገድ በትክክል እንዲረዱ ለብዙ አብያተ ክርስቲያናትና ለመጋቢያንም ስለ እረኝነት ሥራቸው እንዲተጉ ለመምከር መልእክታትን ጻፈ።   

በእነዚህ ኹሉ አስደናቂ ኹኔታዎች ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ኹሉንም ጸሐፍት በመንዳት አንድ መጽሐፍ ቅዱስን አስጽፎታል፤ አእላፍ ጉድኝቶችና ተዛምዶዎች ቢኖሩም አንድና ወጥ መጽሐፍ ቅዱስን ቅዱሳን ሰዎችም ጽፈዋል።

በማናቸውም ኹኔታና በጸሐፊዎቹ የኑሮ ዘይቤ ውስጥ አልፎ የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንዱ ከሌላው ጋር ሳይቃረን፣ ሳይቀዋወም፣ ሳይጋጭ በአንድ ቅኝት አንዱ ከሌላው ጋር በፍጹም ተዛምዶ ተጽፎአል።[1] ኹሉንም ጸሐፍት የነዳውና የቃኘው ታላቁ መሪ መንፈስ ቅዱስ ነው።

ይህ በልዩትነት ውስጥ ያለው ፍጹም የኾነው የመጽሐፍ ቅዱስ አንድነትና ወጥነት፣ መጽሐፍ ቅዱስ የመለኮት እስትንፋስነቱንና ፍጹም ሥልጣናዊ መኾኑን ማስተዋል አያዳግትም። ከዚህ በፊት እዳመለከትነው፣ በተጨማሪ በሚቀጥሉት ምዕራፎችም የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ እንዴት የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን እንደ ተቃወመ እንመለከታለን።

ይቀጥላል …



[1] Josh McDowell, Evidence That Demands a Verdict (San Bernardino: Here’s Life Publishers, 1979), 17.

No comments:

Post a Comment