Sunday, 18 September 2022

“ጳጳስ፣ የማይነቀፍና የአንዲት ሚስት ባል ሊኾን ይገባዋል!”

 Please read in PDF

አባቶቻችን ሐዋርያት በነበሩበት ዘመን ሳይፈቱት የቀረ ችግር፣ ረስተው የተዉት ነገር የለም። በመልእክታቸው ተጽፎ የምናገኘው እምነታቸውን ደግሞም የእምነታችውን ሥርዓት ነው። በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ሰጥተዋል። ከእነዚህ ውሳኔዎች አንዱ የጵጵስና ጉዳይ ነው። ጳጳስ መኾን ያለበት ምን ዓይነት ሰው ነው? እኛ የሐዋርያትን ውሳኔ ላለመቀበል ቃላትን በመሰንጠቅ ትርጉምን ማጣመም ውስጥ ካልገባን በስተቀር፣ እውነቱን በቀጥታ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኘዋለን።

ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል የሚለው ቃል የታመነ ነው። እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊኾን ይገባዋል፤ የማይነቀፍ፥ የአንዲት ሚስት ባል፥ ልከኛ፥ ራሱን የሚገዛ፥ እንደሚገባው የሚሠራ፥ እንግዳ ተቀባይ፥ ለማስተማር የሚበቃ፥ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ ነገር ግን ገር የኾነ፥ የማይከራከር፥ ገንዘብን የማይወድ፥ ልጆቹን በጭምትነት ሁሉ እየገዛ የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር፤ ሰው ግን የራሱን ቤት እንዲያስተዳድር ባያውቅ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ይጠብቃታል?” (1ጢሞ. 3፥1-5)።



የአባቶቻችን የሐዋርያት ትምህርት ግልጥ ያለ፤ አንድምታ የማያስፈልገው ትምህርት ነው። ጳጳስ መሆን ያለበት፣ ባለ ትዳርና ልጆች ያሉት ሰው ነው። እግዚአብሔር በቤተ ሰቡ ውስጥ ማስተዳደርን ካስተማረው በኋላ፣ ቤተክርስቲያንን እንዴት ማስተዳደር እንዳለበት ያውቃል። እንደ ሐዋርያት ትምህርት ጳጳስ መሆን ያለበት ለማስተማር የሚበቃ ነው። ገንዘብ የማይወድ የሚለውም የማይለወጥ እውነት ነው። ራሳቸው ሐዋርያት፣ ከቅዱስ ጳውሎስ በቀር ባለትዳር ነበሩ፤ በወንጌል አገልግሎት ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቅሱም፣ ሚስታቸውን አስከትለው ይሄዱ እንደ ነበር መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል፤ (1ቆሮ. 9፥5)።

ጋብቻ ርኩሰት አይደለም ምንኵስናም ቅድስና አይደለም ለሥራ ያመች እንደ ኾነ እንጂ። እንደ ጳውሎስ ትምህርት፣ “ምንኩስና” በእርግጥ ለወንጌል ከኾነ፣ የተሻለ አድርጐአል፤ (1ቆሮ 7፥37)። ከሐዋርያት ቀጥለው የተነሡ የቤተክርስቲያን መሪዎች ጳጳሳትም፣ እስከ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ባለትዳርና ራሳቸውን የገዙ ቅዱሳን ነበሩ። ታሪካቸውን ማጥናት ይገባናል።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ በግብጽ በረሃ እየተስፋፋ የመጣው ተነጥሎ የመኖር ፍልስፍና [መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም በወንጌል ምክንያት በመሰደድ ካልኾነ በቀር ተነጥሎ መኖር ለምን?] እንደ ፍልስፍናው አልዘለቀም። ተነጥሎ መኖር የሚለው ትምህርት ከአቅም በላይ በኾነ የተፈጥሮ አሸናፊነት እየተዳከመ መጣ። እናም የፍልስፍናው ተማሪዎች ከበረሃ የመጡ ቅዱሳን በመምሰል ወደ ከተማ እየገቡ ተፈጥሮአዊውን እውነታ መለማመድ ጀምሩ። መጽሐፈ መነኰሳት እንደሚናገረው መነኰሳትን ለመቆጣጠር ተብሎ ጥብቅ ሕግ ቢወጣም ሕጉን በመፈጸም ፍልስፍናውን በጥንቃቄ የሚከተል ሰው አልተገኘም።

ስለዚህ ተነጥሎ መኖር የሚለው ፍልስፍና ቀረና፣ የቤተክርስቲያንን አመራር ለመያዝ ልዩ ልዩ ትምህርቶች ተፈልስፈው ሥራ ላይ መዋል ጀመሩ። የፍልስፍናው ሕግ አልሠራም የሐዋርያት ቃልም ተሻረና መነኮሳት የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎች ኾኑ። የአንዲት ሚስት ባል የሚለው ቃል ተተወ። በስውር ከዚያችም፤ ከዚህችም መቀላወጡ ግን በብዙዎች ዘንድ እስከ ዛሬ ድረስ ቀጥሎ እናየዋለን፡፡

ምንኵስናን ወደ ሐገራችን ያስገቡት ዘጠኙ ቅዱሳን ናቸው ይባላል፤ ምንአልባት እነርሱ በዘመናቸው ወንጌልን ቢሰብኩም፣ ተነጥሎ የመኖር ፍልስፍናንንም ሰብከዋል። ምንኵስና እስከ አሥራ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሀገራችን ከፍ ያለ ሥፍራ ይሰጠው ነበር።

በአሥራ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሱት አቡነ ተክለሃይማኖት፣ በሕግ ያገቧትን ሚስታቸውን ያለ ሕግ አባረው፣ ወደ ምንኵስናው ዓለም ከገቡና ከዚያም አልፎ የዛጉየዎችን መንግሥት ለመገልበጥ ባደረጉት የአሥራ ኹለት ዓመት ትግል፣ ሥጋዊ ነገር ውስጥ ገብተው በመገኘታቸው ተነጥሎ የመኖር ፍልስፍናው እጅግ እየቀለለ መጣ። ጵጵስናም በአንስብሮተ ዕድ፤ በቅብአተ መንፈስ ቅዱስ ሲሰጥ፣ ከሐዋርያት ጀምሮ የመጣው ትውፊት፣ እንደ ዋዛ በአቡነ ተክለሃይማኖት ተቀለበሰ።

አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ መልአኩ ሚካኤል የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ አድርጎ ሾሞኛል፣ በማለት ባልታወቀና በተድበሰበሰ ነገር ጳጳስ ኾኑ። የጵጵስና ቀኖና በመልአኩ እንደ ተሻረ አድርገው የቡልጋ ሰባኪዎች ሰበኩት፣ በመጽሐፍም ጽፈውት እስከ ዛሬ ድረስ ይገኛል። እነዚህ ሰባኪዎች በጻፉት ጽሑፍ ላይ፣ “ከተክለሃይማኖት ወገን በቀር የሚሾም አይኑር” በማለት የቤተክርስቲያንን ሹመት በዘር አደረጉት። ከዚህም የተነሣ ጵጵስና በጣም እየወረደ መጣ፣ ጠብና መለያየትም አብሮት መጣ፤ እስከ ዛሬ ድረስ አልበረደም።

ፍልስፍናው በዚህኛው አስተሳሰብ ከተወረሰ በኋላ፣ እስከ ዛሬ ድረስ ቤተክርስቲያኒቱ እየታመሰች ትገኛለች። ዛሬም ቤተክርስቲያኒቱን አልፎ አገሪቱን የሚያምሳት አንዱ ሰበብ ይኸው ነው። ለኢትዮጵያ ሕዝብ እስከ አሁን ድረስ ምሥጢር ነበር። ከዚህ በኋላ ግን የተሠወረ ነገር ይኖራል ብለን አናምንም።

እምነታችን ሐዋርያዊት ናት ሲሉ ምንም አያፍሩም፣ የሐዋርያትን ቃል አሽቀንጥረው ጥለው ሐዋርያዊ ነን እያሉ በስማቸው ይነግዳሉ። እኛ እንደ ሐዋርያት ትምህርት እንኑር ስንላቸው፣ ተሐድሶዎች ናችሁ ብለው በአድማ እነ ስም አያልቅባቸው ስም ይሰጡናል። ጳጳስ መኾን ያለበት እንደ ሐዋርያት ትውፊት ባለትዳር ነበር።

የዚህ ዘመን መነኰሳት ባለትዳር ቄስ ጳጳስ አይኾንም፣ ይህን ጥያቄ የሚያነሳ ተሐድሶ ነው ይላሉ። ነገር ግን እነርሱ ከኹለቱም አይደሉም። በምንኵስናው ሕግ አይመሩም አሊያም ትዳር መሥርተው ሥርዓት ይዘው አይጓዙም። በስውር እየወለዱ እንዲህ ቤተክርስቲያኒቱን ያዋርዳሉ እንጂ። እኛ መውለዳቸውን ወይም ማግባታቸውን አንቃወምም፣ ለምን ሕዝባችንን ቅዱሳን በመምሰል ያታልላሉ? ለምን በሕጋዊ መንገድ አያገቡም? ነው ጥያቄያችን።

እስከ አኹን ድረስ ሐሜት ነው እየተባለ ይወራ ነበር አኹን ሐሜት መኾኑ ቀርቶአል። የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት በታሪኩ ለጳጳሳት ሚስቶች የወራሽነት መብት በማጎናጸፍ አኩሪ ታሪክ አስመዝግቧል። በዚህ ዘመን ተሠውሮ የሚቀር ምንም የለም። እናም የኢትዮጵያ ሕዝብ የነቃ የበቃ ኾኖ ወደ ነጻነትና ወደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚደርስበትን መንገድ ኹሉ ለማሳየት ደከመን፣ ፈራን፣ ራበን፣ አንልም።

እውነት ነጻ ያወጣናል!

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።

1 comment:

  1. እየቀለድህ ነው አይደል? What do you mean by primary and secondary? Come on! let's stop confusing ourselves and others. A given word of God in the Bible has one and only one message for all of us. Primary, Secondary የሚለው ዝባዝንኬ ጸሐፊው እንዳለው የስህተት ትምህርቶችን እውቅና ለመስጠት የተደረገ ነው። እመቤታችንን ለማክበር የግድ ለክርስቶስ የተነገረውን ለእርሷ ማድረግ የለብንም። ይሄ የእግዚአብሔርን ቃል ማጣመም ነው። ክብር ለሚገባው ክብርን እንሰጣለን ግን ያለ ቦታው እና የመጽሐፍን ትርጉም በማዛባት አይደለም። YOur argument regarding some protestant's views on gays and lesbians is confusing. Are you saying we should stop discussing all other issues because of this? I think the witter has a valid point and has done a good job of pointing out a dangerous trend in our church to use the Bible in the wrong way to justify or exagerate some things. I don't understand your view of "value adding areas" Should we just talk about Pentes, Gays, Lesbians? please make yourself clear. ለክርርስቶስ የተነገረው ክብር, ማንነት ለሌላ መሰጠቱ፥ ላንተ ምንም ላይሆን ይችላል። ለአንዳንዶቻችን ደግሞ እጅግ ያሳዝናል። ጥያቄው እኮ እግዚአብሔር ለያዕቆብ ያንን ህልም ሲያሳየው ሊያስተላልፍ የውደደው መልዕክት ምንድንነው? ነው። መልዕክቱ አንድ እና አንድ ነው። እንደዚህም ነው እንደዛም ነው የሚለው ማወናበድ ስህተት ነው!

    ReplyDelete