Saturday 24 September 2022

ጳጳሳት ባሉበት ጉባኤ የሴት አገልግሎት!

 በአንድ ወቅት አቡነ መርሐ ክርስቶስ ባሉበት ጉባኤ፣ አንዲት “ዘማሪ” ስለ ተክለ ሃይማኖት፣ “ባለ ስድስት ክንፉ” ብላ ስትዘምር፣ “ሰውየውን ወፍ አደረገችው” ብለው አሳፍረው አስቀምጠዋታል ይባላል። በርግጥ የአደባባይ ስህተት አደባባይ ላይ መታረም አለበት፤ አግባብም ነው! በዚህ ረገድ አቡነ መርሐ ክርስቶስ ብዙ መልካም ምሳሌነት አላቸው።

ይህን እንድናገር ያደረገኝ ጳጳሳት ባሉበት ጉባኤ፣ አንዲት ሴት ግልጥ ያለ ስህተት ስትናገር ጳጳሳቱ ታግሠው መቀመጣቸውን በማየቴ ነው፤ ሴቲቱ ደፋር ናት፤ ሴቲቱ አረጋዊንና ዘመለኮትን ከሙታን አስነሥታ ምርጥ እንቶ፤ ፈንቶ፤ ድሪት ተረት በመተረት አቻ ያላት አይመስልም። ስለ ዮሐንስ ወንጌላዊ “መከራ ያልተቀበለ ሐዋርያ” ብላ ስትናገር፣ አብራው የነበረችና ኹለ ነገሩን የተመለከተች ይመስላል።

“ኢትዮጵያንና ተዋሕዶን አትለያዩ! እመቤታችንና ኢትዮጵያ አንድ ናቸው፤ አይለያዩም፤ ኢትዮጵያ ከሌላው ዓለም ፍጹም ትለያለች፤ የዳዊትን ዙፋን ይዛለችና” ብላ እድምተኛ ጉባኤውን በደንብ ታስጨበጭባለች። ከንቱ ትምክህት!

ሌላውና እጅግ አደገኛ ራስ ወዳድነትን የገለጠችበት መንገድ ነው፤ ይኸውም፣ “አርቆ ማጠር” በሚለው ዐሳብዋ ጦርነትን ሰው ምድር፣ ኑፋቄውንም ሰው ምድር ላይ ማድረግ እንጂ እኛ ምድር ላይ እንዲኾን መፍቀድ የለብንም የሚል ጸያፍ ዐሳብን ያለ አንዳች ፍርሃት ታንጸባርቃለች። የልጅቱ መናገር አይደንቅም፤ አለማወቅም፣ አጉል ድፍረትም፤ ከንቱ ትምክህትም ወዲህ ሊያደርሳት ይችላል። ነገር ግን ጳጳሳቱ እንዲህ ያለውን አለማወቅ እንዴት ታገሡ? ጉባኤውስ እንዴት እንዲህ ላለ ለማይረባ ዕውቀት ተላልፎ ተሰጠ ግን? ያስብላል።

ከ1000 እና ከ500 ዓመታት በፊት የሞቱ ሰዎች መጥተው መመሪያ የሚሰጡበት ጎዳና ምን ዓይነት ጎዳና ነው? ቅዱስ ቃሉና መንፈስ ቅዱስ ለምሪትና ለሕይወት ተሰጥተውን ሳለ፣ የሙታንን መንፈስ መሳብ ትክክል ነውን? ምሪትስ መስጠት ይችላሉን? አምልኮተ ኢትዮጵያስ የት ድረስ ይኾን ይዞን የሚሄደው? አምልኮ ካል ኾነ በቀር ከሶማሊያ፣ ከኢራቅ፣ ከኢራን፣ ከየመን የምትበልጥና ልዩ ኢትዮጵያን አላውቅም! … ሰው እንዴት የሕይ ወት ቃል እያለ የሞትን መንገድ ይመርጣል? ጌታ ኢየሱስ ለምድራችን እውነተኛ ፈውስን ያድርግ፤ የምድሪቱን ጥቅጥቅ ጨለማ በቃሉ ብርሃን ያርቅልን፤ አሜን።

1 comment:

  1. Ewinet, If you knew the bible and the church well, you would not say that. Do you know "ANDIMINTA Tirgum" in our church? What that means is detailed one-by-one interpretation of each and every verse in the bible. Andem this; andem that; lelam this... Thus, one verse can have three, four or more meanings depending on the case. I suggest that you talk to people who studied the Bible (old & new testaments) in our church. I can give hundreds of examples to highlight my point - I mean verses having multiple interpretaions. thanks.

    ReplyDelete