Thursday 6 February 2020

ንቀት (ክፍል ፲ እና የመጨረሻ ክፍል)

Please read in PDF
እንኪያስ፦
1.      ትናናቁ፦በማንኛውም የኑሮ ዘይቤ የሚኖሩ ሰዎችን ስታከብሩ፣ ሠሪያቸውን ወይም የፈጠራቸውን ያህዌ ኤሎሂምን ነው የምታከብሩት። እግዚአብሔር ሰውን ወደዚህ ምድር ሲያመጣው በትልቅ ዓላማና ለክብሩ መገለጫ ይኾን ዘንድ ነው። እኛ እንደ ሳይንቲስቶች ወይም እንደዚህ ምድር ጠቢባን በፈጠረው ዓለምና ሰው እጅግ በመደነቅና በመመሰጥ የምንዋጥና በዚህ ብቻ የምንቀር አይደለንም፤ ይልቁንም እግዚአብሔር ዓለምንና ሰውን የፈጠረው ያህዌ ኤሎሂም ከሰው ጋር ግላዊና ኅብረታዊ ግንኙነትን ሊመሠርት እንዳለው እናምናለን።

   እግዚአብሔር ሰውን በክብርና በሞገስ ፈጥሮታልና ፈጽሞ አይንቀውም፤ እግዚአብሔር ሰውን ሲመለከት በእርሱ ላይ ሊሠራ ያለውን ዓላማውን ይመለከታል፤ ስለዚህም እግዚአብሔር ሰውን እስከ ምድር ዝቅታ ድረስ መጥቶ ይፈልገዋል፣ ይገናኘዋል፣ ያከብረዋል፣ ውድና ቅዱስ ፈቃዱን በእርሱ ይፈጽማልና ሰዎች ሆይ! ሰውን ፈጽማችሁ አትናቁ፤ ደግሞም አትናናቁ!
2.     ሚንቁትን እንምከር፦ ሰውን የሚንቅ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ያኖረውን መልክና አምሳሉንና በምንቀው ሰው ላይ ሊፈጽም ያለውን መልካምና ቅዱስ ዓላማና ዕቅዱን የምንንቅ ወይም የሚንቅ ነውና፣ ሰዎችን የሚንቁ ሰዎችን ልንመክር፣ የእግዚአብሔርን ቅዱስ ዐሳብ ልናስረዳቸው ይገባናል እንጂ፣ የንቀታቸውን ተግባር ልንተባበር አይገባንም።
 ንቀት ንግግርና ግልምጫ ወይም ጠማማ ዕይታ ብቻ አይደለም፣ ዝንባሌንም ጭምር የሚያካትት ነው። ሰዎች በልባቸው ሰዎችን ንቀውና ተጠይፈው በፊታቸው ፊታቸው በፈገግታ ሊመላ የግብዝነት ሰላምታን ሊሰጡ ይችላሉ፤ ነገር ግን አብረን የምንውላቸውና የምናድራቸው ወንድሞችና እህቶች ዝንባሌአቸውን መግለጣቸው አይቀርም፤ የዚያን ጊዜ በእውነትና በፍቅር እንዲህ ካለ ጥዩፍ እንዲርቁ ልንመክራቸው ይገባል።
3.     ለፉም፦ ባለንበት ዘመን ወቀሳና ዘለፋ አሉታዊ የኾነ አመለካከት የያዙ ሰዎች ወደ መኾን ያዘነበለ ይመስላል። እናም የሚወቅሱና የሚዘልፉ ሰዎች በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ አይደሉም። ስለዚህም የአብዛኛዎቻችን ግንኙነቶች የእኩያና አዎንታዊ ነገርን ብቻ የታከከ፣ “ሰጥቶ መቀበል” ዓይነት ርምጥምጥና ውትፍትፍ ነው። በጌታ እናምናለን እያልን በንቀትና በጥላቻ፣ በዘረኝነትና በቡድንተኝነት መንፈስ ሥር ማየትን እንደ ዋዛ ማየት ከጀመርን ሰነባብተናል።
   ዘለፋ ተንቆአል፣ ወቀሳ ተጠልቶአል፣ ተግሳጽ ተገፍትሮ ከመካከላችን ተሰድዶአል፣ መመከርና መመካከር እጅግ ተዘንግቶአል፤ እናም ሰዎች በንቀት ታጅለውና በአደባባይ ሲገልጡትም የሚዘልፍ፣ የሚቆጣ፣ የሚገስጽ ከምድራችን ሳስቶአልና በብዙ መማለድ ያስፈልገናል። መካካብ፣ መወዳደስ፣ ስህተትና የአደባባይ ነውር እየታየ መዘላለፍ ከባልንጀርነት ፍቅር አልበጥ ብሎብናል።
   ወዳጆች ሆይ! እንደ ቃሉ መዘላለፍና መወቃቀስ በብዙ ይጠቅመናል እንጂ አንዳች አይጎዳንም፤ ቅዱስ ቃሉ፣ “ጻድቅ በምሕረት ይገሥጸኝ፥ ይዝለፈኝም፥ የኃጢአተኛ ዘይት ግን ራሴን አይቅባ፤ ጸሎቴ ገና በክፋታቸው ላይ ነውና።” (መዝ. 141፥5)፣ “ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም።” (2ጢሞ. 4፥2)። “ወዳጁን የሚንቅ እርሱ አእምሮ የጐደለው ነው፤ አስተዋይ ግን ዝም ይላል።” (ምሳ. 12፥11) አእምሮ የጎደላቸውን ዝለፉ፤ ውቀሱም!
4.     ደግሜ እላለሁ ማንም ማንንም አይናቅ፦ ተወዳጆች ሆይ! ባልንጀሮቻችሁን እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ስላኖረው መልክና አምሳሉ፣ በእነርሱ ላይ ስላለው ስለ ቅዱስ ዓላማ ስትሉ አትናቁ! እንደ ጢሞቴዎስ ያሉትን ታናናሾችን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ (1ቆሮ. 16፥10፤ 1ጢሞ.4፥11)፤ ስትናገሩና በዝንባሌአችሁ ኹሉ ከንቀት ጽዱ ኹኑ፤ (ቈላ.4፥6)። ጸጋው ይደግፈን፤ አሜን።
የሚንቁ ሲገጥሙን ምን እናድርግ?
1.      በጐ እንመልስ፦ “ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ።” (ሮሜ 12፥17)። በአንድ ወቅት ንጉሥ ዳዊት፣ ናባል በሚባል ሰው እጅግ ተንቆ እንደ ነበር እናስተውላለን፤ ነገር ግን የናባል ሚስት አቢግያ እጅግ አስተዋይ ሴት ነበረች፤ እናም ዳዊት ለተመለሰት የንቀት ተግባር እጅግ በቁጣ ተግባር ሊመልስ ሲሄድ የታደገችውና ይልቁን በጎ በማድረግ ከቁጣው ያበረደችውን ሴት እናስተውላለን፤ (1ሳሙ. 25፥1-38።
   የሚንቁአችሁን በመናቅና በመጥላት አትሸነፉ፤ ይልቁን ስድብንና ንቀትን ወደ ታገሰውና ወደ ተሰቀለው ኢየሱስ መመልከትን አትዘንጉ! ሰዎች እጅግ ክፉ በሚያደርጉባችሁ ነገር ኢየሱስ እንዴት እንደ መለሰና እንዴት እንዳሸነፈ ከከኢየሱስ ከሕይወቱና ከትምህርቱ በጥንቃቄ ተማሩ! ኢየሱስ እርሱ የማያሳስት ፍጹም መምህር ነውና! ክብር ይብዛለት፤ አሜን።
2.     ንጸልይ፦ ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ ብሎ አስተምሮናል፣ “እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና። የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ።” (ማቴ. 5፥44-48)።
  ለሚንቁአችሁ ጸልዩላቸው፣ ራሩላቸው፤ የሚንቁአችሁ በእናንተ ላይ ያለውን የእግዚአብሔርን መልክ ባያዩ ባያስተውሉም ነው፤ ስለዚህም ጸልዩላቸው እንጂ አትርገሙ፣ አትጥሉም፤ ጌታ ደግሞ በብዙ እንዲባርካችሁ፣ ወንድማችሁን ወይም እህታችሁን እንድታተርፉ በዚህ አስተውሉ!
“ማረን፥ አቤቱ፥ ማረን፤ ንቀትን እጅግ ጠግበናልና፤ የባለጠጎች ስድብና የትዕቢተኞችን ንቀት ነፍሳችን እጅግ ጠገበች።” (መዝ. 123፥3-4)
ማጠቃለያ
   መጽሐፍ ቅዱስ ግን እንዲህ በማለት የሰው ልጆች በሙሉ በእግዚአብሔር ፊት እኩል ዋጋ እንዳላቸው ይናገራል፡-“አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና።” (ገላ. 328) በእርግጥ በክርስትና የሰው ልጆች ዋጋ መሠረቱ በአምሳለ እግዚአብሔር መፈጠራቸው ነው። እያንዳንዱ ሰው ይህን የከበረ ምስል ስለ ተሸከመ ወንድ፣ ሴት፣ ነጭ፣ ጥቁር፣ የተማረ፣ ያልተማረ፣ አካል ጉዳተኛ፣ የተሟላ አካል ያለው፣ ሃብታም፣ ድኻ … ወዘተ. ሳይል እኩል ዋጋ አለው።
  “እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።” (ዘፍ. 127) እንዲል። እንኪያስ ምድራችንን ካረከሰውና ካሳደፈው የንቀትና የጥላቻ፣ የትዕቢትና የስድብ እቡይ ተግባር በመራቅ ለእግዚአብሔር ክብርን እናምጣ፤ ሰውን ኹሉ በመውደድም የእግዚአብሔርን መልክና አምሳል እናክብር! አልያ ግን ከእግዚአብሔር ጋር ስንጣላ፣ በሠራው ሸክላ ላይ ስንዘባበት እንዳንገኝ እጅግ እንጠንቀቅ! ስለ ንቀታችን ኹሉ ዋጋ ልንቀበል በክርስቶስ ወንበር ፊት እንቆማለንና ማንንም እንዳንንቅ በድጋሚ እላለሁ እንጠንቀቅ፤ (ሮሜ 14፥10) ጸጋ ይብዛላችሁ፤ ፍቅርና መጽናናቱ ይብዛላችሁ፤ አሜን።
  በነገር ኹሉ የረዳን የእስራኤል ቅዱስ ተወዳጁ ስሙ ይባረክ፤ አሜን። ተፈጸመ!

1 comment:

  1. "We ought to obey God, rather than men"

    ReplyDelete